Tuesday, 24 January 2017 14:15

በተቃውሞ የታጀበው የትራምፕ በዓለ ሲመት

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  90 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል

        አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ከእልህ አስጨራሽ ፉክክርና የቃላት ፍልሚያ፣ ከብዙ ትችትና ውዝግብ፣ ከብዙ አስደንጋጭና አነጋጋሪ ክስተቶች እንዲሁም አለምን ካስደነገጠ ያልተጠበቀ ድል በኋላ፣ በትናንትናው ዕለት ልዕለ ሃያሏ አገር ሊመሩ፤ ቃለ - መሃላ ፈጽመው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደውን የትራምፕ በዓለ ሲመት በተመለከተ የአለማችን የመገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች ያገኘናቸውን መረጃዎች እነሆ!
የጸጥታ ስጋት
በዓለ-ሲመቱ በሽብርተኞችና ሁከት ፈጣሪዎች እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ጥብቅ ፍተሻና የደህንነት ጥበቃ ተደርጓል፡፡ ከ28 ሺህ በላይ የጸጥታ ሃይሎች በተጠንቀቅ ቆመው በዓሉን ከስጋት ለመታደግ ሲሰሩ ውለው አድረዋል፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚከናወኑባቸው ስፍራዎችም በረዥም መከላከያ አጥሮች ተከልለው ነበር፡፡
በበዓለ-ሲመቱ ላይ የሚቀርቡ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚታደሙ እንግዶች እስከ ስድስት ጊዜ ያህል ፍተሻ እንደተደረገባቸውና ታዳሚዎችም 40 ያህል የተለያዩ ቁሳቁሶችን በዝግጅቶቹ ላይ ይዘው እንዳይገኙ መከልከላቸው ተነግሯል፡፡
ታዳሚ እና ቀሪ
በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ቁጥር 900 ሺህ እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን ይህ ቁጥር ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዓለ-ሲመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ተብሏል። በ2009 በተከናወነው የኦባማ በዓለ-ሲመት ላይ 1.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መታደማቸውን ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡
ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽና ጂሚ ካርተር ሁሉም ከነባለቤቶቻቸው በዓለ-ሲመቱን ታድመዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ፣ ከ60 በላይ የሚሆኑ የዲሞክራት ፓርቲ አባላት በበዓለ ሲመቱ ላይ እንደማይገኙ ባስታወቁት መሰረት፣ ሳይገኙ መቅረታቸው ተዘግቧል፡፡
በድጋፍ እና በተቃውሞ የታጀበው በዓል
ይህንን በዓለ-ሲመት ለየት የሚያደርገው በትራምፕ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሰልፍ መታጀቡ ነው፡፡ በትራምፕ በዓለ-ሲመት ላይ ሊደረጉ የታቀዱ የተቃውሞ ሰልፎች ብዛት፣ በቅርብ ጊዜ የአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው እንደሆነ ተነግሯል። በዋሽንግተንና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ከበዓለ-ሲመቱ ጋር በተያያዘ ሊካሄዱ ለታቀዱ 30 ያህል የተቃውሞ ሰልፎች ህጋዊ እውቅና መሰጠቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉም የተቃውሞ ሰልፎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሴቶች የሚያስተባብሩትና 200 ሺህ ያህል የትራምፕ ተቃዋሚዎች ይሳተፉበታል የተባለውና ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የተቃውሞ ሰልፍ ነው፡፡ አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ የገጠማቸው በአገራቸው ብቻም አይደለም፡፡ ተቃውሞው ወደ እንግሊዝም የዘለቀ ሲሆን ትናንት በለንደን የተለያዩ አካባቢዎች ትራምፕን የሚቃወሙ መፈክሮች ተሰራጭተዋል። ሲሆን ከ20 በላይ በሚደርሱ የተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞችና በአውስትራሊያ ሲድኒ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡
በፊሊፒንስ የተካሄደው ተቃውሞ ግን ከሁሉም ይብሳል፡፡ ትናንት በማኒላ ትራምፕን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ፊሊፒንሳውያን፤ የአሜሪካን ሰንደቅ አላማ በአደባባይ አቃጥለዋል፡፡
ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?
ለትራምፕ በዓለ-ሲመት በድምሩ 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የበዓለ-ሲመት ወጪ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
ብዙዎች ያልታደሙት የሙዚቃ ድግስ
የበዓለ ሲመቱ አካል ከነበሩት ዝግጅቶች መካከል ታዋቂ ድምጻውያን የተሳተፉበትና የሙዚቃ ዝግጅት አንዱ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ  በተካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት 10 ሺህ ያህል ተመልካቾች የታደሙ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከኦባማ የበዓለ ሲመት የሙዚቃ ታዳሚዎች አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡ በኦባማ የበዓለ-ሲመት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የተገኙ ተመልካቾች ቁጥር 400 ሺህ ያህል እንደነበር ተነግሯል፡፡
በዚህ በዓለ ሲመት ላይ የ16 አመቷ ታዳጊ ድምጻዊት ጃኪ ኢቫንቾ፤ የአሜሪካን የህዝብ መዝሙር ያቀረበች ሲሆን ድምፃውያኑ ቶቢ ኬዝ፣ ላሪ ስቴዋርትና ሪቼ ማክዶናልድም በዓሉን በሙዚቃ ስራዎቻቸው ካደመቁት ታዋቂ ድምጻውያን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ካዲላክ ዋን
ትራምፕ ወደ በዓለ-ሲመቱ ያቀኑት እጅግ ዘመናዊና ውድ በሆነቺው አዲሷ ካዲላክ ዋን መኪናቸው ነው፡፡ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የወጣባት ይህቺው መኪና፤ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመቋቋም እንድትችል ተደርጋ የተሰራች ሲሆን፣ ጥቃት ሊሰነዝርባት በሞከረ ወገን ላይ አፋጣኝ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ተጠቁሟል፡፡

Read 5148 times