Monday, 30 January 2017 00:00

የነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ት/ቤቶች፤ ይዘጉ መባላቸውን ተቃወሙ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

    ከ12 ዓመታት በፊት በቱርክ ባለሃብቶች የተመሰረተውና በአገሪቱ ውስጥ ከ1700 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኘው ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ት/ቤቶች እንዲዘጉ ከቱርክ መንግስት የቀረበው ጥያቄ ህገወጥ ነው ሲሉ የት/ቤቱ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
በአዲስ አበባ አለምገና፣ ሳርቤትና ሲኤምሲ አካባቢዎች 3 ቅርንጫፎች ያሉት ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ት/ቤት፤ በቱርክ መንግስት የቀረበበትን፤ “በሽብር ተግባር እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ቡድኖች ጋር ንኪኪ አለው” የሚለውን ውንጀላ በጥብቅ እቃወመዋለሁ ብሏል፡፡ ት/ቤቶቹ ከሃይማኖትና ከማንኛውም የሽብር ተግባር ነፃ የሆኑና የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ያደረጉ ትምህርቶችን ለተማሪዎች በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የት/ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎች ጠቁመዋል፡፡
የት/ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን ት/ቤቶቹን ለጋዜጠኞች ባስጎበኙበትና በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኩባንያቸው በአገሪቱ የንግድ ህግና ሥርዓት መሰረት፣ በህጋዊነት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በከፈታቸው ቅርንጫፎች ከ1700 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ የ38 የዓለም አገራት ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ የተለያዩ ሃይማኖትና እምነቶችን የሚከተሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ት/ቤቶች፣ የትምህርት አስተባባሪና የአይናክ ትምህርትና ህክምና አገልግሎቶች ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰሊን አይዲን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የቱርክ መንግስት በት/ቤቶቹ ላይ ያቀረበው ውንጀላ ተቀባይነት የሌለውና ሲሆን ት/ቤቶቹ ከተሰማሩበትና እየሰጡ ካሉት አገልግሎቶች ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ነው ብለዋል፡፡ በኩባንያው ሥር ተመዝግበው በአገሪቱ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ት/ቤቶችም ሆኑ ሌሎች የንግድ ተቋማት፣ የአገሪቱን የንግድ ህግ አክብረውና ተገቢውን ታክስና ግብር እየከፈሉ የሚንቀሳቀሱ ህጋዊ ተቋማት ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ላለፉት 12 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግስት አንዳችም ችግርና ስህተት ያላገኘባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በቱርክ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚባለው ፌቱላህ ጉለንና በእሳቸው ስም ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የተናገሩት ቱርካዊ የት/ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎች፤ በቱርክ መንግስት የቀረበው የ“ት/ቤቶች ይዘጉልኝ” ጥያቄ ተቀባይነት የሌላቸውና ህገ ወጥች ናቸው ብለዋል፡፡

Read 1789 times