Sunday, 22 January 2017 00:00

ከወልዲያ ባሻገር…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     የመሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታድዬምና የስፖርት ማዕከል በጥር ወር 2005 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ከ4 ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ በመጠናቀቅ ባለፈው ሳምንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።  በምረቃው ስነስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ  አንዳርጋቸው፤ ክቡር ዶክተር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ፤ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው፤ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ሃላፊዎች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ እስከ 10ሺ የሚደርሱ የወልዲያ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች፤ ከ50 በላይ የግል እና የመንግስት ሚዲያዎች ስነስርዓቱን ታድመውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በይፋ በመመረቁትና ለአገልግሎት በዋለው መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ክቡር ትሪቡን ላይ ቆመው ‹‹መንግስት ለስፖርት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም፤ የህዝቡና የባለሃብቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ በሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲና በህዝብ ትብብር የተገነባውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀው ስታድዬም አገር ማስጠራት የሚችሉ ወጣቶች የሚገኙበት ነው›› በማለት ተናግረዋል። የስታድዬምና የስፖርት ማእከሉን  ሙሉ ወጪ በመሸፈን ያስገነቡት ክቡር ዶክተር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በበኩላቸው
‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ፤ እንኳን ደስ ያለን፡፡ ይህን ስታድዬም እንዲሰራ ስናቅደው … ለዶክተር አረጋ ሃላፊነት ስንሰጠው ስራውን እንደሚሰራ ስለማውቅ ነው፡፡ ዶክተር አረጋ ደረጃውን ጠብቆ መሰራት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ስላለው ትንሽ ግዜ ፈጀ፡፡ ግን በመጨረሻም አምሮ ቆንጆ ሆኖ መላው የወልዲያ ህዝብ እንዲጠቀምበት አድርገናል፡፡…. የወልዲያ ህዝብ ውለታ ይህ አይደለም። ይቀጥላል፡፡ ለወልዲያ ህዝብ ስናበረክተው ጥቅም እናገኝበታለን ሳይሆን የወልዲያን ህዝብ ይጠቅመዋል ወይ ነው፡፡ የወልዲያ ህዝብ ደግ ህዝብ ነው፤ ሰላማዊ። አገሩን የሚወድ ነው፡፡ ሃይማኖት፤ ጎሳ፤ ፆታ እና ወገን ሳይለይ ተከባብሮ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ እኛን ያሳደጉን አባቶቻችን ይህን ፍቅር ሰጥተው ነው፡፡ …አገራችንን እንገንባ፡፡ እኔ ባለፉት 25 ዓመታት ከኢህአዴግ የተማርኩት ስርዓት፤ ትእግስት እና አገር መገንባት ነው።…  የምነግራችሁ አገራችን ወደፊት እየነጠረች ነው፡፡… አንድ ላይ ተረባርበን ሁላችንም ይህችን አገር ወደላይ ወደፊት  እንውሰዳት… አመሰግናለሁ፡፡›› ብለዋል፡፡
ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲን የስታድዬም እና የስፖርት ማዕከሉን ቁልፍ ለወልዲያ ከተማ አስተዳደርና ህዝቡ ሲያስረክቡ በአገሩ ወግና ባህል መሠረት፣ ቀደምት አባቶችና እናቶች በተገኙበት በተለያዩ ስነስርዓቶች ተመስግነዋል፡፡ ከከተማዋ እናቶች የመሶብ፤ ከከተማው ታዳጊ ህፃናት የሰላም እርግቦችና የወጣትነት ዘመናቸው የማስታወሻ ፎቶ፤ ከወልዲያ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ ልዩ ሽልማትና ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡ በአገር ሽማግሌዎችም ተመርቀዋል፡፡ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባደረጉት ንግግር ደግሞ ‹‹ለስታድዬሙ የተሰጠው ስያሜ ትክክልና ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ንቁ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ውጤታማ እና ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ልማት እንደሆነ ገልፀው፤ ስታድዬሙ የከተማውን እድገት እና የልማት አጀንዳዎች የሚያነቃቃ እና የሚያቀላጥፍ›› ብለውታል፡፡ በእርግጥም የስታድዬሙና የስፖርት ማዕከሉ የምረቃ ስነስርዓት ከወልዲያ ከተማ ባሻገር በመላው አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ለሚገኙት የስፖርት መሰረተ ልማቶች ተምሣሌት ሆኗል። ከ567 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀው ይህ ስታድዬምና የስፖርት ማእከል  በምስራቅ አፍሪካ ምርጡ እና ዘመናዊው እየተባለ ነው፡፡ በእግር ኳስ ሜዳው የፊፋን ደረጃ የሚያሟላ፤ በመሮጫ ትራኩ የአይኤኤኤፍ ደረጃን የጠበቀ፤ የቅርጫት ኳስ፤ የመረብ ኳስ፤ የመዋኛ ገንዳ እና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎቹ የኦሎምፒክ መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውም እየተገለፀ ነው፡፡
የቢሊዬነሩ እና የሳይንቲስቱ ታላቅነት እና ጥረት
የመሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታድዬምና የስፖርት ማዕከል ምረቃ ስነስርዓት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እና በክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለክቡር ዶክተር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ እና ለሚድሮክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው የዋንጫዎች እና የክብር ሜዳልያ ሽልማቶች ተበርክተዋል፡፡ ሽልማታቸው በዚህ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ ከመመረቁ በፊት ከተማዋ ለሁለቱ ኢትዮጵያውያን ልዩ ክብር አጎናፅፋቸው ነበር፡፡ ስታድዬሙን ለመገንባት ሼህ መሃመድ ቃል ከገቡ እና ሃላፊነቱን ለዶክተር አረጋ ከሰጡ በኋላ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ለሁለቱም በከተማው የጎዳና ስያሜ ሰጥቷል፡፡ ከጀነቶ በር እስከ ጎንደር በር ያለው መንገድ  ‹‹መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ጎዳና›› ሲባል ከጎንደር በር እስከ አናጎ  የሚወስደው መንገድ ደግሞ  ‹‹ዶክተር አረጋ ይርዳው ጎዳና›› በሚል ተሰይመዋል፡፡ የከተማው መስተዳድር ሁለት አደባባዮችን በተጨማሪ ሰይሞላቸዋል፡፡ መቻሬ አካባቢ የሚገኘው አደባባይ   ‹‹መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ አደባባይ›› እንዲሁም አናጎ አካባቢ የሚገኘው አደባባይ  ‹‹ዶክተር አረጋ ይርዳው አደባባይ›› በማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ በምረቃው ስነስርዓት ላይ እንደሁለቱ የተደሰተ አልነበረም፡፡ ስታድዬሙ የተሰራበት ቦታ ድሮ መቻሬ በሚል ስያሜ የሚጠራ ሰፊ ሜዳ ነበር በወጣትነታቸው ኳስ ተጫውተው ያሳለፉበት ይህ ሜዳ ስታድዬምና የስፖርት ማዕከል ስለተገነባበት ልዩ ስሜት ፈጥሮላቸዋል፡፡ በቤተሰቦቻው ቅርበት እና ወዳጅነት በልጅነታቸው ጓደኛሞች ሆኑ፤ በአንድ ትምህርት ቤት በአንድ መንደር አደጉ፡፡ ዛሬ ዶክተር አረጋ የታወቁ ምሁር እና ሳይንቲስት፤ ሼህ መሃመድ ደግሞ ከዓለም ቢሊዬነሮች አንዱ ሆነዋል፡፡ በስታድዬሙ ምረቃ ላይ ከተካሄዱ ስነስርዓቶች አንዱ የነበረው እንደልጅነታቸው በዘመናዊው ሜዳ ላይ እርስ በራስ የፍፁም ቅጣት ምት  በመምታት ኳስ የተጫወቱበት ነበር፡፡ የመጀመርያውን ‹‹ኢሊጎሬ›› ሼህ መሃመድ ከአስደናቂ ማሟሟቅ በኋላ እንደነገሩ ሲመቱ… ዶክተር አረጋ በቀላሉ አድነውታል፡፡ ሁለተኛውን ‹‹ኢሊጎሬ›› ደግሞ ዶክተር አረጋ አክረረው መቱና ሼህ መሃመድ  መረባቸውን በአግባቡ ሸፍነው ቀልበውታል፡፡ ስለሆነም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምቶች ያለምንም ግብ 0ለ0 አቻ ተለያይተዋል፡፡
ቢሊዬነሩ የኢትዮጵያ ስፖርት አጋር ስለመሆናቸው
