Sunday, 22 January 2017 00:00

ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ ውይይት!!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ተቃዋሚዎች ከመንግስት ጋር ምን ለመደራደር ይሻሉ?
                    “ሀሳቦች አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው”
     በሀገሪቱ የተፈጠሩ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ አንጋፋዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የድርድርና ውይይት መድረክ እንዲዘጋጅላቸው በተደጋጋሚ መወትወታቸው አይዘነጋም፡፡ የመጀመሪያው የድርድርና የውይይት መድረክም ባለፈው ረቡዕ በፓርላማ ተካሂዷል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውይይቶቹና ድርድሮቹ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚውሉና የይስሙላ እንዳይሆኑ ስጋት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ በመድረኩ መዘጋጀት ደስተኞች ናቸው። ውይይቱ በታቀደው መሰረት በተከታታይ የሚቀጥል ከሆነ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ የውይይት አጀንዳዎቹን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ/መንግስት ጋር መወያየት የሚሹት ምንድን ነው?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በዚህ ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን መሪዎች ሃሳብና አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው
ተጠናቅሯል፡፡

                    “እኛ የምንፈልገው ውይይት ሳይሆን ድርድር ነው”
                            ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀመንበር)
    
     እኛ የምንፈልገው ውይይት ሳይሆን ድርድር ነው፡፡ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ መደራደር ነው የምንፈልገው፡፡ ለውይይት የሚሆን የመድረክ
አደረጃጀትም እያየን አይደለም፡፡ እኛ መሰረታዊ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ነው ከኢህአዴግ ጋር መደራደር የምንሻው፡፡ አሁን ውይይት የሚሉት
ከፖለቲካ ምህዳሩ ድርድር በኋላ ሊመጣ የሚችል ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን እፈልጋለን፡፡ ይህ ማለት ነፃ የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ አለ፡፡ የሲቪል ማህበረሰቡ ጉዳይ አለ፡፡ ህጎች የመሻርና የመከለስ፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ --- ጉዳዮች ላይ በሙሉ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ የምርጫ ስርአቱና አፈፃፀሙ እንዲታይና ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣበት እንፈልጋለን፡፡ እኛ ስትራቴጂክ ግባችን በሃገሪቱ እነዚህ ሁሉ እንዲሰፍኑ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ድርድሩ በእውነተኛ መንገድ የሚካሄድ ከሆነ፣ እነዚህን ውጤቶች ይዞ እንዲመጣ
እንፈልጋለን፡፡

------------------

                      “የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዴግ አቅም በላይ ነው”
                               ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

      ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል እጅግ ምስቅልቅሉ የወጣ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በመንግስት አቅም ማስተዳደር ባለመቻሉም፣ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ነች ተብሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሞተዋል፤ በ10 ሺዎች የሚገመቱ ታስረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች ይገኙበታል፡፡
በህዝቡ ሰላማዊ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ሲጠየቁ የነበሩትም፣ ከኢህአዴግ አቅም በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ እኛም የምንጠይቀው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ነው። “አሁን ያለው የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዴግ አቅም በላይ ነው” የሚል ሃሳብ ይዘን ነው የምንቀርበው። ስለዚህ ምን ይሁን ከተባለ ደግሞ የተለያዩ አካላት የየራሳቸውን የመፍትሄ አቅጣጫ ይዘው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡
የሽግግር መንግስት ሊሆን ይችላል፣ ስልጣን መጋራት ሊሆን ይችላል፣ አስቸኳይ ምርጫ ማድረግ ሊሆን ይችላል፣ የህገ መንግስት ማሻሻል ማድረግ ሊሆን ይችላል። እነዚህንና መሰል መፍትሄዎችን ተሳታፊዎች ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡
እኔ ከእነዚህ ድርድሮች የምጠብቀው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ፍንጭ ማየት ነው፡፡
ከዚያ ውጪ የማስመሰል ወይም ስልጣንን በዘዴ የማጠንከር፣ አሊያም ለአለማቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ለተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች የተለየ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚደረግ ነገር ከሆነ፣ ህዝብን ለማታለል እኛም መጨመር የለብንም። ስለዚህ ከምር  የኢትዮጵያን ህዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ወደፊት የሚያራምድ፤ ተስፋውን የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ጭምር መሆን አለበት፡፡
በእኔ እምነት ግን ኢህአዴግ አሁን፤ ”ስልጣኑን ተቆጣጥሬያለሁ፤ ሁሉም በኔ ስር ነው” በሚል የራሱን የበላይነት ለማሳየት የሚያደርገው ነው የሚመስለኝ። ኢህአዴግ በአገሪቱ ችግሮች ላይ በግልፅ ተወያይቶ፣ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ወደፊት ሊያራምድ ይችላል ወይ በሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡

---------------

                       “መጀመርያ በቅድመ ውይይት ጉዳይ ላይ መግባባት አለብን”
                                    አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት)

       የድርድርና የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ሲጠይቁ ከነበሩ ፓርቲዎች አንዱ መኢአድ ነው፡፡  መድረኩ የድርድርም ይሁን የውይይት መዘጋጀቱ በራሱ መልካም ነው፡፡ ፓርቲያችን ሀገራዊ የውይይት አጀንዳዎች ብሎ ያስቀመጣቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይሄን አሁን በዝርዝር አንገልጸውም፤ ሂደቱን እያየን ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡ በመጀመርያ ግን ዘላቂ ድርድርና ውይይት ለማድረግ በቅድመ ውይይት ጉዳይ ላይ መግባባት አለብን፡፡
ከውይይቱ ወይም ድርድሮቹ ቢገኙ ብለን ከምንመኛቸው ውጤቶች መካከል፣ ሁሉም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ወደ ሰላም መድረክ የሚመጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው፡፡  
ለዚህ ሀገር ይሆናል ብለን ባሰብነው መጠን ሰርተን የምናልፍበት እድል ቢመቻችም ምኞታችን ነው፡፡

