Sunday, 22 January 2017 00:00

ከሃማ ጀርባ እስከ እማማ አበሬ ምጣድ...

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(2 votes)

        (ትዝታ እና ምናብ)
                             
አይሆንም!...
የአራቱን ሰዎች አስተዋጽኦ ያላካተተ የአለማችን እግር ኳስ ታሪክ፣ በፍጹም የተሟላ አይሆንም!...
“የኢትዮጵያ ፉትቦል ከየት ወዴት?...” ትርክት፣ ያለ ሃማ፣ ያለ ጋሽ አወቀ፣ ያለ በሃይሉ እና ያለ እማማ አበሬ፣ ጎዶሎ ነው!...
እኔ... ይሄንን ጎዶሎ ልሞላ መጣሁ!...
የሃማ ጀርባ...
በዘመነ ደርግ የመጨረሻዎቹ አመታት...
ከእሁዶች መካከል በአንደኛው፣ እግር ጥሎህ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ላይ ብትገኝ...
የከተማዋን ጎዳናዎች ተከትሎ በቀስታ እየተራመደ ከላይ ታች የሚመላለስ፣ አንድ አጠር ያለ ሰው ይገጥምሃል፡፡ ይሄን አዳፋ ልብስ ለብሶ የሚጓዝ ሰው፣ እንደዋዛ አልፈኸው ልትሄድ ትችላለህ፡፡
ትንሽ ቆይቶ ግን፣ ሾላዋን ዞሮ፣ አብማን አካልሎ፣ ሸዋ በርን አዳርሶ፣ የፈረስ ቤትን ዳገት ሲወጣ ደግመህ ታገኘዋለህ፡፡ አሁንም ችላ ብለህ ልታልፈው ትችላለህ፡፡
ደግሞ ትንሽ ቆይቶ፣ ይሄው ሰው በንጉስ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ዞሮ፣ ሽቅብ ወደ ካህን ሰፈር ሲያቀና ለሶስተኛ ጊዜ ታገኘዋለህ፡፡ ይሄኔ ግራ ተጋብተህ ትጠይቃለህ፡፡
“ምን ያዞረዋል ሰውዬው?...” ብለህ፡፡
ይሄን የምትለው አንተ ነህ፡፡
የከተማዋ ሰው ግን፣ ሰውየው ማን እንደሆነም ምን እንደሚያዞረውም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ሰውዬው ሃማ ነው - የሚያዞረው ደግሞ የእግር ኳስ ተልዕኮ!...
በስተኋላው ዞረህ ጀርባው ላይ የተለጠፈውን ካኪ ወረቀት ስታይ፣ ሰውዬውን የሚያዞረው ምን እንደሆነ ይገለጥልሃል...
“አስደሳች ዜና ለደ/ ማርቆስ ከተማ እግር ኳስ አፍቃሪዎች!...
ዛሬ ከሰዓት በኋላ፣ የሚጋጠሙ ቡድኖች...
ከፍተኛ አንድ ከ አውራ ጎዳና
መምህራን ከ ጨርቃ ጨርቅ
መጥታችሁ ተመልከቱ!...” ይላል፣ ሀማ በጀርባው ተሸክሞት የሚዞረው ማስታወቂያ፡፡
አሁን ገባህ አይደል?...
አዎ!... ሃማ የደ/ማርቆስ እግር ኳስ ተመልካች እንዳይርቀው የማድረግ ተልዕኮውን በጀርባው ላይ አዝሎ ሲዞር የኖረ፣ ተንቀሳቃሽ የማስታወቂያ ቦርድ ነው!...
የጋሽ አወቀ ዛፍ...
የጋሽ አወቀ መኖሪያ ቤት የሚገኘው፣ ከደብረ ማርቆስ ስቴዲየም አቅራቢያ ነበር፡፡
የጋሽ አወቀ ቤት በተለያዩ ዛፎች የተከበበ ነበር። ሰውዬው ዛፎቹን የተከሉት የኢንቫይሮመንት ጉዳይ አሳስቧቸው ላይሆን ይችላል፡፡ በአጥራቸው ዙሪያ የተከሏቸው ባህር ዛፎች፣ የከተማዋ ብሎም የአለም የሙቀት መጠን እንዳይጨምር በማገዝ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦም “ምንም” ሊሆን ይችላል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን...
