Saturday, 14 January 2017 16:05

‹‹ከአቅም በላይ መንጠራራት ትርፉ ጅማት መበጠስ ነው!››

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድኅን
Rate this item
(5 votes)

የመፅሐፉ ርዕስ፡- የባለቅኔው ኑዛዜ፤
ደራሲ፡- ፋሲል ከበደ፤ የገፅ ብዛት፡- 240

      በቅድሚያ አያ ሙሌን ከውልደቱ ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ያለውን ታሪክ የአቅሙን ያህል በመጽሐፍ ያቀረበልንን ፋሲል ከበደን አደንቃለሁ። በተለይም የልጅነት ወቅቱን በተመለከተ አብሮ አደጎቹን ጭምር በማነጋገር፣ላደረገው ጥረትና ትጋት አክብሮቴን እገልፃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በቀረበልን የባለቅኔ ሙሉጌታ ሕይወት ታሪክ ውስጥ የተፋለሱና ከእውነት የራቁ ሃሳቦችን አንብቤያለሁና፣ አያ ሙሌን ከልጅነት ዕድሜዬ ጀምሮ በኋላም በስራ መስክ ስለማውቀው ዝም ብዬ ማለፍ አልቻልኩም፡፡
‹‹አያ ሙሌ 1983 ዓ.ም ወደ ወልድያ ሲሄድ የኢህአዴግ ታጋዮች ወልድያ ውስጥ አፈላልገው ይዘውት ነበር፡፡ አያ ሙሌም በኢህአዴግ ታጋዮች ከተያዘ በኋላ ከወልድያ የኢህአዴግ ጦር ሠራዊትን ይዞ እየመራ፣ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አደረገ››
(ገፅ 24፤ አንቀጽ 4)  
 ጥሕሎ ድኣ ኩሕሎ
‹‹አያ ሙሌ በወርሃ ንዳድ የኢህአዴግን ጦር ሠራዊት ይዞ ጎዳናውን እየመራ ደጋውን፤ ቆላውን፣ ሸንተረሩን፣ አምባውን አልፈው በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እንዳይጠፋባቸው፣ አያ ሙሌን እንጦጦ ላይ ጠርንፈውት ነበር፡፡››
(ገጽ 31፤ አንቀጽ1)  
የመጀመሪያው ከወልድያ እንደተቀበላቸው ይገልፃል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከበረሃ ጀምሮ ይዟቸው መጣ የሚል አንደምታ አለው፡፡ የትኛው ነው ትክክል? ትክክለኛው ይኼ ነው ብሎ ፀሐፊው አላረጋገጥልንም፡፡ ሊያረጋግጥልን ደግሞ አይችልም። ምክንያቱም ሙሉጌታ ተስፋዬ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ፣እዚሁ ተቀበለው እንጂ ታጋይ ሆኖ ከበረሃ አልመጣም፡፡ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የብአዴን ታጋይ መሆኑ ግን እርግጥ ነው፡፡ እንዴት?