ክቡር ዶ/ር ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ትውልዳቸው በደሴ ቢሆንም ያደጉት በወልድያ ከተማ ነው፡፡  የሳውዲ አረቢያ እና ኢትዮጵያ  ዜግነት ያላቸው ታዋቂው ባለሃብት  ከዓለማችን ቢሊየነሮች ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  ባለፉት 20 ዓመታት ካላቸው ሃብት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ  ውስጥ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ በኩባንያዎቻቸው በአገሪቱ ዘጠኝ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በሆቴል፤ በኮንስትራክሽን እና በተለያዩ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ዋነኛው የገቢ ምንጫቸው በተለያዩ ሃገራት የተቋቋሙት የፔትሮሊየም ነዳጅ ዘይትና ጋዝ ማምረቻዎች ናቸው።
ባለሃብቱ በኢትዮጵያ ውስጥ 25 እህት ድርጅቶችን ያቀፈው የሚድሮክ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ባለቤትና ሊቀመንበር ሆነው ይሰራሉ፡፡ በስፖርቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የቆዩ ሲሆን በተለይ በእግር ኳስ ፍቅራቸው ለክለቦች፤ ለብሄራዊ ቡድኖች የማበረታቻ ሽልማቶችን በመስጠት፤ በስታድዬሞች ግንባታ የላቀ የገንዘብ ድጋፍ በማበርከት፤ በምስራቅ አፍሪካ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ በማድረግ የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ በጤና ምክንያት ለተቸገሩ ታዋቂ ስፖርተኞች እና ሌሎች ዝነኛ ኢትዮጵያውያን እርዳታ በመለገስ ይታወቃሉ። ክቡር ዶክተር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ የኢትዮጵያ ስፖርት የቅርብ አጋር  መሆናቸውን በተለያዩ ምሳሌዎች ማመልከት ይቻላል፡፡ ከወልዲያ ባሻገር በአገሪቱ የስታድዬም ግንባታዎች የጎላ አስተዋፅኦ አላቸው። ለመቀሌ፤ ለነቀምቴና ለባህርዳር ስታድዬሞች ግንባታ የሰጧቸው የገንዘብ ድጋፎች እና ወደፊት ለመስጠት የገቧቸው ቃሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ የአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይ ጠባቂ ሲሆኑ፤ ኩባንያዎቻቸው የክለቡ  ስፖንሰሮች ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሚያስገነባው ስታድዬም 80 በመቶ ወጭ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል። በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያበረከቷቸው ድጋፎችም ነበሩ፡፡ በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለነበሩ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እውቅ አትሌቶች እና የቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በተለያዩ የህክምና እርዳታዎች ታድገዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል እውቁ የብሄራዊ ቡድንና የቡና ክለብ ግብ ጠባቂ አሊ ረዲ በደቡብ አፍሪካ ህክምናውን እንዲያደርግ ደግፈው ነበር፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ለእግር ኳስ ድጋፍ በማድረግ የክብር ሽልማት ከካፍ ያገኙ ሲሆን በተለይ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ሻምፒዮና ‹‹አላሙዲ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ›› ተብሎ ለ3 የውድድር ዘመናት ሲካሄድ በ1.5 ሚሊዮን ዶላር ስፖንሰርሺፕ በማድረግ የታደጉት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለቱም ፆታዎች በአፍሪካ ደረጃ በ2013 እኤአ የነበራቸውን ስኬት ምክንያት በማድረግ ለሁለቱም ቡድኖች በነፍስ ወከፍ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት ማበርከታቸውም ይታወሳል። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስም የሰጡዋቸው ድጋፎችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በ1996 እኤአ ላይ በአትላንታ ኦሎምፒክ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የትራንስፖርት ወጭ የሸፈኑ ሲሆን ለሰንዳፋ የአትሌቲክስ መንደር ግንባታ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰዋል። በየዓመቱ በመቻሬ ሜዳ የሚካሄደው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እህት ኩባንያዎች የስፖርት ውድድር ቋሚ ታዳሚ ናቸው፡፡ በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ በሜዳ ቴኒስ እና ጠረጴዛ ቴኒስ የሚካሄደው ውድድር ከ550 በላይ የሚድሮክ ሰራተኞችን የሚያሳትፍ ነው፡፡ ክቡር ዶክተር ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በኢትዮጵያ ሚሊኒዬም ለኢትዮጵያ እድገት ባደረጉት አስተዋፅኦ ተምሳሌት ናቸው በሚል ከኢትዮጵያ መንግስት የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በፍልስፍና የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል፡፡
ሳይንቲስቱ ፤ የኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተልማቶች የወደፊት ተስፋ መሆናቸው
ዶክተር አረጋ ይርዳው በትምህርት ደረጃቸው የላቀ ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙ ሲሆን ከዚያም በእንግሊዝ አገር በአየር ትራንስፖርት ምህንድስና የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። በአሜሪካን አገር ደግሞ በትምህርት አስተዳደር በማኔጅመንት የዶክትሬት ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ በስራ ዘመናቸው በመጀመርያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለ6 ዓመት አገልግለው፤ ከዚያም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በመሃንዲስነት ለአስር ዓመታት  ስረተዋል፡፡ ከአገራቸው ከወጡ በኋላ በአሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት በኤሮስፔስ እና በአቪዬሽን ተዛምዶ ባላቸው የሙያ ዘርፎች በምህንድስና ማኔጅመንት እና በአመራር ሰጭነት ለ20 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚነት  ከ18 ዓመታት በላይ የሰሩ ሲሆን ከዚሁ ሃላፊነታቸው ባሻገር የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት፤ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቴክኒክ ሙያና ስልጠና ኢንስቲትዩት ማህበር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ማእድን ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው እያገለገሉ ናቸው፡፡ ዶክተር አረጋ በሳይንቲስትነታቸው የተሳካላቸው መሆናቸውን በተለያዩ ማስረጃዎች ማመልከት የሚቻል ሲሆን፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ በኤሮስፔስ እና በአቪዬሽን የምህንድስና ማኔጅመንት እንዲሁም አመራርነት በብቃት ያገለገሉባቸው ልምዶችን በመጥቀስ ነው፡፡ በአሜሪካ በሚሣይል መርሃ ግብሮችና የሮኬት አካላት ንድፍ ሥራ ውስጥ ተሳትፈው ያስመዘገቡት ውጤት አላቸው። ከስድስት ዓመታት በፊት የአሜሪካው Center for Creative Leadership (CCL) ልዩ ሽልማትን በመጎናፀፍ ከአፍሪካ የመጀመሪያው ናቸው፡፡
ዶክተር አረጋ ይርዳው በስታድዬሙና የስፖርት ማዕከሉ የምረቃ ስነስርዓት ላይ አፅንኦት ሰጥተው ባሰሙት ንግግር በአገራችን በሚሰሩ የስፖርት ማእከላት ላይ  የቴክኖሎጂ ግሩፑ ወጣት ሰራተኞች ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም እንዲያድጉ፤ በአገሪቱ ስታድዬሞች ግንባታ በተሳታፊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው መንግስት ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የ10 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፈርቀዳጅነት
በስታድዬሙ ግንባታ ላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው ከሚመሯቸው 25 ኩባንያዎች አስሩ ተሳትፈውበታል፡፡ በአጠቃላይ 4 ዓመታትን በፈጀው የግንባታ ሂደትም ከ800 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡  ዶክተር አረጋ ይርዳው ስታድዬምና የስፖርት ማእከሉን በመገንባት በ10 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ውስጥ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች አማካይነት የምህንድስና የማምረትና፤ የመገጣጠም ስራው ሙሉ በሙሉ እንዲከናወን መደረጉ እንደ ትልቅ ውጤት የሚጠቀስ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡  በአብዛኛው የአገር ውስጥ ምርቶችን በጥቂቱ ከውጭ በግብዓትነት የተገዙ ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ ወደ ተለያዩ ቅርፆች እንዲለወጥ በማድረግ መሰራቱን ሲያስረዱም፤ የስታድዬሙ ግንባታ እውቀትን፤ ክህሎትን፤ ድፍረትን ለወጣት መሐንዲሶች እና ቴክኖሎጂስቶች የሙያ እድገትን በመፍጠር የጠቀመ፤ እና ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት መቻሉን በመግለፅ ነው፡፡