የሰውዬው ዛፎች ቢያንስ ለከተማዋ አእዋፍት እና ብላቴናዎች ባለውለታ እንደነበሩ መካድ አይቻልም!...
የእኒህ ታላቅ ሰው ዛፎች፣ ከሰኞ እስከ አርብ የወፎች፣ ቅዳሜና እሁድ የብላቴናዎች መጠጊያ ነበሩ፡፡
የእግር ኳስ ፍቅር እንጂ የእግር ኳስ ጨዋታ መመልከቻ ገንዘብ ለሌለን የኔ ቢጤ የከተማዋ ብላቴናዎች፣ የጋሽ አወቀ ዛፎች መጽናኛዎቻችን ነበሩ፡፡
የስቴዲየም መግቢያ ገንዘብ ያልነበረን እኛ የከተማዋ ልጆች፣ ኳስ ለመመልከት ሰልፍ የምንይዘው የስቴዲየሙ ሳይሆን የጋሽ አወቀ ደጃፍ ላይ ነበር፡፡
ማልደን  ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ዛፎቹ ላይ እንወጣለን፡፡ ቅርንጫፎቹን ሙጥኝ ብለን፣ አሻግረን ወደ ስቴዲየሙ ሜዳ እናያለን፡፡
እርግጥ....
ዛፍ ላይ ተንጠልጥለን የምናየውን ኳስ ጨዋታ፣ አፍን ሞልቶ ማየት ለማለት ይከብዳል፡፡ በግማሽ ልብ ነበር የምናየው - ከዛፍ ላይ እንዳንወድቅ ቅርንጫፉን ሙጥኝ ብለን፡፡
ጨዋታውንም ቢሆን በግማሽ ሜዳ ላይ የሚከናወነውን ብቻ ነበር የምናዬው፡፡ ሙሉውን ሜዳ ማየት የሚችሉት፣ ከዛፎቹ አናት ላይ ከፍ ብለው መሰቀል የቻሉ ሁለት ወይም ሶስት ብላቴናዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ሌሎቹ ዝቅ ስለሚሉ፣ ማየት የሚችሉት ግማሹን ሜዳና አንዱን ጎል ብቻ ነው፡፡
እኒህኞቹ የቀረው ጎል ግብ መቆጠሩን የሚያውቁት፣ ከዛፉ ላይ ከፍ ብለው የተንጠላጠሉት ጓደኞቻቸው ወይም ትኬት ቆርጦ ስቴዲየም የገባው ተመልካች ደመቅ አድርጎ ሲጨፍር ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ የጋሽ አወቀ ችግኞች፣ የኛ ዘመን ብላቴና ትውልድ የእግር ኳስ ፍቅሩን በርቀትም ቢሆን መወጣት እንዲችል በማገዝ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የኖሩ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ የአለማችን የእግር ኳስ ታሪክም፣ እኒህን ባለውለታ ሊዘላቸው አይገባም!...
(በ1990 ዓ.ም ይመስለኛል... ከ18 አመት በታች የኢትዮጵያ ቡድኖች የፍጻሜ ጨዋታን፣ ዛፍ ላይ ሆነው ሲመለከቱ ከነበሩ የከተማዋ ብላቴናዎች አንዱ፣ ወድቆ መሞቱና ይህ አሳዛኝ ክስተትም፣ በኢቲቪ የስፖርት ዜና መዘገቡ ትዝ ይለኛል)
የእማማ አበሬ ምጣድ...
በ1980ዎቹ መጀመሪያ...
በደብረ ማርቆስ ትምህርት ቤቶች መካከል ሲካሄድ የቆየው የእግር ኳስ ውድድር ተጠናቀቀ፡፡
የድል በትግል ት/ቤት ቡድን የንጉስ ተክለ ሃይማኖትን ቡድን 7 ለ 0 አሸነፈ....