ለአንድ ነገር መፈፀም ወይም አለመፈፀም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ወሳኝነት አለው እንዲል አርስቶትል። የአቶ ፋሲልን የአሁን ስሜት ባላውቅም ብዙዎች በተለይ ለውጥ ፈላጊ የሆኑ ወጣቶችና ምሁራን፣ በዚያን ጊዜ የነበረውን ኢህአዴግ ለማወቅ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ የኢህአዴግ አባላትም ህዝብ ጋር ለመቅረብ፣ አላማቸውን ለማስረዳት ፍላጎትና ጉጉት ነበራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ብዙ ወጣቶችና ምሁራን ኢህአዴግን የሚደግፉ፣ ከኢህአዴግ ጋር መልካም ጊዜ ይመጣልናል የሚሉ ተስፈኞች ነበሩ፡፡ ይሄ የዚያን ጊዜ እውነት ሆኖ ቀልሟል፡፡ አያ ሙሌም በዚያን ወቅት ‹‹ግንቦት›› የሚል ግጥም ፃፈ፡፡
ግንቦት
እንደበካር ምጥ ዳር እስከዳር አላልቦት…
እያለ የሚቀጥል፡፡ ይህ ግጥሙ መነሻ ሆኖ ከብአዴኖች ---- ከአቶ በረከት ስምዖን ጋር ለመገናኘት ምክንያት ሆነ፡፡ ከዚያም የዋለልኝ መኮንን የትግል ታሪክ በቲያትር መልክ እንዲሰራ ትዕዛዝ ይሰጠውና፣ለመነሻ ይሆንም ዘንድ “ጎብዬ ከተማ ከዋለልኝ ቤተሰቦች ጋር ቃለ-መጠይቅ የተካሄደበት ካሴት፣ሴኩቱሬ ጌታቸው ዘንድ ታገኛለህና ሄደህ ተቀበል” ተብሎ የያኔው የኢህአዴግ ሬድዮ ጣቢያ ጋዜጠኞች ወደ ሰፈሩበት እንጦጦ፣ ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ግቢ መጣ፡፡ ሴኩቱሬን ሲጠይቀው፤ ካሴቱ እኔ ዘንድ (የዚህ ጽሁፍ ፀሐፊ) እንደሚገኝ ነገረውና፣ ወደኔ ሲያመራ በድምፅ አወቅሁት፡፡ ‹‹ጅብ አይበላሽ!›› ብዬ ከተቀመጥኩበት በደስታ ፈንድቄ ተነሳሁ፡፡ ተቃቀፍን፡፡ ተሳሳምን፡፡ እውነታው ይኼ ነው፡፡  
እውነታው ይኼ ከሆነ ታዲያ፤ ‹‹… አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እንዳይጠፋባቸው አያ ሙሌን እንጦጦ ላይ ጠርንፈውት ነበር›› ማለትን ምን አመጣው? እውነት ያልሆነን ታሪክ እውነት ነው ብሎ በመፅሀፍ ጠርዞ፣ ለተደራሲ ማቅረብ ድፍረት አይሆንም? አያ ሙሌ በጊዜው ለነበረው ኢህአዴግ ቀና አመለካከት በነበራቸው የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ወጣቶች፡- እነ ሲዛር አሰፋ፤ ጉልቱ ተፈራና እህቶቹ ሙኒትና ማርታ፣ እነ ሚሊዮን ኮሎኔል ካምፕፋየር አዘጋጅተው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ግንቦት›› የሚለውን ግጥሙን አቅርቦ አድናቆትን አትርፏል፡፡ በዚያን ጊዜ እኮ ሙሉጌታን የሚያውቁት የአካባቢው ተወላጆች እንጂ ሌላ የሚያውቀው አልነበረም፡፡
