Wednesday, 25 January 2017 07:38

የፍልስፍና ጥንስስ - ከኢትዮጵያዊው ፈላስፋ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

     የ3000 ዘመን ታሪክ ባለቤት ከሆነችው ኢትዮጵያ አንድ ፍልስፍና ይመዘዛል፡፡ ይኸውም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቅ ያለው የኢትዮጵያ የፍልስፍና አባት ለማለት የምንደፍርለት ዘርዐ ያዕቆብ ነው፡፡ በዓለም ላይ የተከሰቱ ርዕዮተ ዓለሞችን ሁሉ የፍልስፍና ውጥንና ውጤት መሆናቸው እሙን ነው፡፡ የዘርዐ ያዕቆብ ምናብ ብቻ ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ጥብቅ ሀሳቦች የተነሱበት እውነት፤ ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ የረቀቁ የበለጸጉና የጠለቁ ትንታኔዎችን በመስጠት ነፍሳችንን ይክሰዋል፡፡ ለፍልስፍና አእማድ የሆነው ዘርዐ ያዕቆብ፤ “ማንነትን በበጎ ነገር ማጠር” በማለት የሚያቀነቅነው አስተሳሰብ ውስጥ የሚበቅሉ የእውነት ምንጮችን እናገኝበታለን፡፡ በዚህም ወደ ታላቁ የጥበብ ምንጭ እንመጥቃለን፤ ውለታውን ለማስታወስ፣ ኢትዮጵያዊነቱን ለመመስከር ዝክረ ዘርዐ ያዕቆብ ተዘጋጅቷል፡፡

ውልደትና እድገት
ዘርዐ ያዕቆብ የክርስትና ስሙ ሲሆን የዓለም ስሙ ወርቄ እንደሆነ በአለቃ ያሬድ ፈንታ “ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ ወልደ ሕይወት” መግቢያ ላይ ተጠቅሷል፡፡ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘርዐ ያዕቆብ በገጠር ስለመወለዱ ታሪኩን የሚዳስሱ የተለያዩ ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡ ከገበሬ ቤተሰብ መገኘቱን በገዛ አንደበቱ የሚናገረው ዘርዐ ያዕቆብ፤ በ1592 ዓ.ም ወደዚህ አለም መጥቷል፡፡ ይሄ ዘመን ደግሞ የአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት መሆኑ ነው፡፡
እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ለትምህርት የሰነፈ ባይሆንም የድምጹ ሻካራነትና የተማሪ ቤት ወዳጆቹ ስላቅ፣ ሰዋሰውና ቅኔ ለመማር ፊቱን እንዲያዞር ያስገደደው ሲሆን እግዚአብሔርም ጥበቡን እንደገለፀለትም ደስተኛ እንደሆነ መፅሀፈ ፍልስፍና ላይ ተጠቅሷል፡፡ ለንባብና ለማወቅ ያደረገውን ጥረት ሳንቆጥር፣ ዘርዐ ያዕቆብ 14 ዓመት ከሦስት ወር ለትምህርት በመጠቀም የትምህርትን ህልውና ለማሳየት ጥረት አድርጓል፡፡ ያውም በዚያ ዘመን!!