7 ጎል የገባበት የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ቡድን ግብ ጠባቂ ጠቅሌ በለጠ፣ ለሽንፈቱ ተጠያቂ ተደረገ፡፡
ጠቅሌ ግን...
“ለሽንፈቱ ተጠያቂ የሚሆኑት እማማ አበሬ ናቸው!” በማለት ጥፋቱን ወደ ሴትዮዋ አላከከ...
“እንዴት?...” ሲሉ ጠየቁት፣ የእርሻ አስተማሪያችን ጋሽ አበራ ግራ ተጋብተው፡፡
ጠቅሌ ጉዳዩን በዝርዝር ማስረዳት ቀጠለ...
“ትናንት አመሻሽ ላይ... ትሬኒንግ ሰርተን እንደጨረስን፣ እንደተለመደው እማማ አበሬ በሰፌድ ያመጡልልን የላብ መተኪያ ሽልጦ በልተን ነበር... በጣም የሚያሳዝነው ግን፣ የሰጡን ሽልጦ ጨው የበዛበት ነበር!... ሌሊቱን ሙሉ ታምሜ ስሰቃይ ነበር ያደርኩት። ነግቶ ወደጨዋታው ስገባም ታምሜ ነበር፡፡ ክፉኛ ውሃ ጠምቶኝ፣ ስሰቃይ ነበር የዋልኩት፡፡ ጨዋታው ሊያልቅ 7 ደቂቃ ያህል ሲቀረው ግን፣ የውሃ ጥሙን ልቋቋመው አልቻልኩም!... ተርስኒውን አደራ ብዬው፣ ከጎሉ ጀርባ ወዳለችው ወንዝ ውሃ ልጠጣ በሄድኩበት ነው፣ ሰባቱም ጎሎች የተቆጠሩብን!... ስለዚህ ለሽንፈታችን ተጠያቂዋ እማማ አበሬ ናቸው!...” ሲል ተከራከረ፡፡
 “ነገርን ከስሩ፣ ውሃን ከፋብሪካ” ይላሉ፣ ያልታሸገ ውሃ የሚደብራቸው የቦሌ ልጆች ሲትርቱ...
እማማ አበሬ ከንጉስ ተክለ ሃይማኖት ትምህር ቤት በስተጀርባ የሚገኘው፣ የእግር ኳስ ሜዳ አቅራቢያ የሚኖሩ ባልቴት ነበሩ፡፡
የተክለ ሃይማኖት ቡድን ተጫዋቾች ቅሬታ አቀረቡ፡፡
የውሰታ ትምህርት ቤት ተጫዋቾች ትሬኒንግ ሰርተው ሲጨርሱ፣ በርዕሰ መምህሩ ቤት ሻዎር እንደሚወስዱና ከአባ ሞሴ ኬክ ቤት የላብ መተኪያ አንድ አንድ ቦንቦሊኖ እንደሚበሉ በመጥቀስ፣ እኛም ይህ ሊደረግልን ይገባል ሲሉ አመለከቱ፡፡
የቡድኑ አሰልጣኝ ጋሽ ደረጀ ጉግሳ፣ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ለተጫዋቾቹ ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ አስገኙ፡፡
“ከነገ ጀምሮ ትሬኒንግ ሰርታችሁ ስትጨርሱ፣ ከሜዳው ዝቅ ብላ በምትገኘው ወንዝ ሻዎር እንድትወስዱ ተፈቅዶላችኋል!... ሻዎር ከወሰዳችሁ በኋላም፣ ከእማማ አበሬ ቤት አንድ አንድ ሽልጦ እንደትልበሉ በጀት ተመድቦላችኋል!...” ሲሉ አበሰሩ አሰልጣኙ፡፡
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ...
ተጨዋቾቹ ከትሬኒንግ በኋላ በወንዟ ሻዎር ወስደው፣ የእማማ አበሬን ሽልጦ ማንከት ያዙ፡፡
በነገራችን ላይ...
እማማ አበሬ ለእግር ኳሳችን እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ይህ ብቻ አይደለም!...
