Monday, 30 January 2017 00:00

በኩዌት አሠሪዋን ገድላለች የተባለችው ኢትዮጵያዊት በስቅላት ተቀጣች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   በኩዌት አሠሪዋን ገድላለች፤ የተባለችውን ኢትዮጵያዊት የቤት ሠራተኛ ጨምሮ 7 ሰዎች በስቅላት መቀጣታቸው፣ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ውግዘትን እያስተናገደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም፣ በኩዌት የሚገኘው ኤምባሲ የሐዘን መግለጫ በድረ ገፁ አሰራጭቷል፡፡
ስሟ በውል ያልተገለፀው ኢትዮጵያዊቷ ወጣት፣ ከ6 ዓመት በፊት አሠሪዋን ገድላለች፤ በሚል የተፈረደባት የሞት ፍርድ፣ ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በሀገሪቱ ማዕከላዊ እስር ቤት በስቅላት ተፈፃሚ ሆኗል፡፡
በኩዌት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ፣ በድረ ገፁ ባሰራጨው የሐዘን መግለጫው፣ አሠሪዋን በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ነች፣ በማለት የኩዌት የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሞት እንድትቀጣ ያስተላለፈውን ብያኔ ተከትሎ ለከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ቀርቦ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይግባኙ ተቀባይነት በማጣቱ የተላለፈው የሞት ፍርድ እንዲፀና በመወሰኑ ተፈፃሚ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ይሁንና የሞት ፍርዱ ረቡዕ ዕለት ከመፈፀሙ በፊት ኤምባሲው ከዋናው እስር ቤት ኃላፊ ጋር በመነጋገር፣ የሀገሩ አሰራር በሚፈቅደው መሰረት፤ ፍርደኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ በመሆኗ የኑዛዜና የንስሐ ሥርአት እንዲፈፀምላት ማድረጉን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም፣ ቃል አቃባዩ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ በአጭር የሞባይል መልዕክት በማሳወቃቸው ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  የሃገሪቱን ልኡል ሼክ ፋይሠል አብዱላህ አልሳባህ ጨምሮ አንዲት የሃገሬው ዜጋ፣ 2 ግብፃውያን፣ 1 ባንግላዴሽና አንድ ፊሊፕኖ ሰው በመግደል፣ አስገድዶ በመድፈርና ሰው በመደብደብ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የተወሰነባቸው የሞት ፍርድ በስቅላት ተፈፃሚ ሆኖባቸዋል፡፡
የሃገሪቱ ልኡል በሞት እንዲቀጣ የተወሰነበት፣ የአጎቱን ልጅ በመግደልና ህገ ወጥ መሳሪያ ይዞ በመገኘት በሞት ሲቀጣ፤ ቀሪዎቹ ሰው በመግደልና አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ነው፣ በስቅላት እንዲቀጡ የተበየነባቸው፡፡
የሞት ፍርዱን መፈፀም ተከትሎ፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስዎች እና ሌሎች የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡
የፈሊፒንስ መንግስት በበኩሉ ዜጋውን ከቅጣቱ ለማዳን ሰፊ ጥረት ማድረጉን፣ ነገር ግን እንዳልተሳካላት አስታውቋል፡፡ በተያያዘ ዜና፣ ሁለት ዜጎቻቸውን በቅጣቱ ያጡት ባንግላዴሻውያን፣ ከትላንት በስቲያ የሟቾችን ፎቶ ግራፍ በመያዝ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው እንደነበር ተዘግቧል፡፡

Read 2962 times