Sunday, 22 January 2017 00:00

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች የመወያያ አጀንዳዎችን ያቀርባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       የውይይት መድረኮች በገለልተኛ አካል እንዲመሩ ተስማምተዋል
                               
     ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የቅድመ ውይይት ድርድር፤ ቀጣይ ውይይቶች እንዴት ይካሄዱ የሚለውን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለፀ ሲሆን ፓርቲዎች ለመወያየት የሚሹባቸውን አጀንዳዎች በ15 ቀን ውስጥ ለም/ቤቱ በፅሁፍ እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡
የውይይቱን መጀመር በመልካም ጎኑ እንደሚመለከቱት የገለፁት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳነት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ በዕለቱ በተደረገው ድርድር፤ በ4 መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናል ብለዋል፡፡ ከቀጣዩ መድረክ በኋላ ኢህአዴግ የውይይቱ ሰብሳቢ ሆኖ እንደማይቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ከውጭም ይሁን ከሀገር ውስጥ ገለልተኛ አካል ተፈልጎ በቀጣይ የሚደረጉ ውይይቶችን የሚመራ ይሆናል ብለዋል፡፡
ውይይቱን ገለልተኛ የሆነ አደራዳሪ እንዲመራው፣ ገለልተኛ ታዛቢ ከሀገር ውስጥም ከውጪም እንዲሳተፍ፣ ለሚዲያ የሚሰጥ መግለጫን በተመለከተ በክርክር ወቅት መድረኩ ለሁሉም ሚዲያዎች ክፍት እንዲሆን፣ ድርድር በሚደረግበት ወቅት ግን ፓርቲዎች ተወካያቸውን ብቻ እንዲልኩና ድርድሩ በሚያግባባ ጉዳይ ላይ ሲደርስ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት መስማማታቸውን ም/ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡ የውይይት መመሪያ ወይም የውስጥ ስምምነት መተዳደሪያ እንዲኖር መወሰኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በተካሄደው ድርድር ላይ ከኢቢሲና ከፋና ብሮድካስቲንግ በስተቀር ሌሎች መገናኛ ብዙኃን እንዳይገቡ መከልከሉን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ሙሉጌታ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያቸው መረጃ እንደሌለው ጠቁመው፣ እንዲ ዓይነት ነገር የሚደረግ ከሆነ ፓርቲያቸው በቀጣይ የራሱን ውሳኔ እንደሚወስን ተናግረዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በዕለቱ በተስማሙት መሰረት ግን ‹‹ዝግ ከሆነ ለሁሉም መገናኛ ብዙኃን ዝግ እንዲሆን፤ ክፍት ከሆነም ለሁሉም ክፍት እንዲሆን ወስነናል›› ብለዋል፡፡
በፓርቲዎች መካከል በዚህ መልኩ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ በ15 ቀናት ውስጥ እስከ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ እያንዳንዱ ፓርቲ ሊወያይባቸው የሚሻቸውን ሀገራዊ ጉዳዮችና የድርጅት አቋሙን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሃሳቡን በፅሁፍ እንዲያስገባ መወሰኑንም አቶ ሙሉጌታ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ለአንድ ጊዜ ብቻ ፓርቲዎችን  ለውይይት የመጥራት እድል የተሰጠው ሲሆን በቀጣዩ መድረክም ወደፊት የሚደረጉ ውይይቶችን የሚመሩ ገለልተኛ አካላት ይመረጣሉ መባሉን ተናግረዋል፡፡
የመድረኩ መሪ የነበሩት የኢህአዴግ ተወካዮች፣ ‹‹ለሚዲያ መግለጫ ስትሰጡ አብረን ለመስራት እንደተስማማን ግለፁ ብለውን ነበር” ያሉት አቶ ሙሉጌታ፤ “ግን አብረን ለመስራት ሳይሆን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ነው የተስማማነው፤ ሚዲያዎችም በዚህ አግባብ ነው ጉዳዩን ሊመለከቱት የሚገባው” የሚል ማሳሰቢያ ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል፡፡ “ከኢህአዴግ ጋር የተስማማነው በፖሊሲ፣ በህገ መንግስትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመደራደርና ለመከራከር እንጂ አብረን ለመስራት እንዳልሆነ በደንብ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል - አቶ ሙሉጌታ፡፡
እስከ የሻይ ዕረፍት ሰአት ድረስ በውይይቱ ላይ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው መሳተፋቸውን የገለፁት የፓርቲው አመራር አቶ ስለሺ ፈይሳ፤ ኢህአዴግ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡  ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ብቻ እወያያለሁ ቢልም ነፍጥ ካነገቡ ኃይሎች ጋር ሳይቀር መወያየት እንደሚገባ ሀሳብ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
‹‹የተጀመረውን የውይይትና የድርድር መድረክ ኢህአዴግ ለፕሮፓጋንዳ ብቻ የሚጠቀምበት ከሆነ ፓርቲያቸው ውይይቱን አቋርጦ ሊወጣ እንደሚችል አሳስበናል›› ያሉት አመራሩ፤  ውይይት  አሳታፊነቱ ያልተገደበ መሆን እንዳለበት መግለፃቸውን ተናግረዋል፡፡
ለፓርቲያቸው የውይይት ጥሪ በደብዳቤ  በቀረበለት መሰረት፣ በውይይቱ ላይ መገኘታቸውን የገለፁት ‹አዲሱ የፓርቲው መሪ› አቶ የሸዋስ አሰፋ በበኩላቸው፤ በታዛቢዎች አመራረጥ፣ በመድረክ አመራርና በፕሬስ መግለጫ ዙሪያ ከስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ በ15 ቀን ውስጥ በውይይቱ እንዲነሱ የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች በተመለከተ ፓርቲያቸው ያለውን ሀሳብ እንደሚያቀርብም አቶ የሸዋስ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡

Read 966 times