Sunday, 22 January 2017 00:00

ከማርሽ ቀያሪው ምን እንማራለን?

Written by  በክብሮም በርሀ ዘቢብ
Rate this item
(0 votes)

  “የምሩፅ አልፋና ኦሜጋው ኢትዮጵያዊነት ነው”
                            
      ምሩፅ የተወለደው በትግራይ ክልል ዓዲግራት አካባቢ ጉሎምኻዳ ወረዳ ነው፡፡ ልክ እንደ ዓድዋ፣ የሶማልያውና የማህዲስት ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በጋራ ደማቸው ታሪክ ከፃፉባቸው የአንድነት ሀውልቶች አንዱ የሚገኘው ምሩፅ በተወለደበት አካባቢ ነው፡፡ ሻዕብያ  ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ከሁሉም አቅጣጫ ተሰባስበው እምቢ ለባንዲራችን በማለት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታቸው ያስመሰከሩበት ቦታ ነው፤ ጉሎምኻዳ ማለት፡፡ እንደሚታወሰው ሻዕብያ ኢትዮጵያን ከወረረበት አንዱ ምክንያት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ካለመረዳት ነው፡፡ በጊዜው የነበረው የሻዕብያ እምነት፣ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ መቆም አይችሉም፣ በውስጣዊ ልዩነት፣ በብሄርና በሀይማኖት ይከፋፈላሉ የሚል እንደነበር ይነገራል፡፡ ሻዕብያ የያኔው ግምቱ ከሽፎ የተገላቢጦሽ መሆኑ የተረዳ ቢሆንም፣ የውስጥ ልዩነትን ተጠቅሞ የተበታተነችና ደካማ ኢትዮጵያ ለመፍጠር አሁንም 24 ሰዓት እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡
የአበበ ቢቂላ ልጅ፣ የማሞ ወልዴ፣ የኃይሌ       ገ/ስላሴ፣ የቀነኒሳ፣ የጥሩነሽ፣ የወርቅነሽ፣ የአልማዝ፣ የመሰረት አባት የሆነው ምሩፅ፤ ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም መድረክ ያውለበለበ ጀግና ነው፡፡ የምሩፅ አልፋና ኦሜጋው ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነትን በዓለም መድረክ እንዲታወቅ ካደረጉ የአትሌቲክስ ፈርጦች አንዱ ማን ነው ቢባል፣ ምሩፅና የሙያ ቤተሰቡ እንደሆኑ ግልፅ ነው። አንድ ጀርመናዊ፤ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ከምትለው፣ ”የገብረስላሴ ሀገር ልጅ ነኝ” ብትለው የተሻለ ይረዳሃል ይባላል፤ በቀልድ፡፡ በኛም ሀገር ስንመጣ፣ ከሮናልዶ ሀገር ይልቅ ሮናልዶን የሚያውቅ፣ ጃማይካን ከሚያውቅ ቦልትን የሚያደንቅ በእጅጉ እንደሚልቅ ይገመታል፡፡ ምሩፅ ማለት ታዲያ የኛ ሮናልዶ ወይም ቦልት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
“የነፃነትና የስልጣን ይበቃኛል” ተምሳሌቱ ኔልሰን ማንዴላ፤ ስፖርት አንድ የማድረግ ሀይል እንዳለው መናገራቸው ይታወቃል፡፡ በኛም ዘንድ ሁላችንንም አንድ ከሚያደርጉን ምክንያቶች ስፖርት፣ ከስፖርትም አትሌቲክስ ዋነኛው ነው፡፡ በጋለ የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ሆነን እንኳ የአልማዝ አያና ልዩ ብቃት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ልዩ ደስታ የመፍጠር ጉልበት እንደነበረው በጉልህ ታይቷል፡፡ በድምሩ፣ ከትናንት እስከ ዛሬ የነበሩና ያሉ አትሌቶቻችን፣ ልዩነትን የሚያስውቡ፤ የአንድነት ካስማዎች መሆናቸው ልዩ ስጦታችን ሆኖ ዘልቋል፡፡