ታዲያ ኢህአዴግ እንዳይጠፋበት የሚጠረንፈው በምን ምክንያት ነው? የተሻለ ስልጣንና ቦታ ለማግኘት ይፋ ያልወጣ ሽኩቻ በጀመሩበት ወቅት፣ አንድ ባቅኔ ለእነሱ ምን ትርጉም ይሰጣል? እውነት እንነጋገር ከተባለ ከዚያስ በኋላ ቢሆን ለጥቂቶቹ ካልሆነ፣ትርጉም ሰጥቷቸው ያውቃል?.. አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋዜጣ ጀርባ ገጽ ላይና ማህቶት ጋዜጣ ላይ በሚያሰፍራቸው ግጥሞቹስ አያ ሙሌና ዋና አዘጋጆቹ ተግባብተው ያውቃሉ? ስለ አያ ሙሌው ከተፃፈው ያልተፃፈው ይበልጣል፡፡ በጽሁፍ ካወጋን ዘንዳም፣ እውነት እውነቱን እናውጋ፡፡ እንጦጦ ላይ አያ ሙሌን ማንም ተጠርነፍ ብሎ አስገድዶ ያስቀመጠው የለም፡፡ እንዲያ ካልሆነ፣ አያ ሙሌ የሚፈልገው ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ አዎና!... ፀሀፊው እንደገለፀው፤ ‹‹ጥይት›› ፈለጋኣ! አያ ሙሌ፤ ገንዘብን ‹ጥይት› ብሎ እንደሚጠራ በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል። በዚያን ወቅት የብአዴን አባልና በሬዲዮ ጣቢያው ገንዘብ ያዥ የነበረው፣ልጅ ቢልልኝ አፈወርቅ ይባላል። (ነብሱን ይማረው!) ቢልልኝ አያ ሙሌን እጅግ አብዝቶ ይወደዋል። እጅ ሲያጥረው እየበረረ እንጦጦ ከች ነው፤ ቢልልኝን ፍለጋ፡፡ አይከለክለውም፡፡ ከደሞዙም እላፊ ይሰጠዋል፤ ”ከሚቀጥለው ቀጥሎ ያለ ወር የሚከፈል ስጠኝ” ሲለው ይሰጠዋል። ለሌሎችም እንዲሁ ይሰጣል፤ በእምነት፡፡ ኋላ የገንዘብ ቁጥጥር ሲደረግ፣ አምኖ የሰጣቸውን መልሱልኝ ሲላቸው፤ ‹‹አይ ቢልልኝ፤ ወረቀት ያልያዘውን›› እያሉ የመለሱለት ነበሩ፡፡ ብዙ ገንዘብ አጉድለሃል ተብሎ ተባረረ - ምስኪኑ ቢልልኝ። ብዙም አልቆየ፤ አሸለበ፤ እስከ ወዲያኛው።
ያኔ አማተር የነበሩ ዛሬ አንጋፋ የሚባሉ ከያኒያንም መሀል፣ የቢልልኝን የዋህነት አይተው ገንዘብ ወስደው ያልመለሱለት፣ ኤፍሬም ታምሩ ያቀነቀነውን “ቢልልኝ” የሚለውን ዘፈን ሲሰሙ፣ ቢልልኝን እያስታወሱ፣ ”ያንን ሞኝ ኢህአዴግ ሰራንለት” አስተኔ ከዘፈኑ ጋር የሚወዛወዙ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ነገር ነገር አነሳውና፣ ከመነሻዬ ሃሳብ ወጣ አልኩ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ወደ ገደለው ልግባ፡፡
ምናልባትም ፀሐፊው፤ አያ ሙሌ ከጋዜጠኛ ተፈራ መኮንን ጋር ካደረጉት ሁለት ካሴት ሙሉ ቃለ-መጠይቅ ተቀንጭቦ፣ ፈርጥ መፅሄት ላይ የቀረበውን አላጤኑት እንደሆነ፣ በገዛ አንደበቱ እንዲህ ብሏል፡-
ጥ፡-     ለመሆኑ ወደ ትግል ገብተህ ነበር?
መ፡-   አሳምሬ፤ ታጋይ ነኝ እንጂ
ጥ፡- ከመቼ ጀምሮ?
