Saturday, 14 January 2017 15:56

የኡጋንዳው መሪ፤ ልጃቸውን ልዩ አማካሪያቸው አድርገው ሾሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ የአገሪቱ ልዩ የጦር ሃይል ሃላፊ ሆኖ ሲሰራ የቆየውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ሜጀር ጄኔራል ሙሆዚ
ኬነሩግባን የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ አድርገው መሾማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የተቋቋመውን ልዩ ሃይል ሲመራ የቆየውን የበኸር ልጃቸውን የ42 አመቱን ጄኔራል ሙሆዚ ኬነሩግባን በአማካሪነት መሾማቸው በአገሪቱ ቀጣይ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ ስልጣናቸውን ለማራዘም የያዙት እቅድ አካል ነው መባሉን ገልጧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ የጦር ሃይል መኮንኖች ሹም ሽር ያደረጉት ሙሴቬኒ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ዕድገት ያገኘውን ልጃቸውን በወሳኙ የአማካሪነት ቦታ ላይ መሾማቸው፣ ልጅዬው የሆነ ጊዜ ላይ የአባቱን ስልጣን ተረክቦ የአገሪቱ መሪ መሆኑ አይቀርም የሚለውን የቆየ ጥርጣሬ አባብሶታል ተብሏል፡፡የፕሬዚዳንቱ ልጅ ሜጀር ጄኔራል ሙሆዚ ኬነሩግባ፣ በጦር ሃይሉ ውስጥ ያለው ስልጣን
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ እያለ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው አመት ከብርጋዴር ጄኔራልነት ወደ ሜጀር ጄኔራልነት ማደጉንም አስታውሷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣን ላይ የወጡትና ለአምስት ተከታታይ የስልጣን ዘመናት አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የ72 አመቱ ሙሴቬኒ፤ ስልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በማሰብ ዘመዶቻቸውን በወሳኝ ቦታዎች ላይ እንደሚሾሙ
የጠቆመው ዘገባው፣ ወንድማቸው ሳሊም ሳልህ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ፣ ሚስታቸው ጃኔት ሙሴቬኒ ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡

Read 1074 times