Sunday, 22 January 2017 00:00

የዘሃራ ወላጅ እናት፤ “አንጀሊና ጆሊ ከልጄ ጋር እንድገናኝ ትፍቀድልኝ” አለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ታዋቂዋ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጁሊ በ2007 ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ የወሰደቻት ዘሃራ ወላጅ እናት፤ ‹‹በህይወት አለሁ፤አንጀሊና ከልጄ ጋር እንድገናኝ  ትፍቀድልኝ›› በማለት መማፀኗ ተዘግቧል፡፡
አሁን የ12 ዓመት ታዳጊ የሆነችው ዘሃራ ወላጅ እናት፣ ወ/ት ምንትዋብ ዳዊት ሌቢሶ፤ ‹‹እባክሽን አንጀሊና፤ ልጄን እንዳነጋግራት ብቻ ፍቀጅልኝ›› ስትል በተማፅኖ መጠየቋን የእንግሊዙ “ዴይሊ ሜል ኦንላይን” ዘግቧል፡፡
በደቡብ ክልል ሾኔ ከተማ ከወላጅ እናቷ ጋር በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የምትገኘው ወ/ት ምንትዋብ፤  ዘሃራን በ19 ዓመቷ በማታውቀው ሰው ተደፍራ መውለዷን፣ ጠቁማ፤ ከወሊድ በኋላ ለረዥም ጊዜ በመታመሟ በቤተሰቧ ግፊት ልጇን ለአሳዳጊ ድርጅት ለመስጠት መገደዷን ተናግራለች፡፡
‹‹ልጄን ላለፉት 12 አመታት በቀንም በሌት ሆነ ሳስባት የቀረሁበት ጊዜ የለም›› ያለችው ወላጅ እናቷ፤ ‹‹አሁን ግን የልጄን ናፍቆት መቋቋም አልቻልኩም፤ ልጄ ልክ እንደ አሳዳጊዋ  የምትወዳትና የምትሳሳለት ወላጅ እናት እንዳላት እንድታውቅ እፈልጋለሁ›› ብላለች ከዴይሊ ሜል ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፡፡
አንጀሊና ልጄን በማደጎነት ከወሰደቻት በኋላ ባሉት ጊዜያት ምንም ዓይነት ደብዳቤም ይሁን  መልዕክት አሊያም ገንዘብ ደርሶኝ አያውቅም›› ብላለች፤ የ31 ዓመቷ የዘሀራ ወላጅ እናት
‹‹እንዲያም ሆኖም ዘሃራ ወላጅ እናት እንዳላት እንድታውቅና እንድትጠይቀኝ ብቻ እንጂ ልጅቷን ከአንጀሊና ላይ የመውሰድ ፍላጎት የለኝም›› በማለት አስረድታለች፡፡
እውቋ የሆሊውድ ተዋናይት አንጀሊና ጁሊ፤ በ1997 ዓ.ም ዘሃራን ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ስትወስዳት፣ ወላጆቿን በኤችአይቪ ያጣች ህፃን መሆኗ ተነግሯት እንደነበር ያስታወሰው ዴይሊ ሜል፤ ከ2 ዓመት በኋላ ግን ወላጅ እንዳላት መስማቷን ጠቁሟል፡፡

Read 1505 times