Sunday, 22 January 2017 00:00

በመቃብር አፋፍ ያለው የህዝብ ሃብት

Written by  አክሊሉ ከአ.አ.ዩ
Rate this item
(0 votes)

 ከጥቂት ወራት በፊት ለተከበሩ ሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ መታሰቢያነት የተሠራው ሃውልት ከተመረቀ ማግስት ጀምሮ፣ የብዙዎቻችን ጉጉት የነበረው የጋራ ውርሳችን፣ “ቪላ አልፋ” ዕውን ሆኖ፣ የሎሬትን ዘላለማዊነት ለትውልድ ሲዘክር ማየት ነበር፡፡ ይህ ጥልቅ  ምኞት የሎሬት አፈወርቅም  የነፍሱ ናፍቆት እንደነበረ ማሳያው፣ ከህመም አልጋው ላይ ተነስቶ  ያደረገው አኩሪ ተግባር ነው፡፡
ሎሬት አፈወርቅ ከህልፈተ ሞቱ በፊት የገደደውና ያሳሰበው በመቃብሩ ላይ የሚተከለው የመታሰቢያ ሃውልቱ ጉዳይም አልነበረም፡፡ ይልቁንስ የሎሬት ዘላለማዊ ምኞት፣ የህይወት ዘመን ትሩፋቱን፤ የጥበብ አሻራውን፤ የልጅነት ህልሙና ብቸኛ ልጁን ለሚያከብረውና ለሚወደው ህዝብ አውርሶ ሩጫውን ማጠናቀቅ ነበር፡፡
የሚያሳዝነውና የሚያስቆጨው፣ ዛሬም የህዝብና የመንግስት ያለህ የሚያሰኘው፣ የሁላችን ጉጉት የነበረውና የሎሬትን ዘላለማዊነት ለትውልድ ሲዘክር ይኖራል ብለን የጠበቅነው “ቪላ አልፋ”፤  ከመቃብር አፋፍ መገኘቱን፣ ሃገርና መንግስት አለማወቃቸው ነው፡፡ ለመሆኑ በየሩብና በየመንፈቀ ዓመቱ በሚቀርበው ሪፖርት ላይ፣ የዚህ ትልቅ ተቋም ጉዳይ አለመነሳቱን አስተውሎ ወይም ጠይቆ የሚያውቅ የባህል ዘርፍ ባለስልጣን አለ?
ለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት፣ "ቪላ አልፋ" የያዘው የሃብት መጠን ምን ያህል ነው ብለው ይገምታሉ? ይህን ለማወቅ የሚመለከተው አካል ለህግ ውሳኔ ያቀረበውን ሰነድ ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ "ቪላ አልፋ" በዓይነቱ የተለየና ብቸኛ የሥነጥበብ ማዕከል ሆኖ፣ በሃገሪቱ ውስጥ ለማገልገል ከበቂ በላይ የተለያዩ የሥነ ጥበብ ውጤቶች፤ የተሟላ የሪፍረንስ ላይብረሪና ኦዶቪዠዋል ብሎም የምርምር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጥንስሶች ያሉበት ተቋም እንደ ነበረ መመስከር ይቻላል፡፡ የዛሬን አያድርገውና፡፡ የጎበኙትና ስለ ማዕከሉ በቂ መረጃ ያላቸው ምሁራን ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
ዳሩ ግን የነበረው እንዳልነበረ በመሆን ላይ ነው፡፡ ለመሆኑ የሥነጥበብ ውጤቶቹ አይደለም በዓመታት በጥቂት ወራት ውስጥ በቅዝቃዜና በእርጥበት ውበታቸው እንደሚረግፍ ለመገንዘብ የግድ ሰዓሊ መሆን ያሻ ይሆን? የቤቱ ጣሪያ ማፍሰስ ከጀመረ ቆይቷል የሚሉ የዐይን ምስክሮች፤ ጥያቄው ሰሚ ያጣ ጩኸት መሆኑን በምሬት ይናገራሉ፡፡  
ለመሆኑ ባላደራ ነው ተብሎ የተረከበው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኘው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ስለ "ቪላ አልፋ" ምን ይሉ ይሆን? ለዚህች ድሃ ሃገር ይሄን ትልቅ የሥነ-ጥበብ ቅርስ በከንቱ ማጣት፣ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው። ከሁሉም በላይ የታላቁን ሎሬት ታሪክ ለአዲሱ ትውልድ እንዳይተላለፍ ማድረግ አሳዛኝ ታሪክ ነው የሚሆነው፡፡    
በመጨረሻ፡- ባላደራዎቹ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ ከሆነ ሊሰራ ለሚችል፣ የሙያው ባለቤት ለሆነና ባላደራነት ለሚሰማው መሰል ተቋም የማይሰጥበት ምክንያት ምንድን ነው?                     

Read 1545 times