በስታድዬሙና የስፖርት ማዕከሉ ግንባታ ላይ ከተሳተፉት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ 10 ኩባንያዎች መካከል በዋና ስራ ተቋራጭነት፡ በተባባሪ ተቆጣጣሪነትና በፕሮጀክቱ ዋና ሃላፊነት ሁዳ ሪል ስቴት፤ የፕላስቲክ ወንበሮችን በማምረት እና በመግጠም አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንጨት እና የብረት ዘመናዊ በሮች እና የልብስ ማስቀመጫ ቁምሳጥኖች በመስራት ዋንዛ ፈርኒሺንግ ኢንዱስትሪ፤ ሙሉ ስታድዬሙን የከበበውን የዝናብና ፀሃይ መከላከያ ጣራ ዲዛይን አድርጎ፤ አምርቶ የገጠመው ኮስፒ የብረታብረት ፋብሪካ፤ በጠቅላላ የቅየሳ እና ሰርቬየንግ ስራዎች ሚድሮክ ጂኢኦ እና ኤክስፕሎሬሽን፤ በፕሮጀክት አመራር፣ በኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥናትእና በአስተዳደር ስራዎች የሚድሮክ ሲኢኦ ማኔጅመንት እና አመራር ኢንስትቲዪት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በስታድዬሙና ስፖርት ማዕከሉ ግንባታ አገር በቀል አቅም እና እውቀት መፍጠራቸውን በሁለት የግንባታው ስራዎች ማመልከት ይቻላል፡፡ የፕላስቲክ ወንበሮችን በማምረት እና በመግጠም የሰራው አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ስታድዬሙ በአንድ ጊዜ 25,007 ተመልካቾች የሚይዙ፤ 100 የክብር እንግዶችን የሚያስተናግዱ፤ ለዋና ዳኞችና ተለዋጭ ዳኞች የሆኑ በአጠቃላይ 48 ወንበሮችን በማካተት በድምሩ 25,155 የፕላስቲክ መቀመጫዎች ተገጥመውለታል፡፡  ሁሉንም መቀመጫዎች ዲዛይን አድርጎ ያመረተው፤ ከዚያም በብሎን በሲሊንከን ማስቲሽ እንዳይነቀሉ አድርጎ በመግጠም በአገር ውስጥ ለሚገኙ ስታድዬሞች የሚሆን በቂ አቅም መኖሩን አዲስ ጋዝና የፕላስቲክ ፋብሪካ አረጋግጦበታል፡፡ በሌላ በኩል በስታድዬምና የስፖርት ማእከል ግንባታ በአገር በቀል ኩባንያዎች ያለውን የተሟላ አቅም በተግባር ማስመስከር የቻለው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እህት ኩባንያ ኮስፒ የብረታብረት ፋብሪካ ነው፡፡ የስታድዬሙ ዙርያ ገብ የዝናብና ፀሃይ መከላከያ ጣራ ለመስራት ኮስፒ ከውጭ ያስመጣው ብቸኛው ነገር የፀሃይና ነፀብራቅና ሙቀት ለመከላከል የሚቻልበትን ፕላስቲክን ከእስራኤል በማስገባቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በስተቀር ብረቶቹን በማምረት፤ ዙርያገቡን የስታድዬም ጣሪያ ዲዛይን በማድረግ እና በመግጠም ኮስፒ ብረታብረት ስኬታማ ተግባር ለማከናወን በቅቷል። ይህ ፈርቀዳጅ እና በአገር በቀል ኩባንያ ተግባራዊ የሆነ ግንባታ ስታድዬሙን በማንኛውም የአየር ሁኔታ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያ የአህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ የስፖርት መድረኮች መናሐርያ መሆን ትችላለች
ከሳምንት በፊት በወልዲያ ከተማ ተመርቆ ስራ ከጀመረው መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በኋላ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ የማስተናገድ እውቅና እና ብቃት ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት 6 ደርሷል፡፡ አዲስ አበባ ስታድዬም፤ አበበ ቢቂላ ስታድዬም፤ ድሬዳዋ ስታድዬም፤ ባህርዳር  ስታድዬም፤ ሐዋሳ  ስታድዬም ጨምሮ ማለት ነው። በሚቀጥሉት 5 አመታት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታድዬሞች ብዛት ከ12 በላይ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ከመሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድዬም  በፊት የሐዋሳ እና የባህርዳር ስታድዬሞች ግንባታቸው ሙለሙሉ ተሟልተው ባይጠናቀቁም አህጉራዊና