Saturday, 14 January 2017 16:09

የዓለም መጨረሻ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(16 votes)

“የመጨረሻውን 48 ሰዓታት እንዴት ማሳለፍ ትፈልጋለህ” የሚል ፅሁፍ ማንበብ ጀመርኩና ሰለቸኝ፡፡ በዛ ላይ ፅሁፉ ረጅም ነው፡፡ በምድር ላይ ከቀረችኝ ሁለት ቀን ላይ የማይረባ ጽሁፍ በማንበብ ሽራፊ ሰከንድ ማሳለፍ አልፈለግሁም፡፡ ጋዜጣውን አጠፍኩት፡፡
የተቀመጥኩበት ካፌ በሰው ተሞልቷል። ሁሉም በአንድ ላይ ያወራል፡፡ በአንድ ላይ እያወራ፣ በአንድ ላይ ይደማመጣል፡፡ ካፌው ሻይና ማኪያቶ ማቅረብ ካቆመ ቀናት አልፎታል፡፡ ሰርግ ነው የሚመስለው። ውስኪ በየጠረጴዛው ተቀምጧል፡፡ ከቀኑ አራት ሰዓት ይላል ሰአቴ፡፡ ድካም ይሰማኛል ግን መተኛት አልቻልኩም፡፡ ማንም መተኛት አይሻም፡፡  
አንድ ወር ቀደም ብሎ ገና ዜናው ሲሰማ፣ የሰው ባህሪ ተቀየረ፡፡ “ከዚህ በፊትም እንደዚህ ተብሎ ነበር” ብሎ ዜናውን አላምንም ያለ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ሲፃፃፍ ከረመ። “አላምንም” የሚለው ሁሉ ግን የምድርን መጥፋት ፈላጊ ነበር፡፡ ቀስ እያለ ሁሉም ዜናውን ተቀበለው። ባለሀብቱ ያከማቸውን ሀብት እያወጣ ለደሀ ለመስጠት ልምምጥ ጀመረ፡፡ ግን ደሀውም ዜናውን ሰምቷልና አልፈልግም አለ። “ሞኝህን ፈልግ፤ በአንተ የግፍ ገንዘብ ማን ኩነኔ ይገባል” ብሎ ሀብታም ላይ ተሳለቀ፡፡
“የበደላችሁን ይቅር በሉ!” ብለው የሀይማኖት ተቋማት በምርጫ መቀስቀሻ መኪና ሌት ተቀን መለፈፍ ያዙ፡፡ መጀመሪያ ላይ ትንሽ እንደ ትንግርት፣ ህዝብ ቆሞ ከታዘባቸው በኋላ ጆሮ ዳባ ልበስ አላቸው፡፡ “ተያይዘን ሲኦል እንገባታለን እንጂ ስትበድለኝ ኖረህማ፣ አሁን መጨረሻ ላይ በይቅርታ ብቻ ከገሀነም አትፋታም” እያለ ምዕመኑ ተቋማቱ ላይ መዛት ጀመረ፡፡ ተቋማቱ ከህዝቡ የተለየ ፍርሐት ውስጥ ወደቁ፡፡ የሃይማኖት ልብሳቸውን እየደበቁ ተራ መስለው ከተራው ጋር ተመሳሰሉ፡፡
አንድ ሳምንት ሲቀር የመንግስት አገልግሎት ሁሉ ነፃ ሆነ፡፡ ትራንስፖርት - ነፃ፣ መብራትና ውሃ - ነፃ…፡፡ ባንክ ቤቶች፤ ”በነፃ ብር ካላበደራችሁ ትቃጠላላችሁ” የሚል የወመኔ ቡድን ስላሰጋቸው፣ ብራቸውን ጠቅልለው፣ በራቸውን ዘግተው ተሰወሩ። በየካፌው ነፃ መጠጥ እንዲቀርብ ተደነገገ፡፡ ሰው ሁሉ ሰካራም ሆነ፡፡ ግን ምንም አይነት አምባጓሮ አይታይም፡፡ እንዲያውም ደስተኛ ይመስላል ሰው ሁሉ፡፡
 በበረሀና በህገ ወጥ መንገድ የተሰደዱ፣ በህጋዊ መጓጓዣ ሀገራቸው መግባት ያዙ። “ለካ ተስፋ ነበር ሰውን ያባለገው” የሚል አስተያየት መናፈስ ጀመረ። ለካ ለመኖር የሚያደርገው መፍጨርጨር ነው የሰውን ልጅ ክፉ አድርጎት የነበረው፡፡ …