እኒህ ታላቅ ሴት፣ ለትምህርት ቤታችን እግር ኳስ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉት፣ ከምጣዳቸው ላይ በሚጋግሩት ሽልጦ ብቻ ሳይሆን፣ ከምጣዳቸው ስር በሚያፍሱት አመድም ጭምር ነበር፡፡
የትምህርት ቤታችን የእግር ኳስ ሜዳ መስመር የሚሰራው በኖራ ዱቄት ሳይሆን በእማማ አበሬ አመድ ነበር፡፡
ድንገት ሊጡ ኩፍ አልል ብሏቸው አልያም ማገዶ አጥተው ሽልጦ ሳይጋግሩ ከቀሩ ግን፣ ከሜዳው አቅራቢያ አመድ የሚገኝበት አማራጭ ስላልነበር፣ ዳኛው የሚያጫውቱት በሃሳብ መስመር ላይ ነበር፡፡
የአባ ጌቴ ቆሻሻ መጣያ...
ያኔ በእኛ ዘመን፣ የቆዳ ኳስ ብርቅ ነበር፡፡ ትዝ እንደሚለኝ፣ ትምህርት ቤታችን ሁለት ቆዳ ኳሶች ብቻ ነበሩት፡፡
አንደኛውን የቆዳ ኳስ የስፖርት መምህራችን ጋሽ አስራት ለማስተማሪያነት ይጠቀሙበታል፡፡ እርግጥ እሳቸው የቆዳ ኳሱን ሲያነጥሩ፣ እኛ ግን ራሳችን በሰራናቸው የጨርቅ ኳስሶች ነበር የምንለማመደው፡፡
“ሁለተኛው ኳስስ?...” ብሎ የሚያፋጥጥ አንባቢ ይኖራል፡፡
ሁለተኛው ኳስ፣ የጋሽ አስራት ቤት ውስጥ ስለነበር፣ ልጃቸው ከመዋዕለ ህጻናት ሲመለስ አቅፎት ይውላል፡፡
እንደነገርኳችሁ ቆዳ ኳስ ብርቅ ነበር፡፡
የሚነጥር ኳስ አምሮታችንን ለመወጣት፣ ብቸኛው አማራጫችን የአባ ጌቴ ሆቴል የቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ ነበር፡፡
እርግጥ የበሬ ቆለጥ ነፍተንም እያነጠርን እንጫወት ነበር፡፡ ይህ የሚሆነው ግን፣ አባቶቻችን በሬ አርደው ቅርጫ ሲካፈሉ ብቻ ነው - ከአመት አንዴ ወይም ሁለቴ፡፡
ይህ ግን፣ አመቱን ሙሉ ለሚያንገበግበን የሚነጥር ኳስ ናፍቆት፣ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡
ለዚህ ነው የአባ ጌቴን ሆቴል መፍትሄ ያደረግነው፡፡
የአባ ጌቴ ሆቴል፣ ለአልጋ ላይ ጨዋታ ለደረሱ በርካታ የከተማዋ ጥንዶች ብቻ ሳይሆን፣ ለእግር ኳስ ጨዋታ ለደረሱ እልፍ አእላፍ የከተማዋ ብላቴናዎች ጭምር ሁነኛ መፍትሄ ነበር፡፡
የሚነጥር ኳስ ሲያምረን...
ከአባ ጌቴ ሆቴል ጀርባ ወደሚገኘው የቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ እንዘምታለን፡፡
ቆሻሻውን እየፈለስን አንድ ነገር እንፈልጋለን - ኮንዶም!...
የሚገርመው ባዶ እጃችንን አንመለሰም ነበር!... የታሸገ ኮንዶም ብናጣ፣ ጥቅም ላይ የዋለ ኮንዶም አናጣም!...
አራግፈን እንነፋውና በላዩ ላይ ጨርቅ ጠምጥመን አሪፍ ነጣሪ ኳስ እንሰራበታለን!...
የአባ ጌቴ ቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ እና ኮንዶም...
ከካልሲ ኳስ እና ከአንሶላ ቅዳጅ ኳስ፣ ወደ ነጣሪ ኳስ ያሸጋገሩን የእግር ኳሳችን ባለውለታዎች ናቸው!...
የመስመር ዳኛው ዱላ...
