Saturday, 14 January 2017 16:06

“የስብሀት፣ የአብደላ እዝራና የጥላሁን - ቅኝት!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

ከሰንሰለታማው ዘቢዳር ተራራ ስር፣ እንደ ፋኖስ ብርሃን ጭል ጭል የሚሉ ትዝታዎችን ውስጤ የለኮሰው፣ የቡታጅራው መምህር ጥላሁን ሽሁር ነው፡፡ ጥላሁን ሽሁር፤ የሀያሲ አብደላ እዝራ የ45 ዓመታት ባልንጀራ፣ የደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር የትዝታ ጓደኛ፣ የደራሲ አውግቸው ተረፈ የጓደኝነት ቀኖች አስታዋሽ ነው፡፡
ከወራት በፊት በሞት የተለየው ሀያሲ አብደላ እዝራ፣ በድንገተኛ ህመም ያረፈው እዚሁ መምህር ጓደኛው ቤት ነው፡፡ አብደላና ጥላሁን፣ በዐይን የሚናበቡ፣ በግንባር የሚጣቀሱ፣ በከንፈር የሚገለማመጡ ነበሩ፡፡ የእኔና የአብደላ እዝራ አስተዋዋቂም ይኸው መምህር ነው፡፡
ታዲያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጉራጌና በስልጤ ዞን በነበረኝ ቆይታ፣ ካየኋቸውና ከሰማኋቸው ነገሮች ውስጤ ገብቶ ያመሰኝና የነፍሴን ሰንደቅ የነጠነጣት የጥላሁን ሽሁር የትዝታ ንግግር ነበር፡፡
ቡታጅራ ከተማ ከአንድ መድኃኒት ቤት ብቅ ብሎ ድንገት ሲጠራኝ ስልክ ባለመደወሌ ሀፍረት ቢጤ ቢሰማኝም፤ “ምን ላድርግ ታዲያ?” የሚል ምክንያቴን ለራሴ ሰጥቼ ተፋጠጥኩ፡፡ እውነትም በዚያ በሀዘን ጊዜ አዘጋጀው በነበረው የሬዲዮ ፕሮግራም ስለ አብደላ እዝራ ያወጋነውን ቅጂ መስጠት ይገባኝ ነበር፡፡ ግን … አልቻልኩም!
ያንን ተውኩትና … “ትንግርት ሬስቶራንት” ተያይዘን ሄድን፡፡ ስለ አብደላ እዝራ ሲያነሳ አይታክተውም፣ በሀዘን ምርር ይላል፡፡ ለእርሱ፣ ለልጆቹና ለባለቤቱ ያደረገውን እያነሳ ይቃጠላል። እኔ ደግሞ ወደ መፅናናት እንዲመጣ ሀሳብ እቀይራለሁ! … ግን አሁንም ከአብደላ እዝራ ጋር ተያያዥ ወደ ሆነው ወደ ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ትዝታ ሄደብኝ፡፡ ይሄኔ እኔም ማድመጥ ጓጓሁ፡፡ አብደላ እዝራንና አውግቸው ተረፈን ከጋሽ ስብሀት ጋር ያስተዋወቃቸው መምህር ጥላሁን ሽሁር እንደሆነ አብደላ በህይወት እያለ አውግተውኝ ነበር፡፡
በ1967 ዓ.ም ከምዕራብ ሆቴል ዝቅ ብላ ወዳለች አንዲት ሻይ ቤት ወሰደኝ - በትዝታ፡፡ ይህቺ ቀን ለመምህር ጥላሁን ሽሁር እንደ ህልም የምትታሰብና በተመስጦ የምትተረክ ናት፡፡ ቆቀርና ሻይ ይሸጥባታል፡፡ ያኔ ጥላሁን የዕድገት በህብረት ዘመቻ ምልምል በመሆኑ ምደባውን ይጠብቅ ነበር። ታዲያ በዚያ ጥበቃ ውስጥ ከሰዓት በኋላ ትንሿ ሻይ ቤት ቁጭ ብሎ ሳለ፣ አንድ ጥሩ አለባበስ የለበሰ፣ ፀጉር አቆራረጡ የሚያምር ሰው ወደ ሻይ ቤቷ ገባ፡፡ ከጥላሁን አጠገብ የነበረውን ባዶ ወንበር እያመለከተም፤ “ወንበሩ ሰው አለው?” በማለት ጠየቀው፡፡
“የለውም!” ሲል መለሰ ጥላሁን፡፡
ጥላሁን በኪሱ አንድ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ይዞ ነበር፡፡ ጋሽ ስብሀት ያቺን አይቷል፡፡ “ጫት ትቅማለህ?” አለና ጠየቀው፡፡ ጥላሁን ሆዬ ደስ እያለው፤ “አዎ!” አለ፡፡ ለካ ደክርቷል! የተማሪ ነገር! ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ፈጥኖ ወጣና ጫቱን ሸምቶ መጣ፡፡ ፌሽታ ሆነ፤ተማሪው ጥላሁን ተንበሸበሸ፡፡ ከዚያ ጨዋታ ጀመሩ፡፡
“ሥራህ ምንድን ነው?” ጥላሁን ጠየቀ፤ጋሽ ስብሃትን፡፡
“ራፖር ፀሐፊ ነኝ!”  
