Wednesday, 25 January 2017 07:20

“አንተ ትብስ... አንች ትብሽ”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በአንድ ቀልድ ጽሁፋችንን እንጀምር።
 “ጎን ለጎን ቁጭ ብለው የማይነጋገሩ ወንድና ሴት ካሉ እነርሱ ባልና ሚስት ናቸው” ይላል።
ሁሉንም ባለትዳሮች ከዚህ ያውጣችሁ የሚል ይሆናል የዚህ አምድ ምኞት። በተለይም ሰሞኑን በክርስትናው እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩ በአላትን ያሳለፍን ስለሆነ በእንደዚህ ያለው ወቅት ደግሞ እርስ በርስ መደጋገፍ መናበብ ለልጆችም ፍቅርን ማሳየት በሰላም በመድረሳችን ደስተኞች ነን የሚል ስሜት እንዲንጸባረቅበት ግድ ይላል። አለበለዚያ ቤትን በተለያዩ ቁሳቁሶች ቢያስውቡት የሚበሉ የሚጠጡ ነገሮች በአይነት በአይነት ቢዘጋጁ እና ዝም ተባብሎ ቢመገቡት ደስታን አይሰጥም። ስለዚህም ለእንደዚህ ያለው አጋጣሚ “ፍቅራችሁን ወደነበረበት መልሱት” ይላሉ Carol Sorgen የተባሉ የስነልቡና ባለሙያ።
አንዱ አንዱን የመረዳት ችግር፡-
ባለትዳሮች አንዳቸው አንዳቸውን ለመረዳት አስቀድሞውኑ ሊከሰት የቻለው ነገርን ምንነት በመመርመር የቻሉትን ያህል መታገስና ነገሮችን ግራና ቀኝ መመልከት ሲገባቸው ያንን ከማድረግ ይልቅ ስሜታዊና ቁጡ በመሆን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ መደንፋት አይገባቸውም። ሰው ከሰው ቀርቶ ከራሱም ሊጣላ ይችላል ወይንም እንኩዋንስ ሰው ከሰው ጥርስ እርስ በርሱ ይጋጫል እንደሚባለው እርስ በእርስ መግባባት ሊያቅት የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አይካድም። ነገር ግን ትዳር ትልቁ ማህበራዊ ትስስር ነውና በትንሹም በትልቁም ነገር እቃ እያነሱ ግድግዳ ላይ ከመወርወር ይልቅ ችግር የተፈጠረው የትጋ ነው? የእኔስ ምላሽ ምን ነበር? ወይንም እኔስ ለችግሩ መፈጠር ወይንም መባባስ ምን አስተዋጽኦ አድርጌአለሁ? የሚለውን በእርጋት መመርመር ጠቃሚ ይሆናል። አንድ ሰው በዋለ ባደረ ቁጥር አስተሳሰቡም ሊለወጥ እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት በችኮላ ሰውን ከማነጋገር ወይንም ከውሳኔ ላይ ከመድረስ መቆጠብ ይኖርብናል ይላሉ የጋብቻና ቤተሰብ ምክር አገልግሎት ባለሙያው ልሽሰሻ ማስቂቅቁስ. ይህንን ችግር ለመፍታት ይላሉ ባለሙያው በዚህ ዙሪያ የተጻፉ መጽሐፎችን ማንበብ፣ የተለያዩ ትምህርታዊ ሴሚናሮችን መካፈል፣ የምክር አገልግሎትን ከስነልቡና ባለሙያዎች መጠየቅ ፣የሌሎችን ባለትዳሮች አኑዋኑዋር ማየትና ልምድ መቅሰም ወይንም በራስ ጥረት ችግርን ለመፍታት መሞከር ጥሩ ዘዴ ነው።
ችግሩን ለመፍታት፡-
ባልና ሚስት ችግር ነው የሚሉትን የጋራ ጠላት ለመፍታት የሚነጋገሩበትን ትክክለኛ ሰአት መወሰንና አክብረውም መገኘት አለባቸው።በዚያ ሰአት ምንም ነገር ሊረብሻቸው አይገባም። ልጆች ወደአልጋ የሚሔዱበት ሰአት መሆን አለበት። ስልኮች እንዳይጮሁ ወይንም የቃል መልእክትን እንዲቀበሉ መደረግ አለባቸው።
