Wednesday, 25 January 2017 07:25

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች፤ መንግስት ትክክለኛ ችግራችንን ይመርምርልን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 “መሬታችን ላይ ስደተኞች በመስፈራቸው እየሰራን አይደለም”
                                           
      በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች፤” መንግስት የምናቀርባቸውን ችግሮች ተረድቶና
በፅሞና መርምሮ፣ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አለበት” ይላሉ። በክልሉ ኢታንግ ወረዳ የእርሻ ኢንቨስትመንት ያላቸው ባለሃብቶች
ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከባንክ የብድር አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ቢሮክራሲ፣ የሠው ሃይል ችግር፣ ስደተኞች በእርሻ መሬቶቻቸው ላይ መስፈራቸው------- ለስራቸው እንቅፋት በመሆን ለኪሳራ ዳርጓቸዋል፡፡ በክልሉ ከ2002 ጀምሮ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት
አቶ አደገ ንጉሴ ጨምሮ ሌሎች ባለሃብቶች፣ ቅሬታቸውን ዝግጅት ክፍላችን ድረስ ይዘው መጥተው ነግረውናል፡፡ ከአቶ አደገ ንጉሴ
ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ባለሃብቱ ይጀምራሉ፡-

        የኩባንያዬ ስም “ዌስተርን አግሮ ፕሮሰሲንግ” ነው፡፡ በውስጡ ፈረሱላ ኮፌ ፕሮሰሲንግ፣ አደገ እርሻ፣ አደገ ኤክስፖርት የሚባሉ ድርጅቶች አሉት።
መቼ ነው የጋምቤላውን የእርሻ መሬት ተቀብለው መስራት የጀመሩት?
መሬቱን የተቀበልኩትና ስራ የጀመርነው በ2002 ዓ.ም ነው፡፡ 500 ሄክታር መሬት ነበር መጀመሪያ የተቀበልነው፡፡ መጀመሪያ የተሰጠንን 500 ሄክታር መሬት አልምተን መጨረሳችንን የወረዳው አስተዳደርና የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አንድ ላይ አረጋግጠው፣ ተጨማሪ 500 ሄክታር መሬት ሰጡን፡፡ በዚህ አግባብ አሁን ላይ እስከ 2000 ሄክታር ደርሰናል፡፡ ለ8 ዓመታት ገደማ በቦታው ላይ ኢንቨስት እያደረግን ነው፡፡
የተሰጣችሁን መሬት ሁሉም አልምታችኋል?
ከተሰጠን አጠቃላይ 2 ሺህ ሄክታር መሬት፣ የተሰራበት 1100 ያህሉ ላይ ብቻ ነው፡፡
ለምን ሙሉውን እስከ ዛሬ ማልማት አልቻላችሁም?
ልማቱ ከባድ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ በዚህ መጠን ካለሙት ጥቂት ኩባንያዎች አንዱ የኛ ነው፡፡ አዲስ መሬት መንጥረን ነው የምንሰራው፤ ይሄ በራሱ ብዙ ሂደቶች አሉት፡፡ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር አንድ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ብድር ማግኘት አለብን፤ ግን አሁን ባለው ቢሮክራሲ የተነሳ ይሄን ማድረግ አልቻልንም፡፡
 ምንድን ነው ያለማችሁት?
በዋናነት ከክልሉም ሆነ ከአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለን ስምምነት ጥጥ እንድናለማ ነው፡፡ ከ2006 ዓ.ም በኋላ ግን ጥጥ የማልማት እቅዳችን እንከን ገጥሞታል፡፡ በተለይ ከደቡብ ሱዳን ስደተኞች ጋር በተገናኘ ለጥጥ ልማት የምንጠቀማቸው ኬሚካሎች ጎጂ በመሆናቸው ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎብናል፡፡ ለጥጥ ልማቱ የተለያዩ የአረምና የፀረ-ነፍሳት መድኃኒቶችን እንጠቀማለን፤ ያንን በምንጠቀምበት ጊዜ በስደተኛ ካምፑ ያሉ ሴቶች ለምግብነት የሚጠቀሙበት “ዎር” እና “ሲሞኮር” የሚባሉ ቅጠሎች አሉ። እኛ እንደ አረም ነው የምናስወግደው፡፡ ቅጠሉን ለማስወገድ የምንጠቀማቸው ኬሚካሎች ቶሎ ከቅጠሉ ላይ ለመትነን አይችሉም፡፡ ስደተኞቹ ደግሞ ያንን ቅጠል ስለሚመገቡ፣ ለጤናቸው አስጊ በመሆኑ፣ የጥጥ ልማቱን ወደ ሌላ አዘዋውረን፣ ማሾና ሩዝ ለማልማት ተገድደናል፡፡
በዚህ ምርታችሁ ውጤታማ ሆናችኋል?
በራሳችን ስንሰራ በጣም ውጤታማና አትራፊ ነበርን፡፡ ከ2002-2005 ድረስ በተከታታይ አትራፊ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከባንክ ጋር በነበረው ቢሮክራሲ ኢንቨስትመንታችን አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ እኛ በ2002 መሬቱን ተረክበን ስንሰራ፣ የእርሻ ልማታችን በሚገኝበት “ኢንታንግ” ወረዳ ላይ 5 ኢንቨስተሮች ብቻ ነበርን፡፡ በኋላ ግን ቁጥራቸው እየጨመረ ሄዶ፣ በአሁን ሰዓት ከ160 በላይ ኢንቨስተሮች በኛ ወረዳ ላይ ብቻ አሉ። ያ ደግሞ የመሬት መደራረብና ሽኩቻ ውስጥ ከተተን፡፡ የባንክ ብድር ሂደቱም ከዚህ ጋር ተያይዞ ቢሮክራሲያዊ ነው የሆነብን፡፡
በሌላ በኩል እ.ኤ.አ በታህሳስ 2013 በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ በርካታ ስደተኞች መጡ፡፡ በኛ ኢንቨስትመንት ላይ ነው ካምፖቻቸው የተገነባው፡፡ እሱ በእጅጉ ጎድቶናል፡፡
የባንክ ብድር አሰጣጡ ላይ የነበረው ችግር ምንድን ነው?
ግልፅነት አልነበረውም፤ ቢሮክራሲያዊ ነበር። ይሄ ውስብስብ የሆነ ነገር ውስጥ ከቶናል፡፡ አሁን ኩባንያችን በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ነው ያለው፤ ዘግቶ እስከ መውጣት ደርሰናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የምናለማበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም ቦታው በስደተኞች ተይዞ ነው ያለው፡፡ ጥቂት መሬት ነው ክፍት የሆነው፡፡ በእኔ እርሻ ላይ እስከ 300 ሰዎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። ኩባንያችን ከክልሉ ግብርና ቢሮና ከክልሉ ም/ፕሬዚዳንት፣ በ2006 ዓ.ም ተሸልሟል። 10 ሄክታር መሬት ለአግሮ ፕሮሰሲንግና በሽልማት መልክ ተሰጥቶናል፡፡ በ2007 ዓ.ም በተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች በአል ላይ፣ ከክልሉ ፕሬዚዳንት “ጠንካራ አልሚ” ተብለን ሽልማት ተሰጥቶናል፡፡
ሌላው ያጋጠመን ችግር፣ በአካባቢው በሚገኙ ሁለት ብሄሮች ግጭቶች ሲከሰቱ የሚደርስብን ጥቃት ነው፡፡ ዘበኞቻችን ተመተውብናል፡፡ ቋሚ ሰራተኞቻችን ተበትነውብናል፡፡ በቀላሉ ሰራተኞች አይገኙም፡፡ የተዘራው ሰብልም እዛው ማሳ ላይ ነው ሲቀርብን የነበረው፡፡ የሰው ኃይል በዋናነት የምንጠቀመው የአካባቢውን ወጣቶች ነው፡፡ በዚህ በእጅጉ ተጎድተናል፡፡
ከእርስዎ መሬት በምን ያህሉ ላይ ነው ስደተኞች የሰፈሩት?
400 ሄክታር በሚሆን ቦታችን ላይ ነው፡፡
እንዴት ነው የሰፈሩት? ፍቃዳችሁ ተጠይቆ ነው?
አልተጠየቅንም፡፡ አንድ ስሙን የማልጠቅሰው ባለስልጣን ነው ደውሎ፣ ያለን አማራጭ በቦታው ላይ ማስፈር ብቻ ነው ያለኝ፡፡ የስደተኛ ህግ እንደሚለው፤ ካምፕ ከኢንቨስትመንት አካባቢ 6 ኪ. ሜትር መራቅ አለበት፣ የሰው ቁጥርም የተመጠነ ሊሆን ይገባል፡፡ መጀመሪያ ተነጋግረን ተማምነን የነበረ ቢሆንም፣ ከ4 ወር በኋላ ግን በድንገት አሰፈሩብን፡፡
ስደተኞቹ ሲሰፍሩ፤ ”በዚህን ጊዜ ይለቁላችኋል” ተብሎ የተሰጣችሁ የጊዜ ገደብ አልነበረም?