------------------

                  “በፌደራሊዝም አወቃቀሩ ላይ መደራደር እንፈልጋለን”
                           ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

       ከዚህ ቀደም ጠ/ሚኒስትሩ የጋራ ም/ቤት አባል ፓርቲዎችን ሰብስበው ቃል በገቡት መሰረት፣ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ መልካም ነው። የህግ አወጣጥ አፈፃፀም ችግሮችን በተመለከተ፣ የማያሰሩና ችግር ያለባቸው እየተባሉ በኢህአዴግም በኩል የሚገለፁ የፖለቲካ አቅጣጫዎች አሉ። እዚህ ላይ ሰፊ መግባባት የሚደረስበት ውይይት እንዲካሄድ እንሻለን፡፡ አሁንም ትልቁ የዲሞክራሲያዊ ሂደት ግዙፍ ተቋም ነው ተብሎ የሚታወቀው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ይህ ምርጫ ቦርድ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በሰጡት አቅጣጫና ጠ/ሚኒስትሩም ለወደፊት በውይይት የምናዳብረው ይሆናል ብለው ቃል በገቡት መሰረት፣ እየጠየቅናቸው ያሉት የምርጫ ህግ ክፍተቶች የሚሟሉበት ሁኔታ በዚህ ውይይት መፈጠር አለበት፡፡ የምርጫ ቦርድ አወቃቀርና የምርጫ ስርአቱ የሚሻሻልበት መንገድ መፈጠር ስላለበት፣ አንዱ የድርድር አጀንዳ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡
ሚዲያን በተመለከተ፣ በአሁን ወቅት የግል ሚዲያዎች በፍርሃት ራሳቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ሣንሱር እያደረጉ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ የሚፈልገውን መረጃ የመስጠትና የመቀበል ህገ መንግስታዊ መብቱ እየተጣሰ ነው። በዚህም ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት እንዲደረግ እንፈልጋለን፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣንም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉ ህጎችን እንደገና የሚፈትሹበት ሁኔታ እንዲፈጠርና ሚዲያዎች የሁሉም ድምፅ መድረኮች እንዲሆኑ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መነጋገር አለብን፡፡
ሌላው ሀገሪቱ አሁን የምትተዳደርበት ስርአትና የክልል አወቃቀሮች ሂደት የፌዴራሊዝም እውነተኛ ገፅታ የያዙ ባለመሆኑ፣ ፌደራሊዝሙ ምን መምሰል እንዳለበት መወያየት አለብን፡፡ ራሱን የቻለ የህገ መንግስት ድንጋጌዎች እንዳሉ ሆነው፣ የክልል ቅራኔ እያመጡ ያሉ የድንበር አከላሎች በሙሉ ሊፈቱበት የሚችል፣ አንድ ወጥ የሆነ መላ ሊዘየድ ይገባል። እውነተኛና ሊያሰራ የሚችል ፌደራሊዝም መዋቀር እንዳለበት፣ ከፕሮግራማችንም ተነስተን ማብራሪያ እንሰጥበታለን፡፡ በሌላ በኩል ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ያስፈልገናል ብለን እናምናለን። የዚህም ሂደት ምን መሆን እንዳለበት መደራደር እንፈልጋለን። መንግስት በቁርጠኝነት ስለ እውነት ብሎ የሚሰራ ከሆነ፣ የተለያዩ ቅራኔ የፈጠሩ አካሎች ስላሉ፣ ብሄራዊ እርቁ መሬት ላይ ወርዶ የምናይበት ሁኔታ እንደሚፈጠር እናምናለን፡፡ ስለዚህ እርቅ መደረግ አለበት የሚለው አንዱ የድርድር አጀንዳችን ነው፡፡ በተረፈ ውይይቱና ድርድሩ በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲካሄድ እንፈልጋለን። ህዝቡ ከዚህ ድርድርና ውይይት ምን ይጠብቃል የሚለው አሳሳቢ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይም ህዝቡ በተሳታፊነት ጉዳዮቹን በዝርዝር ማወቅ አለበት። የተቃዋሞ ጎራው በራሱ አንድ እንደ ም/ቤት ያለ አካል መስርቶ፣ ህዝብን ማንቃት ይኖርበታል። የራሱን አቅጣጫዎች ጥርት አድርጎ ይዞ መቅረብ ስላለበትም፣ ይሄን የተቃውሞ ጎራው ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡
ከድርድሩና ውይይቱ የምንጠብቀው ውጤት የዴሞክራሲ ተቋማትን መጎልበት፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ማገልገልን ነው፡፡ ህብረተሰቡም ሆነ መንግስት አሊያም የተቃውሞው ጎራ ከፅንፈኝነት አመለካከት ይልቅ የሠከነ ውይይት አድርጎ፣ ስልጣን በሠላም የሚሸጋገርበትን መንገድ መፍጠር ለሃገሪቱ ትልቅ ጥቅም ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ እኛ ከዚህ ድርድር እንዲመጣ የምንፈልገው፣ ህብረተሰቡን በነፃነትና ገለልተኝነት የሚያገለግሉ የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት እንዲፈጠሩ ነው፡፡

Read 1292 times