ለመነጋገር አመቺ እንዲሆን የተወሰኑ ሕጎችን በመስማማት ማስቀመጥ አለባቸው። አንዱ አንዱን ያለማቋረጥ ወይንም ንግግሩን ላለማደናቀፍ ግዴታ ሊገቡ ይገባል። ለምሳሌም አንዱ በሚናገርበት ወቅት ሌላው ጣልቃ ገብቶ “አንተ/አንቺ እኮ ሁልጊዜ”“ አንተ/አንቺ ምንም “ የመሳሰሉትን ነገሮች አለመደንቀር ያስፈልጋል።
ፊትን ፣ እጅን ወይንም ሌላ አካልን በጸጥታ በማሳረፍ በማዳመጥ ላይ መሆንን ለተናጋሪው ማሳየት ይገባል። አንዱ ላንዱ በሚናገርበት ወቅት ግድ የለሽ በመምሰል አንድ ጊዜ ሰአትን ማየት ሌላ ጊዜ ደግሞ የጥፍርን ቆሻሻ ማጽዳት የመሳሰሉ የግድየለሽ ምልክቶችን ለተናጋሪው ማሳየት አያስፈልግም።
የወሲብ ግንኙነት፡-
ባልና ሚስት ምንም እንኩዋን ቢዋደዱም በወሲብ ስሜት አለመግባባት ሊኖራቸው ይችላል። የወሲብ ግንኙነት የእርስ በእርስ ቅርበትንና መፋቀርን እንደሚፈጥር የታወቀ ነው። ከዚያም በላይ ተፈጥሮአዊ በሆነው መንገድ በአካልም ይሁን በስነልቡና ላይ ጥቅም ያላቸውን ሆርሞን የተባሉ ንጥረነገሮች በተገቢው እንዲሰሩ እና ጤናማ ለመሆን ይረዳል። ስለዚህ ባለትዳሮች የወሲብ ግንኙነታቸውን በሚመለከት እኔ እፈልጋለሁ ...እኔ አልፈልግም ማለት ሳይሆን በሚ ከተለው መንገድ እቅድ ቢኖራቸው ጠቃሚ ነው።
ባለትዳሮች መቼ መገናኘት እንዳለባቸው እቅድ ቢነድፉ ጥሩ ነው። ነገር ግን የግድ ምሽት ላይ፣ ሰዎች ሁሉ ከተኙ በሁዋላ ወይንም ሁለቱም በተለያዩ የስራ ጉዳዮች በደከሙበት ወቅት መሆን የለበትም። ምናልባትም ልጆቻቸው የቀን እንቅልፍ በሚፈልጉበት ሰአት ሊሆን ይችላል። ወይ ንም ወደስራ ከመጣደፋቸው በፊት ቀን ላይ ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም የሚገናኙበትን ጊዜ ከወሰኑና ከተግባቡ ምናልባትም ሰአቱ ሲዳረስ ስሜትም አብሮ የመዘጋጀት ነገር ሊታይበት ይችላል።
Allison Cohen የተባሉ የስነ አእምሮ ሐኪም እንደሚሉት ምናልባትም በመካከል የመፈላለግ ነገር እንኩዋን ቢፈጠር እና አንዱ ለሌላው ስሜት ተገዢ ያለመሆን አዝማሚያ ቢታይበት አንዳቸው ባንዳቸው ላይ የሚያዩትን በጎና የፍቅር መንገድ ማሰብ ጠቃሚ ነው።ባል ወይንም ሚስት አንዳቸው የሌላኛውን ስሜት መረዳት እንጂ ጉዳት ሊያደርሱ አይገባም። የተቻለው ሁሉ ተሞክሮ ነገር ግን ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ የስሜት ወይንም የአካል ችግር ከተፈጠረ ወደሕክ ምናው በመሔድ ባለሙያ ማማከር ጠቃሚ ይሆናል።
ገንዘብ፡-
ገንዘብ በሁለት ተጉዋዳኞች መካከል ችግር ለመፍጠር ሌላው ምክንያት ነው። በገንዘብ በኩል የሚከሰተው ችግር ምናልባትም ገና ሰርግ ከመዘጋጀቱ አስቀድሞም ሊሆን ይችላል። በሰርግ መዋቢያ ቁሳቁስ ፣ወደፊት ሊኖር ስለሚገባ ሀብት በመሳሰሉት ሁሉ አስቀድሞውኑ ችግር ሊፈ ጠር ይችላል። ስለዚህ ቢቻል የገንዘብን ጉዳይ በፍቅራቸው መካከል ጣልቃ ሳያስገቡ ከመጋባታ ቸው በፊት በቂ የሆነ ውይይት አድርገው ኑሮአቸውን ቢመሰርቱ ይመከራል። ሆኖም ግን ችግሩን ለማስወገድ ባለሙያዎች እንደሚከተለው ይመክራሉ።
በቅድሚያ በጊዜው በእጅ ላይ ስላለው የኢኮኖሚ እውነታ ታማኝ መሆን ይጠበቃል። ነገሮች ባልተጠበቀ ሁኔታ እያቆለቆሉ ከሄዱ ኑሮውም እንዲሁ በማይጠበቅ ሁኔታ ይበላሻል።
