Saturday, 14 January 2017 15:49

በ17ኛው የዱባይ ማራቶን ቀነኒሳ ለዓለም ሪከርድ ሲጠበቅ፤ ለመሰለችም ግምት ተሰጥቷታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው ለ17ኛ የዱባይ ማራቶን የሚሳተፈው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ  የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊሰብር እንደሚችል እየተጠበቀ ነው፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ ለመሰለች መልካሙ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ ከ5 ወራት በፊት በ43ኛው የበርሊን ማራቶን 2፡03፡03 በሆነ ጊዜ ያሸነፈው አትሌት ቀነኒሳ፤ ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ በርሊን ላይ የማራቶን ሪከርድ ስላመለጠው መበሳጨቱን አስታውሶ፤ በልምምዱ ላይ የተወሰኑ ለውጦች በማድረግ በዱባይ ሪከርዱን ለመስበር እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ከቀነኒሳ ባሸገር በዘንድሮው የዱባይ ማራቶን የማሸነፍ ግምት የተሰጠው በ2014 እኤአ ላይ አሸናፊ የነበረው ፀጋዬ መኮንን ነው፡፡
የ34 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ማራቶን ያሸነፈበት 2፡03፡03 በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ፤ በኬንያዊው ዴኒስ ኪሚቶ 2፡02፡57 በሆነ ጊዜ ከተያዘው  የዓለም ሪከርድ በ6 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ እንዲሁም ከ8 ዓመታት በኋላ አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ  መሆኑ ይታወቃል። ከ2፡04 በታች በመግባት በውድድሩ ታሪክ 10ኛ ሯጭ ሆኖ ለመመዝገብ የበቃበትም ነው፡፡   
በረጅም ርቀት ሩጫዎች በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን ከተቆጣጠረ ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ቀነኒሳ ከሳምንት በኋላ የሚሳተፍበት የዱባይ ማራቶን ብርቀት አይነቱ 6ኛው ይሆናል፡፡  የመጀመርያ ማራቶኑን በ31 ዓመቱ የሮጠው በፓሪስ ማራቶን በ2014 እኤአ ላይ ነበር ፡፡ በ2፡05፡04 በሆነ ጊዜ የግሉን ፈጣን ሰዓትና የቦታውን ክብረወሰን  አስመዝግቦ ሲያሸንፍ ያገኘውም የገንዘብ ሽልማት ደግሞ 41100 ዶላር ነበር፡፡ በዚያው ዓመት ከ6 ወራት በኋላ 2ኛውን ውድድር በቺካጎ ማራቶን ተሳተፈና በ2፡05፡51  በሆነ ጊዜ 4ኛ ደረጃን ለማግኘት ሲችል ሽልማቱ ደግሞ  25ሺ  ዶላር ነበር፡፡ በቺካጎ  ማራቶን ከሮጠ ከ3 ወራት በኋላ  ደግሞ በ2015 የውድድር ዘመን መግቢያ የመጀመርያ ወር ላይ 3ኛ ማራቶኑን ለመሮጥ የወሰነው በዱባይ ማራቶን ሲሳተፍ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር፡፡ ይሁንና በ30ኛው ኪሜ ላይ ውድድሩን በጉዳት ምክንያት አቋርጦ ወጣ፡፡ ከዚያም በኋላ አራተኛ ማራቶኑን በለንደን ይሮጣል ተብሎ ቢጠበቅም ተሳትፎውን ካገረሸበት ጉዳት ጋር ተያይዞ ሰረዘው፡፡ 4ኛውን የማራቶን ውድድር ለማድረግ የበቃው በ2016 የውድድር ዘመን በለንደን ማራቶን ነበር፡፡ በ2፡06፡36 በሆነ ጊዜ በ3ኛ ደረጃ ሲጨርስ የገንዘብ ሽልማቱ 72500 ዶላር ነበር።  ከዚያም በ43ኛው የበርሊን ማራቶን 5ኛውን ውድድር አደረገና  በ2፡03፡03 በሆነ ጊዜ አሸንፎ  ከ150ሺ ዶላር በላይ አግኝቷል፡፡
በዱባይ ማራቶን በሁለቱምፆ ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ ሁለት መቶ ሺ ዶላር የሚበረከት ሲሆን የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግብ 100ሺ ዶላር ተጨማሪ ቦነስ ሆኖ ይታሰባል፡፡ በሌላ በኩል በ2016 የተካሄደው የሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የመወዳደር ፍላጎቱ ሳይሳካለት የቀረው ቀነኒሳ ዘንድሮ በለንደን ከተማ በሚካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ቢናገርም ሁኔታዎች ግልፅ አይደሉም፡፡ ዋናው ምክንያት የዱባይ ማራቶንን ከሮጠ ከ4 ወራት በኋላ ደግሞ በ2017 የለንደን ማራቶን እነደሚሳተፍ እየተገለፀ በመሆኑ ነው፡፡ አሰልጣኑ ሬናቶ ናኖቫ አትሌቱ ከዓለም ሻምፒዮናው ይልቅ ትኩረቱ ለለንደን ማራቶን እንዲሆን እየገለፀም ነው፡፡
በተያያዘ ዜና በረዥም ርቀትና በአገር አቋራጭ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆነችው የ32 ዓመቷ  መሰለች መልካሙ በዱባይ ማራቶን ትኩረት ከሳቡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋና ተጠቃሽ ናት፡፡ ሰሞኑን በ2017 የዱባይ ማራቶን የግሏን ፈጣን ሰዓት ለማሻሻል ትኩረት ማድረጓን አስታውቃለች። ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት  በተሳተፈችባቸው የማራቶን ውድድሮች የተሳካላት መሰለች በዱባይ ማራቶን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን ባለፈው ዓመት በ2፡22፡29 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡  የመጀመሪያ ማራቶን የሮጠችው በ2012 እኤአ በፍራንክፈርት ማራቶን ሲሆን፣ ውድድሩን ስታሸንፍ 2:21:01 በሆነ ጊዜ ሲሆን  ብርቀቱ የተመዘገበላት ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ በ2016 የዱባይ ማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ በመካፈል 3ኛ ደረጃ ካገኘች በኋላ በሀምቡርግ ማራቶንም አሸንፋለች፡፡ ከወራት በፊት ደግሞ ያሸነፈችው የአምስተርዳም ማራቶንን ነበር፡፡ ከመሰለች ሌላ በዱባይ ማራቶን ከሚሳተፉት መካከል  ሹሬ ደምሴ፤ ታደለች በቀለ እና የብሩቃል መለሰ ይገኙበታል፡፡
ባለፉት 16 የዱባይ ማራቶኖች የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነትን የሚስተካከል አልተገኘም። በ2004  ጋሻው አስፋው፤ በ2005 ደጀኔ ጉታ፤ በ2008ና በ2009 ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2013 ሌሊሳ ደሲሳ፤ በ2015 ለሚ ብርሃኑ እንዲሁም በ2016 ተስፋዬ አበራ በወንዶች ምድብ አሸንፈዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ በ2004 ለይላ አማን፤ በ2005 ድርቤ ሁንዴ፤ በ2007 አስካለ ጣፋ፤፤ በ2008 ብርሃኔ አደሬ፤ በ2009 ብዙነሽ በቀለ፤ በ2010 ማሚቱ ደስቃ፤ በ2011 እና በ2012 አሰለፈች መርጊያ፤ በ2013 ትርፊ ፀጋዬ፤ በ2014 ሙሉ ሰቦቃ ፤ በ2015 አሰለፈች መርጊያ እንዲሁም በ2016 ትርፌ ፀጋዬ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡





Read 1366 times