እና እኔም ዘና ብያለሁኝ፡፡ ማግኘት የምፈልጋቸው ሰዎች የሉም፡፡ ቢኖሩም የምናመራው ወደ አንድ መጨረሻ ስለሆነ እዛው እንገናኛለን፡፡ መለያየት አለመኖሩ ሁሉንም አረጋግቶታል፡፡  ዓለም ላይ በተለያየ ስፍራ እየተካሄደ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ይዘገባል፡፡ ዘገባው ለመጀመሪያ ጊዜ ፖለቲካም ሆነ ውሸት የሌለበት ሆነ፡፡ ዘገባውን የሚከታተሉ ይከታተሉታል፡፡ ግን ብዙም ትኩረት አይሰጡትም።
የክፉ ጊዜ አትራፊ ነጋዴዎችም አትርፈው የሚሸሸጉበት እንደሌለ ማወቃቸው አልቀረም። የሰበሰቡትን መስጠት ላይ አተኮሩ፡፡ ግን የሚሰጡት ነገር እንደ ቀድሞው ፈላጊ አልነበረውም፡፡ ዋጋው ያልረከሰ ሙዚቃ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም እስከሚሞት መስማት የሚፈልገው ሙዚቃ አለው፡፡ በጋራ ወይም በጆሮው ላይ ማዳመጫ ሰክቶ ያዳምጣል፡፡
የመጨረሻው የማስፈራሪያ ደወል ቢወደልም የፈራ ግን አልነበረም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ሁሉም “የሰው ልጅ መጥፊያው መቃረቡ ጥሩ ነው” ብሎ ያምናል፡፡ “መጥፋት የለበትም … እናድነው” የሚሉ ሳይንሳዊ ክርክሮች ከስመዋል፡፡ በሙዚቃው ውስጥ ተውጠዋል፡፡
“የቧንቧ ውሀ መጠጣት ጤናዬን ያሰጋዋል”… ብለው የተዉት ያገኙትን ውሃ መጠጣት ጀምረዋል። በጥንቃቄ የታሸገና ብዙ ብር ይገዙት የነበረውን ውሃ፣ አትክልታቸውን እያጠጡበት ይሳሳቃሉ። አትክልቶቹ የተመረጠ ውሃ በመጠጣታቸው እንደሚደሰቱ ያውቃሉ፡፡ ከራሳቸው ፍርሐት ነፃ መውጣታቸውን ለመግለፅ ይመስላል ----- ይሳሳቃሉ፡፡
“ድንግል ሆኜ መሞት አልፈልግም” የሚሉ ኮረዶች፤ የሆቴል ቤትና የወላጆቻቸውን ቤት ተቆጣጥረውታል፡፡ ጊዜ የለም፡፡ ፀሎት ማድረስ የሚፈልግም በጎዳና ተንበርክኮ ይጮሀል። እንደ ቀድሞው ለማስመሰል ወይ ለታይታ እንዳልሆነ ግልፅ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ብዙ የአዕምሮ ቀውስ ያለባቸው ሰዎች ድንገት ጤነኛ ሆኑ፡፡ ለዘመናት የሆስፒታል አልጋ የተቆጣጠሩ፣ የምድር ፍፃሜ ዜና እየቀረበ ሲመጣ፣ ከህመማቸው እያገገሙ ተነሱ፡፡
ለካ ሰብዕና ይህንን ያህል ያረጀ ልብስ ሆኗል? ብዬ አስባለሁ፡፡ እንቅልፍ ባልተኛም … መጠጥ ባበዛም፣ንዴትና ጭንቀት ሳይሆን ሰላም ነው የሚሰማኝ፡፡ በቃ ሰው ያረጀውን ህልውናውን መገላገል ፈልጓል፡፡ እጣ ፈንታ ሊገላግለው በመምጣቱም ደስተኛ ሆኗል። ደግሞ ይኼንን ደስታውን የሚነጥቀው ማንም የለም፡፡ ማንም ቀድሞ ወይንም ዘግይቶ አለመሞቱ፤ አንድ ላይ በአንድ ቅፅበት፣ ከጠፈር በሚመጣ አለት መጨፍለቁ እኩል ----- አድርጎታል፡፡
እኩልነት ለካ በዚህ መልክ ብቻ ነው እውን ሊሆን የሚችለው እያልኩ አስባለሁ፡፡ ግን በጣም ለጥጬ አላስብም፡፡ ያሰብኩትንም ለሰው አላካፍልም፡፡ ጭንቀት ውስጥ አይደለሁኝም፡፡ ሀሳቤን በማካፈል የምገላገለው ነገር ስለሌለ፣ለምን የሌላውን ጥሞና አጨናንቃለሁ?