ደብረ ማርቆስ ያማረ ስቴዲየም ባለቤት ከመሆኗ በፊት፣ የከተማዋ የእግር ኳስ ቡድኖች ለረጅም አመታት የሚጫወቱት፣ በከተማዋ ምስራቃዊ ዳርቻ በሚገኘው ውሰታ ሜዳ ላይ ነበር፡፡
ከውሰታ ወንዝ ዳር በሚገኘው በዚህ “አጥር የለሽ ስቴዲየም”፣ ብዙ ገራሚ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡
የሆነ ቀን...
የመስመር ዳኛው ማራገቢያቸውን ቤታቸው ረስተውት መጡ፡፡
ማራገቢያውን እንዲያመጣ ወደ ሰውዬው ቤት የተላከው ብላቴና፣ አባ አደም ዳቦ ቤት በራፍ ላይ ተዘብቦ የትኩስ ፉርኖ ሽታ ሲምግ በመዘግየቱ፣ ሌላ መፍትሄ ተፈለገ፡፡
ጸጥታ ሊያስከብሩ የመጡ አንድ የቀበሌ 5 ጥበቃ ጓድ በያዙት ዱላ ላይ፣ የአሰልጣኙ መሃረብ ተቋጥሮበት ማራገቢያ ሆነና ጨዋታው ተጀመረ፡፡
የሚገርመው ግን፣ የመስመር ዳኛው የያዙት ዱላ፣ መምታት ስለለመደ እጃቸው ውስጥ ሆኖ ይሻፍድ ጀመር። የእጅ ውርወራ የተሰጠው ተጫዋች ሲወረውር እግሩን ከነቀለ፣ የመስመር ዳኛው በማራገቢያው ባቱ ላይ ዠለጥ ያደርጉታል፡፡
ምን ይሄ ብቻ!?...
ኦፍሳይት የገባን ተጨዋች እንደዱሮው ማራገቢያ ከፍ አድርጎ ምልክት ማሳየት ትተው፣ ዱላውን አውዠምዥመው ማጅራቱን ጠቅልለው መጣል ጀመሩ።
አንድ ተጫዋች በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሲጎዳስ?... ከውሰታ አፋፍ ላይ የሚኖሩት ወጌሻው ጋሽ በቃሉ ይጠራሉ፡፡ እሳቸው እስኪመጡ ተጨዋቹ ሲንፈራፈር ይቆያል፡፡
በነገራችን ላይ... ልክ እንደ መስመር ዳኛው ሁሉ፣ የመሃል ዳኛውም ለዳኝነት የሚያስፈልጋቸውን መሳሪያ ረስተው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሰዓት...
ዳኛው የሚዳኙበትን ሰዓት ረስተው ሲመጡ፣ የጨዋታው ጊዜ ማለቁን አረጋግጠው ፊሽካ የሚነፉት፣ እረኛው ተበጀ ከእንድማጣ ቤተክርስቲያን ማዶ ሲያስግጣቸው የዋላቸውን ከብቶች እየነዳ ወደ ከተማ ሲያልፍ ሲያዩት ነበር፡፡
የአዲስ አረጉ ውሾች እና የኡመሬ ጮርናቄ...
ደሞ ሌላ ቀን...
ከፍተኛ አንድ እና ጨርቃ ጨርቅ ለዋንጫ እየተጫወቱ እያለ... ዙሪያውን ከቦ የነበረው ተመልካች፣ ድንገት ትርምስምሱ ይወጣል፡፡ ተጫዋቹና ተመልካቹ ይደበላለቃል፡፡ ሁሉም ነፍሴ አውጭኝ ይላል፡፡
“ከማን ነው የምታወጣው?...” አልክ?...
ከአዲስ አረጉ ውሾች ነዋ!...
በትርምሱ መሃል... እሳት የላሱ አራት ውሾች እየተወነጨፉ ከተፍ ይላሉ፡፡ ይሄን ተከትሎም... አንድስ የሚያህል፣ ቀይ ፊቱ በጺም የተወረረ፣ ገጽታው የሚያርድ ሰው፣ ነጭ ፈረሱን እየጋለበ ብቅ ይላል፡፡
አዲስ አረጉ ነው!...
