Tuesday, 17 January 2017 00:00

የሰው ሀብት አመራር ባለሙያዎች ማህበር፤ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያዘጋጃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

 *የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው
                                 
     በተወሰኑ የሰው ሀብት አመራር ባለሙያዎች የተቋቋመውና በሰው ሀብት አያያዝ፣ በሰራተኛ ምልመላና ቅጥር ላይ አተኩሮ የሚሰራው "ሶሳይቲ ኦፍ ሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት ኢን ኢትዮጵያ” የተሰኘው ማህበር የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ያከበረ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በሰው ሃብት አመራር ላይ ያተኮረ ልዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያዘጋጃል ተብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ማታ በካፒታል ሆቴል በዓሉን ያከበረው ማህበሩ፤ባሳለፋቸው 10 ዓመታት በስኬት ስላጠናቀቃቸው ስራዎች ለማህበሩ አባላትና ለባለ ድርሻ አካላት ያብራራ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሰው ሀብት አመራር፣"የድርጅቶች አጋር" እየተባለ መጠራት መጀመሩ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተነግሯል፡፡  
 “ማንኛውም ስራ ውጤታማ የሚሆነው ያለንን የሰው ሀብት በአግባቡ ስንጠቀም ነው” ያሉት የብሪቲሽ ካውንስል የሰው ሀብትና ድርጅት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሚካኤል ሽፈራው፤በአገራችን ያሉ አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ያላቸውን የሰው ሀብት የማስተዳደር ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው ፣ማህበሩም የድርጅቶች አጋር በመሆን የሰው ሀብት አመራር እንዲሻሻል ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
ማህበሩ በዋናነት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል፤ወርሃዊ የሰው ሀብት አመራር ትስስር መድረክ ማዘጋጀት፣በሰው ሀብት አመራር ላይ ያተኮሩ ወርክሾፖችንና ስልጠናዎችን መስጠት፣የሥራ አውደ ርዕይ (Job fair) ማቅረብ፣ ጥናታዊ ፅሁፎችን ማሰናዳት፣የቀጣሪ ድርጅቶች ብራንዲንግና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ የስራ አውደ ርዕዮቹ ለበርካታ ቀጣሪና ተቀጣሪዎች፣ፊት ለፊት የመገናኘት እድል እንደፈጠሩላቸው የተናገሩት የፊኒክስ ቢዝነስ አማካሪና የማህበሩ የቦርድ አባል ወ/ሮ ነባት አባስ፤ማህበሩ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት 2018፣በአይነቱ ለየት ያለ ጉባኤ (“Human Capital Summit”) እንደሚያዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይም ከውጭ አገር የሚመጡ የሰው ሀብት አመራር ባለሙያዎች ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉና በሰው ሀብት አመራር ላይ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች እውቅና እንደሚሰጣቸው አክለው ገልጸል፡፡  
ማህበሩ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ፤ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰው ሀብት አያያዝ፣ የሰራተኛ ምልመላና ቅጥር ሁኔታ ለማሻሻልና የሰው ሀብት አመራር ሙያ እንደ ማንኛውም ሙያ እንዲከበር ለማስቻል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ 400 የዘርፉ ባለሙያዎችንና ከ50 በላይ ኩባንያዎችን በአባልነት ማቀፉም ታውቋል፡፡

Read 3365 times Last modified on Tuesday, 24 January 2017 14:05