መ፡- ከተፈጠርኩበት ቀን ጀምሬ፤ የወገንኩት ለኢህአዴግ ነው…
(ገጽ 101፤ አንደኛው አንቀጽ ግርጌ)
ከተፈጠርኩበት ቀን ጀምሮ ካለ በኋላ ድርብ ሰረዝ አለ፡፡ ልብ ይሏል? ከዚያም በኋላ የወገንኩት ለኢህአዴግ ነው፡፡ መወገን መደገፍን ያመለክታል፡፡ በሌላ መንገድ አያ ሙሌ ወደዚህ ዓለም የመጣው አንተም እንደገለጽከው፣ በ1946 ዓ.ም ነው፡፡ ያኔ ደግሞ ኢህአዴግ አልነበረም፡፡
በጋዜጠኛ ተፈራ መኮንን እጅ የነበረውን ካሴት አግኝቼ አዳምጨዋለሁ፡፡ አያ ሙሌ፤ ከተፈጠርኩ ጀምሮ ታጋይ ነኝ፤ ሲል---- በትምህርት ያሳለፈውን ጊዜ ሲገልፅ፡-
“ምን ልልህ ፈልጌ መሰለህ! በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ዲቃላ ነኝ፤ አባቴ ትግሬ ናቸው፡፡ እናቴ የዋድላ ደላንታ ሴት ናት፤ ወልድያ ውስጥ ሙጋድ የሚባል ቦታ፣ እናቴ በፊት ለፊት በር ጠላ ትሸጣለች፡፡ አባቴ ደግሞ በጓሮ በር በኩል ጨው ይሸጣሉ፡፡ እናቴ ጠላዋን እየሸጠች ታንጎራጉራለች፡፡ በእንጉርጉሮዋም የእኒህን ቄስ ቀልብ ትጠልፋለች … ቄሱ ሽማግሌ ቢልኩ አይሆንም ይባላሉ፡፡ በሯ አንዲት ነበረች። እናትና አባቴን የምታገናኛቸው፡፡ ቄስ ሆዬ፤ አይሆንም ሲባሉ ጊዜ፣ ያቺን አንዲት በር ገንጥለው ይገባሉ፡፡ ኸዚያ በኋላማ ወንድምህ ኸነቃጭሉ ዱብ ነዋ፤ በ1946 ዓ.ም፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የድኻ ልጅ ነኝ፡፡ እናቴ መጀመሪያ ትምህርት ቤት ያስገባቺኝን ቀን ነው እንጂ የማውቀው፣ ኸዚያ በኋላ የገዛቺልኝ ደብተርና እስክርቢቶ ትዝ አይለኝም፡፡ አለቀ፡፡ እዚህ ጋ ነው የተገኘሁት …”
አስተዳደግህስ?
ኸዚያ በኋላ እንግዲህ አስፋልት ዳር ነው ያደኩት፡፡ ሊስትሮም ሆኜ፣ የፈረንጅ አሽከርም ሆኜ፣ አስጎብኚም ሆኜ፣ የመሳሰለውን ሆኜ ላይ ታች እያልኩ፣ እየወደቅሁ እየተነሳሁ ነው የመጣሁት…
(ገጽ 100-101)
አያ ሙሌ ታጋይ ነኝ ሲል፣ ከልጅነቱ አንስቶ የመጣበትን በትግል የተሞላ ህይወቱን እንጂ በረሃ ወርጄ የመጣሁ ታጋይ ነኝ እያለ አይደለም፡፡ የፋሲል ብዕር ግን ለራሱም እርግጠኛ ባልሆነ መልኩ ትርጓሜውን ለውጦ የበረሃ ታጋይ ያደርገዋል፡፡
ፀሐፊው ፋሲል ከበደ አያ ሙሌን እጅግ አብዝቶ ይወደዋል፡፡ መጽሐፍን ያህል ነገር እስከ ማዘጋጀት፣ አሳትሞም ለህዝብ ለማድረስ እስከ መሻት ድረስ ለአያ ሙሌ ያለውን ውዴታ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ስሜታችንን ተከትለን እንዳንሄድ መጠንቀቅ ግድ ይለናል፡፡ በምዕራፍ 18፤ አያ ሙሌን ፀሐፊው ሲገልጽልን - (ገጽ 156፤ አንቀጽ 4 ላይ) እንዲህ ይለናል፡-
“አያ ሙሌ አንድ ነገር ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ የማወቅ፣የወደፊቱን የመተንበይ፣ ጨርቃቸውን የጣሉ እብዶችን የማዳን፣ ህመምተኞችን የመፈወስ፣ የሰውን የፊት መልክ በማየት ብቻ ማንነቱን የመለየትና የማወቅ እንደዚሁም ጥልቁን መንፈስ እየመረመረ፣ የረቀቁና ግዑዝ ነገሮችን እስከ ማናገር የደረሰ የብቃት ደረጃ - ፀጋ/ሥጦታ/ ነበረው፡፡”
አያ ሙሌ እንደ ባለቅኔ፣ እርግጥ ነው የመንፈስ ከፍታ አለው፡፡ ይህንንም በግጥሞቹ ውስጥ እናስተውለዋለን፡፡ ነገር ግን አያ ሙሌ ክርስቶስን አይደለም፡፡ እንደ ሰው የኖረ፣ ሰው ሆኖ ያለፈ ባለቅኔ ነው!