ምንም አይነት የጊዜ ገደብ አልተሠጠንም፡፡
አቤቱታ አላስገባችሁም?
ለወረዳው አመልክተን ነበር፤ ምላሽ የለም። በ2006 ዓ.ም ይህ ችግር ሲፈጠር ከወረዳው፣ ከክልሉ አስተዳደርና ከግብርና ቢሮ፣ ሰዎች ተመድበው፣ ድንበራችን ምልክት ተደርጎ ተሠምሮ ነበር፡፡ ስደተኞቹ ያንን ድንበር ነው አልፈው የገቡት፡፡ አሁን በክልሉ ባለስልጣናት የተቀያየሩ በመሆኑ አዲሶቹ ይሄን ጉዳይ ብዙ የሚያውቁት አይመስለኝም። እኛ ይሄን ኢንቨስትመንት ስንጀምር፣ የክልሉን ተወላጆች ነበር አሰልጥነን የምንቀጥረው። እነዚህን ወጣቶች ስናሰራ፣ “ስደተኛ አሰራችሁ” እየተባልን፣ ሠራተኞቻችን እየታሰሩብን ሁሉ ነበር። ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
አሁን መፍትሄው ምንድን ነው? መንግስት ምን ማድረግ ነው ያለበት?
በዋናነት ኢንቨስትመንቱ አደጋ ላይ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ መንግስት ያለውን ቢሮክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታልን፣ መሬታችን ላይ የሠፈሩት ስደተኞች ጉዳይ እንዲመረመረልን እንፈልጋለን፡፡ የተወሳሰቡ ችግሮች ሁሉ መጀመሪያ እንዲፈቱልን እንሻለን፡፡ እነዚህ ሳይፈቱ እርምጃ መውሠዱ ድራማ ነው የሚሆነው። የስደተኞቹ ጉዳይ ሊጠናልን ይገባል፡፡ ብድር መክፈል አልቻልንም፡፡
ካልሠራን እንዴት እንከፍላለን? አሁን መንግስት ችግሩን እየፈታበት ያለው መንገድም በፅሞና ሊጤን ይገባዋል፡፡ የታሰሩ ሰዎች አሉ፤ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡ ሁላችንም መጀመሪያ ከመንግስት ጋር በእኩል መወያየት አለብን፡፡
ከአቶ አደገ በተጨማሪ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ አዲስ አድማስ ቢሮ ከመጡት አንዱ አቶ ሃብቱ ዳኘው ናቸው፡፡ እሳቸውም ስለ ችግሩ እንዲህ ያብራራሉ፡፡
አቶ አደገ እንዳሉት እኔም የስደተኛ ካምፑ ተጠቂ ነኝ፡፡ የተሠጠን 1 ሺህ ሄክታር መሬት ነበር። የጥጥ ልማት ልናለማ ነበር ውላችን፡፡ ግን ምን ያህል ሄክታር ላይ እንዳረፈ ባልለካውም፣ በኔ የኢንቨስትመንት መሬት ላይም ስደተኞቹ አሉ፡፡ በኔ እርሻ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጎራባች ኢንቨስትሮች መሬትም ላይ ስደተኞቹ አርፈውበታል፡፡ የስደተኞቹ በዚያ ማረፍ የፈጠረብን ችግር፣ ጥጥ ሲዘራ የምንጠቀመው ኬሚካል ጎጂ በመሆኑ ለማቆም ተገድደናል፡፡
ችግራችሁን አመልክታችሁ ነበር?
አዎ ለሚመለከታቸው ሁሉ ለክልሉም ለግብርና ቢሮም አመልክተን ነበር፤ ግን ከአንድ ወር በኋላ ስደተኞች ይነሣሉ ነበር የተባልነው፡፡ ግን ይኸው 9 ወር አልፎናል፤ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ እርሻችንን ለማቆም ተገደናል፡፡
(የክልሉን የእርሻ ኢንቨስትመንት በተመለከተ በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት፤ በክልሉ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው የእርሻ ኢንቨስትመንት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ በተለይም ባለሃብቶቹ ከባንክ የሚወስዱትን ብድር ላልተገባ አላማ እያዋሉ፣ መሬቱን ፆም ማሳደራቸውን ይጠቅማል። ለ623 ባለሀብቶች 630,518 ሄክታር መሬት የተላለፈ ቢሆንም፣ የለማው 76,862 ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑ በጥናቱ ተለይቷል፡፡)

Read 1397 times