Monday, 30 January 2017 00:00

ዶ/ር መረራ ለ3ኛ ጊዜ የ28 ቀን ቀጠሮ ተሰጠባቸው

Written by  ማህሌት ፋሲል
Rate this item
(7 votes)

የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
   አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ለ3ኛ ጊዜ አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ክስ ሳይመሰረትባቸው የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሲሆን የዋስትና ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከትላንትና በስቲያ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት የቀረቡት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ፖሊስ ተጨማሪ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለት፣ ለየካቲት 16 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡ የተከሳሹ ጠበቆች የዋስትና ጥያቄና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዳይሰጥ ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ እንዳደረገው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ፖሊስ ባለፉት 28 ቀናት ሰነዶችን እንዳሰባሰበ፤ ምስክሮችን እንዳናገረ እንደሁም የሽብር ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አግኝቶ እንዳናገረ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ከውጪ ኃይሎች ገንዘብ የተላከበትን ማስረጃ ከባንኮች እያጣራ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ፤ ሌሎች ቀሪ ምርመራዎች እንዳሉት በማመልከት፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን ጠይቋል፡፡
ዶ/ር መረራ፤ የአውሮፓ ህብረት ባዘጋጀው ኢትዮጵያን የተመለከተ ስብሰባ ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ በሽብር ከተፈረጁ ድርጅቶች አመራሮች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ከ3 ወር በፊት መታሰራቸው ይታወሳል፡፡



Read 3395 times