Wednesday, 25 January 2017 07:25

በ1.9 ቢ. ብር ዘመናዊ የወረቀት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ስራ ይጀምራል ተብሏል
                                 
      የካቲት ፐርፕል ወረቀት ፋብሪካ በ1.9 ቢ. ብር ዘመናዊ ፋብሪላ ሊገነባ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ላይ የሚገነባው ፋብሪካው፤ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ ፋብሪካው የቻይና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተባለ መንግስታዊ ተቋራጭ ጋር የዲዛይን፣ የግዥና የግንባታ ስምምነት ሰሞኑን በማርዮት ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ የግንባታው ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ያለው እንደተናገሩት፤የ ፋብሪካው ግንባታ በ3 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ፣ በቀን 210 ቶን ጥቅል ወረቀት ለማምረት የሚያስችል ግንባታ ያካሂዳል፡፡ በምዕራፍ ሁለቱ ግንባታ ደግሞ በቀን 45 ቶን ለስላሳ ወረቀት ለማምረት የሚያስችል ግንባታ እንደሚካሄድ አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ የምዕራፍ ሶስቱ የፋብሪካ ግንባታ ሂደት የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት በበቂ መጠን ማግኘት እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል፡፡
70 ከመቶ በላይ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል የተባለው ይኸው ፋብሪካ፤በዓመት 70 ሺህ ቶን የማሸጊያ ካርቶኖችና 15 ሺህ ቶን ለደብተርና ለልዩ ልዩ ውጤቶች ማምረቻ የሚሆኑ ለስላሳ ወረቀቶችን ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአገሪቱ በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ምርት ፍላጎት መኖሩን የገለፁት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ዓለሙ ሶሜ፤ይህንን የወረቀት ፍላጎት ለማሟላት ከ2.6 ቢ. ብር ወይም ከ130 ሚ. ዶላር በላይ ገንዘብ በየዓመቱ ወጪ ይደረጋል ብለዋል። የወረቀት ፋብሪካው መገንባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ከማስቻሉም በላይ ምርቱን ወደ ውጪ አገር ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝም ተነግሯል፡፡  
ከሰባት ዓመታት በፊት ወደ ግል ይዞታነት የተቀየረው የካቲት ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ የሚያስገነባው አዲሱ የወረቀት ፋብሪካ፤ለ2500 ሰራተኞች ቋሚ፣ ለ7 ሺዎቹ ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል እንደሚያስገኝ ተጠቁሟል፡፡  

Read 2225 times