Wednesday, 25 January 2017 07:24

ከ15 ሚ. ብር በላይ የወጣበት "አሰር ፓርክ" ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በመንገድ፣ በውሃ ስራዎች፣ በሪል እስቴት ግንባታና መሰል የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ የተሰማራው አሰር ኮንስትራክሽን፤ከ15 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ ቦሌ ሩዋንዳ ድልድይ ስር ያሰራውን "አሰር ፓርክ" በዛሬው ዕለት ያስመርቃል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር የማነ አብርሀ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ፓርኩ 6ሺህ46 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን አረንጓዴ ስፍራ፣ የልጆች መጫወቻ፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ፣ ደረጃውን የጠበቀ ካፍቴሪያ፣ የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ማራኪ ፏፏቴ፣ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መፀዳጃ ቤት---- ተሟልተውለታል፡፡
አሰር ኮንስትራክሽን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና በከተማዋ ላይ ያለውን የመናፈሻ እጥረት በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ በማሰብ፣ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር የፓርኩን ግንባታ እንዳከናወነ ጠቁሟል፡፡  
አሰር የፓርኩን የማስተዳደር ሂደት ሌላ ድርጅት ቀጥሮ ለማሰራት መወሰኑን ገልፆ፣ ፓርኩ ለተጠቃሚዎች መጠነኛ ገንዘብ እንደሚያስከፍልና ገቢውም ፓርኩ ራሱን የሚያስተዳድርበት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ግንባታው በውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎች  ችግሮች ከታቀደለት ጊዜ በሁለት ዓመት ቢዘገይም በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁንና ለከተማዋ አንድ የአይን ማረፊያ መሆኑን የተናገሩት ኢንጂነር የማነ፤ለተወሰኑ ሰራተኞችም የስራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

Read 1430 times