“አትመስልም…. ደግሞ ስለ መጻሕፍት ታውቃለህ!”
 “ራፖር ፀሐፊ እኮ ብዙ ነገር ያነብባል!” በማለት ጋሽ ስብሃት አድበሰበሰበት፡፡
ጥላሁን አልተዋጠለትም፡፡ ምክንያቱም ንግግሩ፤ አቋሙና አስተሳሰቡ ሁሉ ራፖር ፀሐፊ አይመስልም፣ ቅር እያለው፣ ወጋቸውን ቀጠሉ፡፡
ይሁን እንጂ የጋሽ ስብሀት ታሪክ ተሸፍኖ አልቀረም፤ ጨዋታው እየጦፈና እየተግባቡ ሲሄዱ፣ ምርቃናውም ነፍሱን ወደ ገራምነት ሲመልሳት፣ ደራሲ መሆኑንና ማስታወቂያ ሚኒስቴር መስራቱን ሁሉ ነገረው፡፡ ሰፈሩን … ቢሮውን …. ህይወቱን ሁሉ ዘከዘከለት፡፡ ይሄኔ … ጥላሁን ጮቤ ረገጠ፡፡ በልቡም … የትምህርት ቤት ጓደኞቹን እያስታወሰ ዕድለኝነቱን መረቀ፡፡፡ … ከጋሽ ስብሀት ጋር መተዋወቁን ለጓደኞቹ እስኪነግር ቸኮለ፡፡ በኋላም ለአብደላ እዝራ እንዲሁም “ሊቅ! ለሚሉትና ኢሕአፓ ተብሎ ለተገደለው ጎበዝ ተማሪ ጓደኛቸው … ለሌሎቹም ተረከላቸው፡፡ በሌላ ቀን ጋሽ ስብሀትን ቀጠሮ አስይዞት ስለነበር አንድ ላይ ሆነው አገኙት፡፡
ከሁሉ ይልቅ አብደላ እዝራ፣ ስብሀትን በመተዋወቁ ፈነጠዘ፡፡ ውሎ አድሮም ጋሽ ስብሀት መኖሪያ ቤቱ ድረስ ተረት ሰፈር ወሰዳቸው፡፡ “ደራሲው” የተሰኘው የበዓሉ ግርማ ገፀ-ባህርይ፣ የሲራክ ኑሮ፣ የጋሽ ስብሀት የራሱ እንደሆነም ቡታጅራ “ትንግርት ሬስቶራንት” ውስጥ ሆነን ጥላሁን አስታወሰ፡፡ ሀጂ ሙስጠፋ የሚባሉ ሰውዬ ቤት ተከራይቶ እንደሚኖር፣ እሳቸውም ቤቴን ልቀቅልኝ እያሉት፣ እርሱ ግን እዚያ ሰፈር ለድርሰት ተመችቶት፣ ስለወደደው፣ አልለቅም እንዳለ፣ የጋሽ ስብሀት ሚስት በበኩሏ፤ “አልፈልግም፣ እንውጣ!” እያለችው እንደሚጨቃጨቁ ሁሉ ጥላሁን በተመስጦ አስታውሶ….አወጋኝ፡፡
“ደራሲው” በተሰኘው የበዓሉ ግርማ ልብ ወለድ መፅሃፍ ገፅ 82 ላይ እንዲህ ይላል፡-
“… በአላህ ብለው ቢለቁልኝ” አላቸው (ቤቱን መሆኑ ነው)
“እስከመቼ?”
“አንድ መፅሐፍ ጀምሬአለሁ፡፡ እሱን እስክጨርስ ድረስ፡፡”
“የምን መፅሐፍ?”
“ልብ ወለድ መፅሐፍ ነው …”
“ይቀልዳሉ ልበል?”
“ቀልዴን አይደለም፡፡”
እብድ ነው ወይስ ጤነኛ እንደ ማለት በትንንሽ አይኖቻቸው ትኩር ብለው ተመለከቱትና፣ “ታዲያ መቼ የሚጨርሱት ይመስልዎታል?” አሉት፡፡
“አንድ ዓመት ወይም ሁለት … እኔ እንጃ፡፡ አሳቡ እንደተሳካልኝ ነው” አላቸው፡፡
“ለምን ሌላ ቦታ ሄደው አይፅፉም?”