የአገር ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታዎችን በማስተናገድ አገልግሎት መስጠታቸውን በመጀመር  የፈጠሩት መነቃቃት በሌሎች ከተሞችም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም የሚቀጥል ቢሆንም ስታድዬሞቹን የገነቡት፤ የሚያስገነቡት እና የሚያስተዳድሩት የፌደራል መንግስት፤ የክልል መስተዳደሮች፤ የከተማ መስተዳድሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚንቀሳቀሱበት አቅጣጫ መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የመሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድዬምና የስፖርት ማዕከልን በአገር በቀል ኩባንያዎች በመገንባት የፈጠረውን አቅምና ብቃት ተምሳሌት በማድረግ እና በጋራ የሚሰሩበትን ስትራቴጂ መፍጠር መንቀሳቀስአለባቸው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በ2020 እኤአ ለምታስተናግደው 6ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን በስታድዬሞች ያላትን ዝግጁነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራቱ እና ስኬታማ ለመሆን መብቃት ሌሎች ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የስፖርት መድረኮችን ለማስተናገድ የሚቻልባቸውን እድሎች እንደሚፈጥር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ስታድዬሞች ባሻገር ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁ የሚገለፀው የነቀምቴ ስታድዬም፤ በግንባታው ሶስተኛ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የመቀሌ ስታድዬም እንዲሁም ዘግይተው የተጀመሩትና ገና ዲዛይኖቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ያሉት የአዳማ፤ ጋምቤላና ድሬዳዋ ከተሞች   ስታድዬሞች ከመሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድዬም የስፖርት ማዕከል ተምሳሌትነት ተመክሮ በመውሰድ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቀው እና ተመርቀው ወደ አገልግሎት መግባት ይኖርባቸዋል፡፡  በተጨማሪም  በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ዞኖች ይገነባሉ የሚባሉት ስታድዬሞችእና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶች በዚሁ አቅጣጫ መግፋት ይኖርባቸዋል፡፡  እነ ሻሸመኔ፤ ጎንደር፤ ጅማና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ስታድዬሞች እና የስፖርት መሰረተልማቶች ለመገንባት በማቀድ መንቀሳቀስም አለባቸው፡፡ የስታድዬሞች፤ የስፖርት ማዕከሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በኢትዮጵያ መስፋፋታቸው በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች የሚኖራትን ንቁ ተሳትፎ የሚያነቃቃ፤ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጥቅም እና የገፅታ ግንባታ በመፍጠር ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ይሆናል፡፡ በተያያዥ አገሪቱ በትልልቅ የስፖርት መድረኮች በመስተንግዶው፣ በትራንስፖርት አቅርቦት፤ በፀጥታና ደህንነት ያሏትን መሰረተልማቶች ይፋጠኑላታል። በየከተሞቹ ከስታድዬሞቹ ባሻገር ሙሉ የስልጠናና የልምምድ ሜዳዎች ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርትና የመዝናኛ ማዕከሎች እና ሆቴሎች እየተገነቡ ከተሞቻችን በፍጥነት እድገቶች እንዲራመዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የስታድዬሞቹ፤ የስፖርት ማእከሎቹና ሎሎች መሰረተ ልማቶች በየክልሉ መስፋፋት የወጣቶች እና የአገር ተረካቢውን ትውልድ ተስፋ የሚያሳድግ፤ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያነቃቃም ይሆናል። አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮችን በማስተናገድ በቂ ተመክሮ እና አቅም እየተገነባ ሲሄድ እንደ ዓለም ዋንጫ ኦሎምፒክአይነት ታላላቅ መድረኮችን ኢትዮጵያ ማዘጋጀት የምትችልበት ምእራፍ ላይ የሚያደርሳትም ይሆናል፡፡

Read 2086 times