ትዳርና ልጅ
አፈንጋጩ ዘርዐ ያዕቆብ ከፍልስፍና ልጆች የሚቃረነው የትዳር ጓደኛ ምርጫው ጋብቻውን አክባሪነቱ ከመረዳት እንጀምርና ከእርሱ እውቀትና ምጥቀት የማትስተካከለዋን የሀብቱ ቤተሰብ ለማግባት ሲጠይቅ፣ ሲደራደር እሺኝታ ሲያገኝ፣ ሚስቱን ለማስደሰት ሲጥር እንመለከታለን፡፡ በእርሱ አንደበት፤ “ይህ መንገድ ወደ አበሳ ይስባልና ሴት የሌለችው ወንድ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንደማይገባው አወቅኩ” ሰዎች ተፈጥሮአቸውን ክደው ሊኖሩ አይገባቸው እያለ ይሞግታል፡፡ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ከሚለው መለኮታዊ ሃሳብ ጋር ስምሙ የሚያደርገው፣ እምነቱን በዘመን ተሻጋሪ ስብከቱ ሲያስጠነቅቅ፡- የባልና ሚስት ድንበርና ክልሉ ፍቅር መሆን እንዳለበትም አጽእኖት ይሰጣል፡፡
መልከ ጥፉ እንደሆነች የሚመሰክርላት ሂሩት፤ ምግባሯን ልባምነቷን መመዘኛ ማድረጉ፣ ጠንካራ የሆነ የፍቅር እምነት እንዳለው ለማሳየት ምስክር ይሆናል፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ልጁ ሀብተ እግዚአብሔርን መውለዱ፣ ዘርዐ ያዕቆብ የቤተሰብ ምጣኔን የያኔ ጀምሮታል ለማለት ያስደፍራል። ከፅሁፍ ስራ ባገኘው ሀብት ቤት ከሰራና የቤት እንስሳ ከገዛ በኋላ መውለዱ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ወደ ምንኩስናው የሸፈተውን የልጁን ልብ መልሶ፣ የሦሶት ልጆች አያት መሆን መቻሉ ለህጋዊነት የላቀ ዋጋ እንደሚሰጥና እምነቱ እንደሆነ ያረጋግጥልናል።

ፍልስፋና
ዘርዐ ዕቆብ ወደ ፍልስፍና የገባባት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ተለምዶአዊ አኗኗሮችን በመገርሰስ፤ ባልዘመነ ዘመን፣ ዘመናዊ ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ ይሰጣል፡፡የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የተመለከታቸው “ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ” ሆነ “መጽሐፈ ፍልስፋና” ሥለ ፈላስፋው ያለንን ግንዛቤ ከማሳደግና እውቀት ከማዳበር በዘለለ ተቃርኖ የላቸውም፡፡ የዘርዐ ዕቆብ የምርምር ፍልስፋና፤ ወሰን ያልተበጀለትና ሁሉን አቀፍ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በሁለቱም መጽሐፎች ላይ ፈላስፋው በጥልቀት የተመለከታቸውን የእግዚአብሔር ህላዌነት፣ሥነ ምግባር፣ እውነት፣ በዓለም ላይ ስላሉ ሐይማኖቶች እሰጣ ገባ፣ ፍትህ፣ ስለ መለኮታዊውና ሰዋዊ ህግ፣ ማህበራዊ ኑሮና ዘመናዊነት በተመሳሳይ መልኩ ያቀርባል፡፡ አለቃ ያሬድ ፈንታ ለየት ባለ መልኩ የፈላስፋውን የስነ ፍጥረት ሐተታ፣ ከንባብና ትምህርት ስለሚገኝ ጥቅምና ስለተለያዩ ሕይወታዊ ምክሮች በስፋት ሲዳስስ፤ በአንጻሩ “መጽሐፈ ፍልስፋና” በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ስለተነሱ ጥቄዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ የዘርዐ ዕቆብ የፍልስፋና ጥልቀት፤ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው አጥር ክፋት መሆኑን በማስረዳት ይኮንናል፡፡ ፈላስፋው የእግዚአብሔርን መኖር ቢያረጋግጥም የሁሉንም ሐይማኖት ግን ከመንቀፍ ቦዝኖ አያውቅም። ስለዚህ ሐይማኖት ምንድነው ብለን ለመፈተን ጥልቅ ምርምር ይጠይቀናል፡፡ ሰዎች “ሁሌም በራሴ ልክ ነኝ” ከሚል ትምክህት መውጣት አለባቸው የሚለው በምርምሩ የደረሰበት ጥግ ሲሆን ለእናም የሚበጅ መላ ነው፡፡ የፖስት ሞደርኒዝም አቀንቃኝ የሆነው የመካከለኛው ዘመኑ ዘርዐ ያዕቆብ፤ በ68 ዓመቱ ለዚህ ትውልድ የሚረቡ ሁነኛ ሀሳቦችን በተማሪው ግፊት አንደጻፋቸው ይናገራል፡፡

Read 4283 times