ምሩፅ የፅናት ተምሳሌት ነው፡፡ የሰው ልጅ ከጋሪ ገፊነትና ከፋብሪካ ሰራተኝነት ተነስቶ የዓለም ተምሳሌትነት ወደ መሆን መሸጋገር እንደሚችል ምሩፅ አንድ አብነት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ያሉበትን ደረጃ በማየት ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ አይረዱም፡፡ ከትንሽ መጀመር ማለት ትልቅ ቦታ አለመድረስ የሚመስለው ካለ፣ ከምሩፅ ቢማር ይጠቀማል። በየትኛውም የስራ ዘርፍ ያለውና የሚኖረው መሰናክልና ፈተና፣ ጥንካሬ መሆኑን የማይረዳ ካለ፣ ምሩፅን አርአያ ማድረግ ይችላል። ምሩፅ ከእነ አበበ ቢቂላና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ጋር በአስመራ ከተማ የማራቶን ውድድር ላይ ሮጦ፣ መጨረሻ እንደወጣ አዲስ ልሳን ጋዜጣ አስነብባናለች፡፡ ታድያ ከዚህ መማር የሚቻለው ጠንክሮ ለሰራ ሰው፣ ዛሬ መጨረሻ ቢወጣም ነገ ሌላ ታሪክ መስራት እንደሚችል ነው። በጊዜው መጨረሻ መውጣቱን የተመለከተ ሰው፣ የምሩፅን ማንነት ላይረዳ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን፣ ራሱንና እምቅ ችሎታውን የተረዳው ምሩፅ፤ መክሊቱን ፍለጋ ከመኳተን አልቦዘነም፡፡ ህልሙን ለማሳካት እንቅልፍ ያልነበረው ምሩፅ፤ ከመጨረሻው ደረጃ ተነስቶ አንደኛ ለመሆንና ዓለምን ለማስደመም ጊዜ አልፈጀበትም። ፅናት የስኬት ሚስጥር መሆኑን፣ ከምሩፅና መሰል ጀግኖች መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
ጠፈር ከሄደው ይልቅ ጠፈር እንዲሄድ ያደረገው ይሻላል የሚባል ነገር ትክክል ነው፡፡ ከምሩፅ ይልቅ ለአትሌቲክሱ ፈር ቀዳጅ የሆነው አስተማሪው አበበ ቢቂላ የሚደነቅ ነው፡፡ አበበ ቢቂላ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁሮች በሞላ “ይቻላልን” ማስተማሩ ዓለም ያውቃል፡፡ ሻምበል ጉዲና ጎቲና ሌሎች በውል የማናውቃቸው የምሩፅ መምህራንና አሰልጣኞችም ሊደነቁ ይገባል፡፡ እንደ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ገለፃ፣ በጊዜው የአየር ሀይል አሰልጣኝ የነበሩት ሻምበል ጉዲና ጎቲ፣ ምሩፅ የነገ የሀገር ተስፋ እንደሚሆን በመገንዘብ፣ ለድል ማብቃታቸው ትልቁ ነጥብ ነው፡፡ ምናልባት ሻምበሉ ዛሬ ዛሬ እንደሚሰማው፣ ከምሩፅ ጉቦ ቢጤ ቢፈልጉ ኖሮ፣ ምሩፅ ወደ ጋሪ ገፊነቱ መመለሱ አይቀርም ነበር፡፡ በጉቦና በመሰል የሙስና ድርጊቶች ራዕይን የሚያጨናግፉ የአትሌቲክስ አመራሮች መኖራቸው ሲታወቅ፣ ምሩፅም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ቢገጥመው ምን እንደሚሆን ለመገመት ያስቸግራል፡፡  
ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን ለሀገሬ ምን አደረግኩኝ ማለት ጠቃሚ እንደሆነ አስረግጠው የተናገሩት ጆኔፍ ኬኔዲ የተባሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ሀገራችን የምታደርግልን፣ እኛ ስናደርግላት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ምሩፅ ከእንግልት እስከ እስር የደረሰ በደል ቢፈፀምበትም ለሀገሩ መትጋቱን አላቆመም። ምሩፅ እስከ ዕለተ ሞቱ የሰራውን ያህል ባያገኝም፣ የሀገሩን ባንዲራ በዓለም አደባባይ ማውለብለቡን አላቆመም፡፡ በቅርቡ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ በሰይፉ ፋንታሁን ፕሮግራም፣ በካናዳ ከተኛበት ሆስፒታል ሆኖ በስካይፒ ቃለመጠይቅ የተደረገለት ምሩፅ፤ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ስሜት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ያመሰገነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ምንም ሳያገኝ ሀገሩን ማገልገሉ እውነት ቢሆንም፣ መጨረሻ ላይ ግን ሀገሩና ህዝቡ ደርሰውለት ሲያመሰግን አየን፡፡ ከዚህ መማር የሚቻለው ሁሉንም ነገር ትቶና አልፎ ሀገሩን ማገልገል የቻለ ሁሉ መጨረሻ ላይ የልፋቱን እንደሚያገኝ ነው፡፡
በተቃራኒው በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት ጥቅሙን ሲያሳድድ ሀገሩን የረሳ ቢኖር፣ ዕዳ ከፋይ መሆኑ የጊዜ ጉዳይ ነው። በወደቀበት አልጋ ሲቃ እየተናነቀው፣ ያ ሁሉ ሞራላዊና ቁሳዊ ድጋፍ እንደተደረገለት የነገረን ምሩፅ፤ ሀገሩ መጨረሻ ላይ እንደደረሰችለት ማሳያ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ፣ በድካሙና በሞቱ “ይድፋህ” የሚል ቢገኝ እንጂ ለድጋፍ እጁን የሚዘረጋ ባልተገኘ ነበር፡፡  ለአሶሼትድ ፕሬስ አስተያየቱን የሰጠው ጀግናው ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ ምሩፅ ማለት ለዛሬው ማንነቱና ለዛሬው ስኬቱ አብነት የሆነው ሰው እንደሆነ መስክሯል፡፡ ሀይሌ በምሩፅ ብቃት እየተደነቀ ያደገ መሆኑን፣ ሰው መሆኑን እስከ መጠርጠር የደረሰበት ጊዜ እንደነበርና ከአበበ ቢቂላ ቀጥሎ የሚያደንቀው ሰው ቢኖር፣ ምሩፅ መሆኑን ተናግሯል፡፡ መሪነት እንዲህ ነው፡፡ የተሳካለት መሪ፤ ከራሱ የተሻለን መሪ የመፍጠር ልዩ ብቃትና ትጋት አለው፡፡
ሀይሌ ማለት ደግሞ ዘርፈ ብዙ ብቃቶችን ያሳየና በምሩጽ ተምሳሌትነት፣ ዓለምን ያስደመመ ጀግና ነው፡፡ ይህ በተለይ በፖለቲካው መስክ ላሉት ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ አበበ ምሩፅን፣ ምሩፅ ኃይሌን፣ ሀይሌ ቀነኒሳን፣ መሰረት ገንዘቤን፣ ጥሩነሽ አልማዝን ወዘተ----መፍጠራቸው የአትሌቶቻችን ምትሀታዊና ተምሳሌታዊ የመሪነት ችሎታን ያሳያል። በፖለቲካው ዓለም የተለመደው ግን በተቃራኒው ነው፤ ዝንጀሮዎችን ይሰበስብና፤ “ቆንጆ ነህ! በሉኝ” ይላል፡፡ ይህ ማክያቬላዊ የፖለቲካ ሴራ፣ ምሩፅ ሀይሌን እንዲፈጥር አያደርግምና፣ የአትሌቲክስ መንደሩ ለተማረበት ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡
በመጨረሻም፣ የአትሌቲክስ ሰፈሩን በዋናነት እንዲመራ ሀላፊነት የተረከበው ጀግናው ሀይሌ ገ/ስላሴ፤ የመሪነት ቀመርን በተግባር ያሳያል ብለን ብንጠብቅ አልተሳሳትንም፡፡ ሀይሌ ያደረገውን ሌሎች እንዲያደርጉት ለማድረግ አይቸገርም፡፡ በሌሎች ዘርፎች በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ያለው ችግር ዳዴ ሳያውቁ ሩጫን ማስተማራቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡
የአበበ፣ የምሩፅ ልጅ የሆነው ሀይሌ ግን ይቻላል ብሎ እንደሚችል አሳይቶ አስደምሞናልና፣ ለሌላው መንደር የሚተርፍ ስራ ይሰራል ብለን በጉጉት እንጠብቅ፡፡

Read 1149 times