እብዱ አዲስ አረጉ ትርምሱን ከቁብ ሳይቆጥር፣ እየጋለበ ሽቅብ ወደ እንድማጣ እየሱስ ደብር ይፈተለካል... እየዘፈነ...
“አረገረገ ወፉ አረገረገ ወፉ...” እያለ፡፡
ተመልካቹ ተረጋግቶ ጨዋታው ይቀጥላል፡፡
በመካከል ግን... የከፍተኛ አንድ ቡድን አጥቂ፣ ግብ ሊያስቆጥር ጥቂት ሲቀረው...
የኡመሬ ጮርናቄ በኩሽኔታ ተጭኖ ወደ ሜዳው ይገባና፣ አጥቂውን ጠልፎ ይጥለዋል፡፡ ደጋፊው በንዴት ሲጮህ፣ ዳኛው ጨዋታውን አስቁመው እየሮጡ ወደ ኡመሬ ይሄዳሉ፡፡ ከፊቱ ሲደርሱ እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ይልካሉ፡፡ ቀይ ካርድ ሊያወጡ ነው ብለው ሲጠረጥሩ፣ ስሙኒ ያወጡና አሪፉን ጮርናቄ መርጠው ይገዙና፣ እየጎመዱት ጨዋታውን መዳኘታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
የኳስ አቀባይነት አመጣጥ...
እንደሚመስለኝ በአለማችን የእግር ኳስ ታሪክ፣ ኳስ አቀባይነት የተጀመረው በውሰታ ሜዳ ነው፡፡
እንደነገርኳችሁ የመጫወቻ ሜዳው ከውሰታ ወንዝ ጋር ይዋሰናል፡፡
ኳሷ ወንዝ ውስጥ እየገባች ስላስቸገረች፣ የአውራጃው ስፖርት ኮሚሽን መፍትሄ አመጣ፡፡ ፈቃደኛ የሆኑ ብላቴናዎች ከወንዙ ዳር ሆነው ኳሷ እንዳትገባ መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ወዲያው ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ኳስ እንዳያቀብሉ መከልከል ጀመሩ፡፡ ይሄም የሆነው ኳስ አቀባይ የነበሩ ሶስት ብላቴናዎች፣ በብርድ ተመትተው በመታመማቸው ነው፡፡
እንዴት ብርድ መታቸው?... ብላቴናዎቹ ኳሷ ድንገት አምልጣቸው ወንዙ ውስጥ ከገባች፣ ፈጥነው ለማውጣት ሲሉ፣ ራቁታቸውን ሆነው ነበር የሚጠባበቁት፡፡
ስለ ውሰታ ሜዳ ኳስ አቀባይ ብላቴናዎች ካነሳን አይቀር...
የሆነ ጊዜ ላይ... ከፍተኛ ሁለት እና ፖሊስ ቡድኖች እየተጫወቱ እያለ... የከፍተኛ ሁለቱ አጥቂ የሽዋስ ተከስተ፣ በአየር ላይ አክርሮ የመታት ኳስ ከሜዳው ወጥታ፣ ወንዙን አቋርጣ፣ ጫካውን አልፋ የገባችበት ጠፋ፡፡
በአካባቢው ከብት ሲያስግጥ የነበረው እረኛው ተበጀ ኳሷ በአየር ላይ እየተንሳፈፈች ወደ እንድማጣ እየሱስ አቅጣጫ መሄዷን እንዳየ ተናገረ፡፡
ኳስ አቀባዮቹ ብላቴናዎች፣ ተበጀ በሰጠው ጥቆማ መሰረት፣ ጫካውን በሩጫ ሰንጥቀው ወደ እንድማጣ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ገሰገሱ፡፡ ጨዋታው ለሁለት ሰዓት ያህል ተቋርጦ፣ ሁሉም ልጆቹን ሲጠባበቅ ቆየ፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ... ኳስ ሊያመጡ ወደ ደብሩ የሄዱት ብላቴናዎች፣ ኳሷን ትተው ቆርበው ተመለሱ፡፡

Read 2351 times