የመጨረሻዎቹ አስራ ሁለት ሰዓታት ሲደርሱ፣ ምድር በሀይማኖት መጻህፍት ድሮ ነበረች እንደተባለችው ሆነች፡፡ ሁሉም ሰው የዋህና እውነተኛ፣ ተንኮልም ሆነ የመብለጥ ፍላጎት የሌለው ሆነ፡፡ ንግግሩን ቀነሰ፡፡ መጠጥ ሳይጠጣ መስከር ቻለበት፡፡ ስካሩ አዎንታዊ የሚባለው ነው። የሚያንገዳግድ ወይንም የሚያሰዳድብ ወይንም አምባጓሮ ቀስቅሶ የሚያጋጭ ሳይሆን የመሬት ስበትን ቀንሶ፣ በአየር ላይ የሚያንሳፍፍ አይነቱ ነበር፡፡
ሁሉም ሰው አዳም ፍሬውን ከመብላቱ በፊት የነበረው ልበ ሙሉነት በገፅታው ላይ ይታያል። ሁሉም ሰው ከፍርሐት ነፃ ሆኗል። ሁሉም ሰው የሰራውን ሀጢዓት ረስቷል። አዲስ ሰብዕናው ድሮ ሀጢአት ለመስራት ከተገደደው ሰብእናው ጋር ተሰነባብቷል። ከመሰነባበትም በላይ የቀድሞ ሰብዕናውን ከመወለድ በፊት ወይም ከሞት በኋላ እንዳለ ቅዠት ፈፅሞ ረስቶታል፡፡
የመጨረሻዎቹ አስራ ሁለት ሰዓታት እየተቀነሱ ሲመጡ የሰዓት ፅንሰ ሀሳብ ራሱ ትርጉም አልባ ሆኖ ነበር፡፡ በስምምነት ወይንም በድንጋጌ ሳይሆን በቃ ሰዓት ራሱ ሰዓት አልፎበታል፡፡ እንዳለፈበት ደግሞ ከራሱ ከሰዓቱ በስተቀር የሚገደው አላገኘም። የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲደርሱ በሰዓት አማካኝነት ሳይሆን ህያው ቀልቡ በየነብሱ ውስጥ ምልክት የሰጠው ሁሉ ወደ አደባባይ ወጣ፡፡ እንደ አመፅም እንደ ትዕይንተ ህዝብም ያልሆነ መሰባሰብ ተፈጠረ፡፡
እኔም ራሴን እንደ ግለሰብ ከዘነጋሁት ብዙ ሰዓታት እንዳለፉ እንኳን አላውቅም፡፡ ሁሉም ሀገር በስልጣኔ ወይንም ምጣኔ ሀብት ሳይሆን በሰውነቱ እኩል ሆኗል፡፡ መሆኑን እንኳን ማወቅ ግን አስፈላጊ አልነበረም፡፡
ሰው ተፈጠረ፡፡ በዛ …፡፡ እናም ጠፋ፡፡ አለቀ፡፡
ሲያልቅ ሁሉም ወደ ሰማይ አንጋጧል፡፡ እየመጣ ያለው ነገር ብርሃኑ ፊትን ያቀልጣል፡፡ ግን ማንም ከብርሃኑ ለመሸሽ ያጎነበሰ ወይንም ያጎበደደ አልነበረም፡፡     






Read 4486 times