Saturday, 14 January 2017 15:53

ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላከያ በአፍሪካ ደረጃ ቅድመ ማጣርያቸውን ከወር በኋላ ይጀምራሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክሉት  ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ በቅድመ ማጣርያ ተሳትፏቸውን ከወር በኋላ ይጀምራሉ፡፡ በ2017 ሁለቱ የአፍሪካ ትልልቅ የክለብ ውድድሮች በቶታል ኩባንያ ስፖንሰር በመደረጋቸው በየደረጃው የሚበረከተው የሽልማት ገንዘብ ከመጨመሩም በላይ  ከቅድመ ማጣርያ እና የመጀመርያ ዙር ማጣርያዎች በኋላ በሚቀጥሉት የምድብ ፉክከሮች የሚሳተፉ ክለቦች ብዛት ወደ 16 ማደጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ከቅድመ ማጣርያ አንስቶ 43 ፌደሬሽኖችን የወከሉ 55 ክለቦች ተሳታፊ ሲሆኑ ይሆናሉ፡፡ ትልቁ የክለቦች ውድድር ሆኖ ሲካሄድ ለ53ኛ ጊዜ ሲሆን በካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ ፎርማት ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ ነው፡፡
በ2008 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን በመሆኑ በሻምፒዮንስ ሊጉ ተሳትፎውን ለ23ኛ ጊዜ የሚያደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ ማር ኖይ የሚመራ ነው፡፡ ከ2011 እስከ 2015 በነበረው ተሳትፎ በካፍ የ5 ዓመት የውጤት ደረጃ በ3 ነጥብ 17ኛ ደረጃ በመያዝ በቅድመ ማጣርያ ተሳትፎውን ይጀምራል። ተጋጣሚው የሲሸልሱ  ሻምፒዮን ኮት ዲ ኦር ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታ ከወር በኋላ በሲሸልስ ዋና ከተማ  በአሚቴ ስታድዬም ይደረጋል፡፡  በ2013 እና በ2016 እኤአ የሲሸልስ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ኮት ዲ ኦር ዘንድሮ ሻምፒዮንስ ሊጉን ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፍበት ሲሆን በ2015 እኤአ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በቅድመ ማጣርያው ከሌላው የኢትዮጵያ ክለብ ደደቢት ጋር ተጫውቶ 5-2 በሆነ አጠቃላይ ውጤት ተሸንፎ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያው ኮት ዲ ኦርን ጥሎ ካለፈ፤ በቀጣዩየ1ኛ ዙር ማጣርያ የሚገናኘው ከኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፓርድስ እና ከካሜሩኑ ዩኤምኤስ ዴ ሉም አሸናፊ ጋር ነው፡፡
በ2008 የኢትዮጵያ ጥሎማለፍ ባገኘው ሁለተኛ ደረጃ በ2017 ቶታል ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ የሚሳተፈው መከላከያ በዋና አሰልጣኝሻለቃ አምሳሉ ገብረ ኪዳን ይመራል፡፡ በቅድመ ማጣርያው የሚገናኘው ከካሜሩኑ ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚ ሲሆን የመጀመርያው ጨዋታ ከወር በኋላ በአዲስ አበባ ስታድዬም ነው፡፡ በቅድመ ማጣርያው የደርሶ መልስ ትንቅንቅ መከላከያ የካሜሮኑን ክለብ ጥሎ ማለፍ ከቻለ በ1ኛ ዙር የሚገናኘው  ከቱኒዚያው ሲኤስ ሴፋክሲየን እንደሆነ ታውቋል፡፡
በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  እና ኮንፌድሬሽን ካፕ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሁለቱ ክለቦች እስከ ምድብ ማጣርያ በመድረስ አዲስ ታሪክ ማስመዝገባቸው የሚጠበቅ ይሆናል፡፡  በካፍ አዲስ የውድድር አሰራር መሰረት በሁለቱም የአፍሪካ ክለቦች ውድድሮች ወደ ምድብ ድልድሉ የሚገቡት ክለቦች ብዛት  ወደ 16 ማደጋቸው የፈጠረው እድል ንቻ ሳይሆን ወደ ምድብ ፉክክር በመሸጋገር ዳጎስ ካለው የገንዘብ ሽልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ማነጣጠር አለባቸው፡፡ ይሄው ስኬት ፌደሬሽኑንም በገንዘብ ሊያሸልም የሚበቃ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮት ዲ ኦርን በቅድመ ማጣርያው አሸንፎ በ1ኛ ዙር ተጋጣሚው የሚሸነፍ ከሆነ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ወርዶ የሚጫወትበት እድልም ይጠቀሳል፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንና በቶታል ኩባንያ ስምምነት መሰረት  ሁለቱ የአህጉሪቱ የክለብ ውድድሮች በየደረጃ የሚሸልሙትን የገንዘብ ሽልማት አሳድገዋል። በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 2.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ 1.25 ሚሊዮን ዶላር ዘንድሮ ለሚያሸንፉት ሻምፒዮን ክለቦች ተዘጋጅቷል፡፡ የክለብ ውድድሮቹ ላይ የኢትዮጵያዎቹ ክለቦች የሚኖራቸው ውጤታማነት ፌደሬሽን እንደሚጠቅም ከአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዝርዝር የሽልማ ክፍያዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን የሚያሸንፍ ክለብ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሸለም ፌደሬሽኑ 125 ሺ ዶላር፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚጨርስ ክለብ 1.25 ሚሊዮን ዶላር  ለፌዴሬሽኑ 62.5ሺ  ዶላር ፤ ለግማሽ ፍጻሜ የሚደርሱ 4 ክለቦች እያንዳንዳቸው 800ሺ ፌደሬሽኖቻቸው 40ሺ ዶላር፤ ሩብ ፍፃሜ የሚደርሱት ስምንት ቡድኖች እያንዳንዳቸው 650ሺ ዶላር ፌደሬሽኖቻቸው 32ሺ ዶላር፤ በየምድባቸው 4ኛ ደረጃ የሚያገኙት ክለቦች 550ሺ ዶላር ፌደሬሽኖቻቸው 27.5 ሺ ዶላር እንዲሁም በምድባቸው በመጨረሻ ደረጃ የሚጨርሱት ክለቦች እያንዳንዳቸው 550ሺ ዶላር ፌደሬሽኖቻቸው 22ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡

Read 2197 times