Saturday, 14 January 2017 16:14

ሀበሻ ቢራ ለ“ጌርጌሴኖን” ግማሽ ሚሊዮን ብር ለገሰ በቅርቡ የሳሚ ዳን ኮንሰርት ይቀርባል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የቢራ ገበያውን ከተቀላቀለ አንድ አመት ተኩል የሆነው ሀበሻ ቢራ፤ በገና ዋዜማ ከጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከተገኘው የትኬት ሽያጭ ትርፍ 50 በመቶውን ሽሮሜዳ አካባቢ ለሚገኘው ‹‹ጌርጌሴኖን” የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ለገሰ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የኮንሰርቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለመገምገምና ተባባሪ አካላትን ለማመስገን፣ በራማዳ አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ የእራት ግብዥ ላይ ነው ግማሽ ሚሊዮን ብሩ የለገሰው፡፡
የሀበሻ ቢራ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ጌታነህ አስፋው - ለ“ጌርጌሴኖን” የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አየለ ገንዘቡን ካስረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የ“ገና በዓል የምስጋና፣ የመረዳዳት፣ የመጠያየቅና ደምቆ የመታያ በዓል በመሆኑ ከተገኘው የትኬት ሽያጭ ትርፍ ላይ 50 በመቶውን፣ (ግማሽ ሚሊዬን ብሩን) ለአዕምሮ ህሙማን መለገሳችን ያስደስተናል፤ ማዕከሉን በቀጣይ ለመደገፍ ድርጅቱ ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡
ድጋፍ በማጣት ማዕከሉን ወደ መዝጋት ታቀርበው እንደነበር የተናገሩት የ“ጌርጌሴኖን” መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አየለ፤ በተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ ሀበሻ ቢራና ሰራተኞቹ ማዕከሉን ሲደግፉ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ጠቁመው በህሙማኑ ስም አመስግነዋል፡፡ ሀሻ ቢራ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንሰርቱን ያዘጋጀውን ጆርካ ኤቨንትን ያመሰገነ ሲሆን በቀጣይ አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙዚቃ ኮንስርቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ጆርካ ኤቨንት፤ በአንድ ወር ውስጥ በመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነት ያተረፈውን የሳሚ ዳንን ኮንሰርት እንደሚያዘጋጅ ገልፆ በቅርቡ አጠቃላይ የኮንሰርቱን መረጃዎች ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ድርጀቱ በኢትዮጵያ ትልቁን የሙዚቃ ሽልማት ለማዘጋጀት በመሰናዳት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

Read 1787 times