“ስሜቱ ይበላሽብኛል፡፡ እዚሁ እንደጀመርኩት እዚሁ መጨረስ አለብኝ፡፡ ይታገሱኝ፡፡”
በዓሉ ግርማ ሀጂ ሙስጠፋን እንዲህ ይገልጻቸዋል፡-
“… በጣም ረጂም፣ ጠይም፣ አፍንጫቸው እንደ ሸንበቆ ቀጥ ብሎ የሚወርድ፣ ጆሮዎቻቸው ትላልቅ፣ አይኖቻቸው ትንንሽ፣ ሸበቶ ሽማግሌ ናቸው፡፡…”
የቡታጅራው መምህር ጥላሁን ሽሁር እንደነገረኝ፤ የስብሀት ገ/እግዚአብሔር የተረት ሰፈር ቤት አከራይ፣ ስማቸው ሀጂ ሙስጠፋ፣ መልካቸውም በመፅሐፉ ውስጥ የተሳሉትን ራሳቸውን ነው፡፡ ጋሽ ስብሀት ጥላሁንና ጓደኞቹን ብዙ ጊዜ ቤቱ ወስዶ ጋብዟል፤ አብልቷል አጠጥቷል፤ … አጫውቷል… አዝናንቷል። የሀጂ ሙስጠፋን ጭቅጭቅ … የጀመረውን ድርሰት ምጥ ሁሉ ያስታውሳሉ፡፡ የባለቤቱን ቅሬታም ጭምር! ባለቤቱ “ቤቱን እንልቀቅ!” ስትል፣ ጋሽ ስብሀት “አይሆንም፤ ድርሰቱን ሳልጨርስ አንለቅም” ይል ነበር፡፡  የያኔው የስብሀት ናፍቆት ደግሞ የተረት ሰፈር የልብ ትርታ፣ የነፍስ ጥሩንባ ነው፡፡ ጥሩንባ በነፍሱ ጆሮ የሚጮኸው ይህን እያስታወሰ ነበር፡፡ …
“… ተረት ሰፈር ፀጥ ብላለች፡፡ በቀን ደርቶ የሚታየው ጉልት ገበያ ተበትኗል፡፡ እንጀራ የሚሸጡ ጥቂት አሮጊቶችና ቆሎ የሚቸረችሩ ህፃናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ የመንደሩ ውሾች ጉልት ገበያው የዋለበትን ስፍራ እየተዘዋወሩ ያነፈንፋሉ፡፡ መንገዱ ላይ በብዛት የሚታዩት ከስራ የሚመለሱ ሰርቶ አደሮች ናቸው፡፡ አገልግላቸውን ይዘው በፍጥነት ይራመዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ቆም ብለው ከጉልት ያሉ ሴቶችም ወንዶች፣ እንዲሁም ወጣት የቤት ገረዶችና አሽከሮች፣ እነርሱም ደብተር ይዘው፣ ወደ መሰረተ ትምህርት ቤት ለመሄድ ይጣደፋሉ፡፡ …”
እያለ የመጽሐፉ ትረካ ይቀጥላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስዕል፣ ይህ ህይወትና መልክ በስብሀት ገ/እግዚአብሔር የእውኑ ዓለም ነበረ ብሎ፣ መምህር ጥላሁን ከዚህ ቀደም በአብደላ እዝራ ፊት (በጥቂቱ) አሁን ደግሞ በዝርዝር አጫወተኝ፡፡ … እንደ ሊዎ ቶልስቶይ፣ እንደ ፊትዝ ጌራልድ … የህይወቱን ጉዞ፣ የኑሮውን ገጠመኝ ፅፎልናል በዓሉ፡፡
ጓደኛውን ስብሀትንና ህይወቱን ይዞ፣ በፈጠራ ቀለም እየነከረ፣ በመንስዔና ውጤት አጣምሮ፣ በክብ ገፀ ባህሪ ውስጥ ግዙፍ ታሪክ አሸክሞት፣ የወለዳቸውን ገፀ ባህሪያት ከጫንቃው ሳይነጥቀው፣ ወይዘሮ አልታዬን ከእነ ስኒያቸው ከህዝብ ጋር አገናኝቷል፡፡
እኔም ይህንን ታሪክ ከታሪኩ ተጋሪ ከመምህር ጥላሁን ሽሁር አንደበት በግርምት ሰምቻለሁ። የምዕራብ ሆቴልዋን ታሪካዊ ሻይ ቤት፣ በዐይነ - ሕሊናዬ ሥዬ፣ ታላላቅ ሰዎች፣ ትልቅ ጥንስሳቸውን የገለጡበት ድንኳን አድርጌ ወስጃታለሁ፡፡
ከዚያ ግጥምጥሞሽ በኋላ የአብደላ እዝራ ብዕር “የስብሀት ጉድጓዶች”ን ወልዷል፡፡ ታላቁን የአጭር ልቦለድ ደራሲ አውግቸው ተረፈን ከስብሀት ገ/እግዚአብሔር ጋር አንድ የጥበብ መሶብ እንዲቆርሱ ፍጥነቱን ጨምሯል፡፡
ከዘቢዳር ተራራ ሥር፣ በ”ትንግርት ሬስቶራንት”፣ ረዥም የጥበብ ሰዎችን ግጥምጥሞሽ - ያጣጣመ ተረክ በግርምት አዳምጫለሁ፡፡ … ያዳመጥኩትንም እነሆ ለማለት ያህል ነው ይህችን ማስታወሻ መከተቤ!! ከዚህ ዓለም ለተለዩን ነፍስ ይማር! በህይወት ለቀረነው ጥበብ የሞላበት ዕድሜ ተመኘሁ!     

Read 4214 times