Saturday, 14 January 2017 15:58

የፊሊፒንሱ መሪ፤ ከንቲባዎችንና ባለስልጣናትን እንደሚገድሉ አስጠነቀቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴሬ፤ ከአደንዛዥ ዕጽ ህገወጥ ንግድ ጋር ንክኪ ያላቸው የአገሪቱ ከንቲባዎችና ባለስልጣናት ከህገወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ አልያ ግን ያለአንዳች ማመንታት በግድያ እንደሚያስወግዷቸው ባለፈው ሰኞ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአደንዛዥ ዕጾች ንግድ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ 10 ሺህ የሚደርሱ የአገሪቱ ከንቲባዎች፣ አገረ ገዢዎች፣ የፖሊስ መኮንኖችና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትን ስሞች የያዘ ዝርዝር ሰነድ ማሰናዳታቸውንና እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የተጠቀሰ ከንቲባዎች፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ በአፋጣኝ ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁና ከህገወጥ ስራቸው እንዲታቀቡ ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህን በማያደርጉት ላይ ፈጣን የግድያ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደምም በከንቲባነት ሲሰሩ፣ከአደንዛዥ ዕጾች ህገወጥ ንግድ ጋር ንክኪ አላቸው ያሏቸውን የመንግስት ባለስልጣናት መግደላቸውን ማመናቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ አላቸው ባሏቸው ዜጎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ፣ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ5 ሺህ 900 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሲኤንኤን በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አስረድቷል፡፡

Read 1450 times