አቶ ፋሲካ ሊያሳዩን የፈለጉት ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ የልጅነት ጊዜውና አለፍ አለፍ ብሎ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንጂ በዚህ መጽሐፍ እኔ የማውቀውን አያ ሙሌ ሙሉ ለሙሉ አላየሁትም። ምን አልባትም ሌላ ልምድ ያለው ፀሐፊ፣ ይህን መጽሐፍ ቢፅፈው የተሻለ ነበር፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት 349 አንቀፆች መካከል፣ 234 የሚሆኑት አንቀፆች መደምደሚያቸው “ነበር” የሚል ነው፡፡ እንዴት ያሰለቻል! ደግሞስ አያ ሙሌ እንዴት በነበር ይደመደማል፡፡ ፍላጎቱን ነግሮን አልነበር?
“ምናልባት ልትሄድበት ያሰብከው አገር የት ነው? ብለህ ብትጠይቀኝ፣ የሰው ልጅ ልብ ውስጥ እምቡር እምቡር ነው የምልህ፡፡ ይሄ ነው የኔ አገር፤ ይሄንን ንገር፡፡”
አንድ ታዋቂ ባለሀብት ቢሞትና “ነበር” ተብሎ ቢደመደም ያስኬዳል፤ ምንም ነውር የለውም፡፡ እንዴ ባለቅኔ‘ኮ ነው! … አያ ሙሌ‘ኮ ነው! እንዴት በነበር ይደመደማል? … በአንደበቱ ያለን’ኮ፤”የኔ አገር የሰው ልጆች ልብ ነው” አይደል? በኔም ባንተም፣ በሌሎችም አድናቂዎቹ ልብ ውስጥ አያ ሙሌ የለም? በየልባችን ውስጥ እምቡር እምቡር እያለ አይደለም? አያ ሙሌ እኔም ጋ አለ፡፡ አንተም ጋ አለ። ነበር ብዬማ አላወራም፡፡
በመፅሐፉ ጀርባ ላይ ያለው ምስል፣ የመጽሐፉን ይዘት ይገልፀዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ የተወለደበትን ቤት፣ የፀሐፊው ምስል ሊሸፍነው እንደሞከረ ሁሉ፣ አያ ሙሌንም ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ የአቅሙን ያህል ሞክሯልና ሸጋ ነው፡፡ አያ ሙሌው ግን አልተገለፀም፡፡
የባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ስራዎችን እስቲ እናሰባስባቸው፡፡ ያልታተሙ ስራዎቹ በየሰው እጅ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የምናሰባስብበት ቢሆንስ? … እኔ ዘንድ ያልታተሙ ሁለት ስራዎቹ አሉ፡፡ “እኔም ቅኔ ልዝረፍ!” የሚልና “ብዕር ቀለም ቀንዱ!” የሚል ርዕስ ያላቸው፡፡ ይኸው በጀማሪነት ሰጥቻለሁ፡፡ ቢያንስ ልጁን እንታደገው፡፡
የመጀመሪያ ልጁ ዳኒ ቦይ፣ አንዳንዴም “ሸህ አብዲ” እያለ የሚጠራው ልጁ፣ጎዳና ላይ ወድቋልና፣ አያ ሙሌን ከወደድነው ----- እጃችን ከምን? ቸር ያክርመን!


Read 2515 times