ጉዳዮን በሚመለከት ለመወያየት ሰላማዊ መንገድን መጠቀም እንጂ በጋለ እና ጸበኛነት ስሜት ባሆን ይመረጣል። ጊዜ ወስዶ ምቹ በሆነ ሁኔታ በማያስፈራ መንገድ መነጋገሩ ለሁለቱም ተጋቢዎች ይጠቅማል።
አንዳቸው ገንዘብ አጥፊ ሌላኛው ደግሞ ገንዘብን ቆጣቢ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህንን ተረድቶ አንደኛው ከአንደኛው ለመማር መሞከር እና ኑሮአቸውን ግንኙነታቸውን ለመጠበቅ ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው።
ገቢን ወይንም ብድርን መደበቅ ትክክል አይደለም። ማንኛውንም ገንዘብን በተመለከተ የሚኖሩትን ዶክመንቶች በግልጽ ባለትዳሮች ሁለቱም ሊያውቁዋቸው ይገባል። ይሄ የአንተ/የአንቺ ኃላፊነት ነው በመባባል ጊዜ ማጥፋት አይፉባም። ለሚፈጠረው ነገር ሁለቱም እኩል ኃላፊነት እኩል ድርሻ እኩል ተጠያቂነት እንዳለባቸው አስቀድመው በማወቅ ተግባብተው ኑሮአቸውን ኢኮኖሚያቸውን መምራት አለባቸው።
ተጋቢዎች ሁለቱም በጋራ የሚመሩትን በጀት የቁጠባ ሂሳብን ጨምሮ መመስረት መቻል አለባቸው። በኑሮአቸው ውስጥ ማን ...ምን መስራት አለበት የሚለውም በስምምነት መወሰን አለበት።
ሁለቱም የየራሳቸው ማለትም አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ የሚመሩት የግል ሂሳብ ሊኖራቸውም ይገባል።
ምትዳር መንከል የአጭርና የሩቅ የግልና የቤተሰብ ግቦች አስቀድሞውኑ መቀመጥ እና ተግባራዊ መሆን አለባቸው።
ተጋቢዎች ሊረሱት የማይገባው ነገር ወላጆቻቸውን የመጦር ግዴታ እንዳለባቸው ነው። ስለዚህም የሁለቱም ወላጆች ድጋፍ የሚሹ ከሆነ በምን መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግና ምን ያህል ወጪ እንደሚያስፈልግ አስቀድሞውኑ በመተማመን መወሰንና ማከናወን አለባቸው።
በቤት ውስጥ በየቀኑ የሚያጋጥሙ ትግሎች፡-
አንዳንድ ባለትዳሮች ከበድ ያለ ስራ ላይ ተጠምደው የሚውሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ መካከል አስፈላጊ የሚሆነው አንዱ ያንዱን አዋዋልና አመሻሽ በትክክል ተረድቶ ስራን በተገቢው መንገድ መከፋፈል ሲሆን ይህም ብልህነትና ትዳርን ከአደጋ የሚጠብቅ ይሆናል። አንተ ትብስ አንች ትብሽ መባባል በትዳር መካከል እጅግ አስፈላጊው አስተሳሰብ ነው።
በቤት ውስጥ የማይቀሩና ሊተገበሩ ይገባል የሚባሉ ነገሮችን በዝርዝር መመዝገብ እና ማንኛችን ምን እንስራ ብሎ መመካከር ይጠቅማል። ግልጽ በሆነ መንገድ በቤት ውስጥ ከእኔ ምን አይነት ስራ ይጠበቃል የሚለውን በመነጋገር ይሄንኛውን አንተ ... ይሄንኛውን አንቺ ስሪው/ ስራው መባባል ብልህነት ነው። ተግባብቶ ለመኖር ለመተዛዘንም ይረዳል።
ባጠቃላይም መፍትሔ ለመስጠት መንገድ መፈለግም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌም አንዱ የቤት ውስጥ ስራን መስራት ካልፈለገ እንደልብስ ማጠብ፣ የልጆች ገላ ወይንም መኪና ማጠብ በመሳሰሉት ስራዎች ላይ መሰማራትና ነገሮችን ቀለል ለማድረግ መሞከር የትዳር ግንኙነትን ለማጠንከር ይረዳል።
ምንጭ webmd.com

Read 1678 times