Sunday, 22 January 2017 00:00

የቱ ይሻላል - ሹመት ወይስ ሽረት?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ምን ይላል?  
    
- ከኃላፊነት የሚነሱ የመንግስት ባለስልጣናት የመቋቋሚያ አበል፣ የስራ ስንብት ክፍያ፣ የቤት አበልና የተሽከርካሪ አገልግሎት ይሰጣቸዋል
- ከኃላፊነት የተነሳ የመንግስት የስራ ኃላፊ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ተሽከርካሪውን ጨምሮ ሊያገኝ የሚገባው ጥቅማ ጥቅም ለቤተሰቦቹ ይሰጣል
- ለተሿሚ የስራ ኃላፊዎች የሚሰጠው ጥቅማጥቅም፣ከኃላፊነት ለሚነሱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ተግባራዊ ይደረጋል
                     
         በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው የሚነሱ የሀገርና የመንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሚያገኙዋቸውን ጥቅማ ጥቅሞች ለመወሰን የሚያስችልና የቀድሞውን አዋጅ የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያመለክተው፤ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የህዝብ ተመራጮችና ዳኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ የተለያዩ ጥቅሞችና መብቶችን እንዲያገኙ ማድረግ በሌሎች አገራት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ስርዓቱ በአገሪቱ መዘርጋቱና በየጊዜው እንደ ሁኔታው እየተሻሻለ መሄዱ ለአገሪቱም ሆነ ለባለስልጣናቱ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን ማውጣቱ አስፈላጊነቱ ታምኖበታል፡፡ አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ተጨማሪ ወጪዎችን ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑን የገለፀው ረቂቅ አዋጁ፤ወጪውን ግን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የሚወጣ በመሆኑ መከፈል የሚገባውና መከፈል ያለበት ወጪ ነው ብሏል፡፡
በነባሩ አዋጁ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል የመቋቋሚያ አበል፣የስራ ስንብት ክፍያ፣ የቤት አበል ክፍያና የተሽከርካሪ አገልግሎት ይገኙባቸዋል፡፡  
የመቋቋሚያ አበልን በተመለከተ ከኃላፊነት ለተነሱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ከኃላፊነት ለተነሱ የምክር ቤት አባላት የሚከፈለው የመቋቋሚያ አበል ክፍያ ላይ ለአንድ ዓመት አገልግሎት የስድስት ወር ደመወዝ ሆኖ፣ ከዚያ በላይ አገልግሎት ለሰጡ ኃላፊዎች ደግሞ በእያንዳንዱ የአገልግሎት ዓመት የአንድ ወር ደመወዝ እየታከለ እንዲታሰብና አጠቃላይ የመቋቋሚያ አበል ጣሪያ ክፍያው ከ18 ወራት ወደ ሃያ ወራት ደመወዝ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የስንብት ክፍያን በተመለከተም ለአንድ ዓመት አገልግሎት፣የስድስት ወር ደመወዝ እንዲሆንና ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ አገልግሎትም የመጨረሻ ወር ደመወዙ አንድ ሁለተኛ እየታከለ እንዲታሰብ ተደርጓል፡፡ አንድ የምርጫ ዘመንን አገልግሎ ከኃላፊነት የተነሳ ወይም አንድ የምርጫ ዘመንን ግማሽ ያገለገለና በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነት የተነሳ የሥራ ኃላፊ እንደየስልጣን ተዋረዱ ከዘጠኝ ወራት መሉ ክፍያ እስከ አራት ወራት ሙሉ ክፍያ ይከፈለዋል ይላል - ረቂቅ አዋጁ፡፡  
ማንኛውም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ቢያንስ ሁለት የምርጫ ዘመን አገልግሎ ከኃላፊነት ከተነሳ ወይም አንድ የምርጫ ዘመን ከግማሽ አገልግሎ በህመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ፣ ለራሱና ለቤተሰቡ መኖሪያነት የሚያገለግል ራሱ ኪራይ የሚከፍልበት የመኖሪያ ቤት እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ የቤቱ ደረጃም እንደስራ ኃላፊው የስልጣን ተዋረድ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ከኃላፊነት ለሚነሱ ሚኒስትሮች፣አፈ-ጉባኤዎች፣ የመንግስት ተጠሪዎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በእኩል ደረጃ ተፈፃሚ እንደሚሆንም አዋጁ ይገልጻል፡፡  
ሁለት የምርጫ ዘመንን አገልግሎ ከኃላፊነት የተነሳ ወይም አንድ የምርጫ ዘመን ከግማሽ አገልግሎ በህመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ በሌላ ምክንያት ከኃላፊነት የተነሳ ሚኒስትር፤አንድ የቤት አውቶሞቢል እንዲመደብለት ይደረግና ለሚመደበው የቤት አውቶሞቢል የሾፌር ደመወዝ፣ የነዳጅ፣ የጥገና እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች በመንግስት ይሸፈናሉ፡፡ ከሚኒስትር በታች ለሆኑ የሥራ ኃላፊዎችም እንደየአገልግሎት ዘመናቸው ከዘጠኝ ወራት የተሽከርካሪ አበል ክፍያ እስከ ስድስት ወራት ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚደረግ ሲሆን የሚሰጣቸው የተሽከርካሪ አበል ጠቅላላ ክፍያ ከ18 ወራት ወደ 24 ወራት ከፍ እንዲልና ከመኖሪያ ቤት አበል ጣሪያ እንዳይበልጥ ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡
ማንኛውም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ቢያንስ ሁለት የምርጫ ዘመን አገልግሎ ከኃላፊነት ከተነሳ ወይም አንድ የምርጫ ዘመን ከግማሽ አገልግሎ በህመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ፣ በራሱ ወይም በባለቤቱ ስም የተመዘገበ መኖሪያ ቤት ከሌለው፣ራሱ ኪራይ እየከፈለ የሚገለገልበት የመኖሪያ ቤት እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ ከኃላፊነት ለተነሱ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የተፈቀደው የቤት አበል ወይም የመኖሪያ ቤት አገልግሎት ከኃላፊነት ለተነሱ አፈጉባኤዎች፣ የመንግስት ዋና ተጠሪዎችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ተፈፃሚ ይደረጋል፡፡
ማንኛውም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ፤ከኃላፊነት ተነስቶ ጥቅሞቹን ከማግኘቱ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ሊከፈለው ይገባ የነበረው የመቋቋሚያ አበል፣ የስራ ስንብት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤት አበል ወይም የመኖሪያ ቤት አገልግሎትና የተሽከርካሪ አበል ወይም የተሽከርካሪ አገልግሎት ለቤተሰቦቹ እንዲሰጥ ይደረጋል ይላል - አዋጁ፡፡ የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ ተደርጓል፡፡

Read 1313 times