Monday, 30 January 2017 00:00

ሼህ ኑሩ ይማምን ገድላችኋል የተባሉ ግለሰቦች እስከ 16 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(4 votes)

     ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 5 ሰዓት በደሴ ከተማ የሸዋ በር መስጅድ፣ የሀይማኖት አባት የሆኑት ሼህ ኑር ይማምን በሽጉጥ ገድላችኋል የተባሉት 13 ተከሳሾች፣ ከ3 ዓመት ከ8 ወር እስከ 16 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ፣ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ከትንትና በስቲያ ባስተላለፈው ቅጣት፣ ተከሳሾቹ እስላማዊ መንግስት ለመመስረትና አላማቸውን የማይደግፉ አካላት ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው የተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል ክስ፣ ፍ/ቤቱ ታህሣሥ 27 በዋለው የችሎት የጥፋተኝነት ብይን ተሰጥቶባቸዋል፡፡  ድርጊቱን በዋነኝነት ፈጽመሀል የተባለው 8ኛ ተከሳሽ ይመር ሁሴን፡- በ16 ዓመት ፅኑ እስራት ውሳኔ ሲተላለፍበት፣ 7ኛ ተከሳሽ ኡመር ሁሴን 15 ዓመት ከ 6 ወር፣ 1ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች አህመድ ኡመር፣ ሳህሊ መሀመድና ሼህ አደም አራጋው 15 ዓመት ፅኑ እስራት፤ 6ተኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ኢብራሂም ሙሴና ከማል ሁሴን በ14 ዓመት 2ኛ ተከሳሽ አንዋር ዑመር 12 ዓመት፣ 12ተኛ ተከሳሽ አብዱ ሀሰን 6 ዓመት፣ 10ኛ ተከሳሽ እስማኤል ሀሰን 5 ዓመት፤ 14ኛ ተከሳሽ መሀመድ ዮሴፍ አራት ዓመት ከ4 ወር እንዲሁም 13ኛ ተከሳሽ አህመድ ጀማል 3 ዓመት ከስምንት ወር ተፈርዶባቸዋል፡፡
በዚሁ ክስ 9ኛ ተከሳሽ ሆኖ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ሙባረክ ይመር፤ መከላከያ ምስክር ሲያሰማ ፍርድ ቤት ቆይቶ ሌሊት ላይ በደረሰበት ድንገተኛ ህመም ማረሚያ ቤት ውስጥ ጥር 05 ቀን 2008 መሞቱ ይታወሳል፡፡

Read 1589 times