Monday, 30 January 2017 00:00

ለሊዮ ቶሎስቶይ የተጻፈ ደብዳቤ

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(7 votes)

(እውነተኛ የሰሙኑ ገጠመኝ)

አንድ ወዳጄ ከሳምንታት በፊት አንድ ቴአትር ይጽፍና በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት ቴአትር ቤቶች ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ ድርሰቱን ለግምገማ እንዲያስገባ ይነገረዋል፡፡ አስገባ፡፡ በቀደም ዕለት የግምገማውን ውጤት ለማየት ወደ ቤተ ተውኔቱ ያመራል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም “የግምገማው ውጤት ደርሷል፡፡ መታወቂያዎትን አሳይተው ፈርመው መውሰድ ይችላሉ” ይሉታል፡፡ ከደረት ኪሱ መዥለጥ አድርጎ መታወቂያውን ሰጣቸው። የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ መታወቂያውንና ደብዳቤውን አስተያየና “እርስዎ መውሰድ አይችሉም፤ መውሰድ የሚችለው ደራሲው ነው” ይሉታል፡፡ እርሱም ደረቱን ነፍቶ “የድርሰቱ ባለቤት እኔ ነኝና ልውሰድ” ይላል፡፡ መዝገብ ቤቶቹም “እዚህ ላይ የተጻፈው ግን የእርስዎ ስም ሳይሆን የደራሲው ስም ነው” ይሉታል፡፡ ግራ ገባው፡፡ እዚህ ቴአትር ቤት ይህንኑ ድርሰት ይዞ የመጣ ሌላ ደራሲ ይኖር ይሆን? ብሎ አሰበ። የትርጉም ሥራዎች አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች አንድን ሥራ ያውም በተመሳሳይ ጊዜ ተርጉመው ሊያቀርቡት ይችላሉ፡፡
“የተጻፈውን ደብዳቤ ማየት እችላለሁ” ይላል ወዳጄ፤ የተጻፈለትን ሰው ስም ለማየት ጓጉቶ፡፡
“መውሰድ አይችሉም እንጂ ማየትስ ይችላሉ” አለው፤ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ፡፡
ወዳጄ ወደ ማኅደሩ አንገቱን ልኮ ሲመለከተው ግን ክው ብሎ ነበር የቀረው፡፡
የወዳጄ የቴአትር ደርሰት የዝነኛው ሩሲያዊ ደራሲ የሊዮ ቶሎይስቶይ ድርሰት ነው፡፡ ወዳጄ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ነው ያቀረበው፡፡ በድርሰቱ ጽሑፍ ላይ “ደራሲ ሊዮ ቶሎይስቶይ፣ ተርጓሚ እገሌ” ይላል፡፡ አስደናቂው የቴአትር ቤቱ ደብዳቤ  “ለአቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ” ተብሎ ነው የተጻፈው። ለዚህ ነበር መዝገብ ቤቱ መስጠት የቸገረው። ወዳጄ መጀመሪያ ነደደው፣ ቀጥሎ ገረመው፣ በመጨረሻም ዞረበት፡፡ ለማረጋገጥም ፊርማና ማኅተሙን አየው፡፡
“ሊዮ ቶሎይስቶይኮ የለም” አለ ወዳጄ፤ የሚናገረው ነገር ግራ ገብቶት፡፡
“ታድያ አቶ ሊዮ ሲመጡ ይውሰዱ፣ ወይም እርስዎ ሕጋዊ ውክልና ይዘው ይምጡና ይውሰዱላቸው” አለ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ነገሩን ያቀለለ መስሎት፡፡
“ከማን ነው ውክልና የማመጣው” አለ ወዳጄ፤ የማሽላ ሳቅ ስቆ፡፡
የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ መነጽሩን አፍንጫው ላይ አስደግፎ መዝገቡን እያየ፤ “ከአቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ ነዋ፡፡ ዛሬ’ኮ ውክልና ቀላል ሆኗል፡፡ በ30 ደቂቃ ይጨርሱታል፡፡ ወጭ ሀገር ከሆኑም መላክ ይችላሉ” አለው፡፡
“ሊዮ ቶሎይስቶይን ታውቀዋለህ?” አለው፡፡
“እዚህ ቴአትር ቤት ድርሰት ይዞ የሚመጣው ብዙ ነው፡፡ ስንቱን ዐውቀዋለሁ ብለው ነው። በተለይ ጀማሪ ደራሲዎችን አናውቃቸውም፡፡ ጀማሪ ጸሐፊ ይሆን?” አለና በግማሽ መነጽሩ እያየ መለሰለት፡፡ እንዴት አድርጎ ሊያስረዳው ይችላል። ሊቃውንት ተብለው የተቀመጡት ኮሚቴዎች ያላወቁትን፣ ይህንን የመዝገብ ቤት ሹም ዕወቅ ማለት ግፍ ነው፡፡ ‹ድኃው ምን አረገ ሊቆቹን ነው መርገም› አለ ገሞራው፡፡
“ሊዮ ቶሎይስቶይኮ ሞቷል፡፡ እንዴት ነው ለሞተ ሰው ደብዳቤ የምትጽፉት?”
“ውይ፣ ውይ፣ ውይ” ብሎ የመዝገብ ቤቱ ሹም አዘነ፡፡ ባያውቀውም በባህሉ መሠረት ለሞተ ሰው ማዘን ያለ ነው፡፡
“መቼ ነው የሞቱት? አይ ሰው መሆን ቴአትራቸው ሳይታይላቸው፤ ትንሽ ቢሆን ገንዘብ ሳያገኙ፤ አይ ሰው፤ ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው” አለ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ አንገቱን እየነቀነቀ፡፡
“የሞተውማ በ1903 ዓም የዛሬ 106 ዓመት በኅዳር ወር ነው” አለው ወዳጄ፡፡ የመዝገብ ቤቱ ባልደረባ ግራ ገባው፡፡ እስከዛሬ የተገመገመ ድራማ ሲያስረክብ እንጂ ድራማ ሠርቶ አያውቅም፤ አሁን ግን ራሱ ድራማ እየሠራ መሰለው፡፡    
“አሁን የሚሉኝ ነገር እዚህ አንዳንዶች ጽፈው ከሚያመጡት የተሻለ ድራማ ይወጣዋል” አለና መዝገብ ቤቱ ሳቀ፡፡  
“እንዴት የሚገመግሙት ሰዎች ሊዮ ቶሎይስቶይን አያውቁትም? ለመሆኑ ምን ተምረው ነው ገምጋሚ የሆኑት፡፡ የድርሰት አብነቶችን ሳያውቁ ምኑን ነው የሚገመግሙት? በ1821 ዓም ራሽያ ተወልዶ፣ በ1903 ዓ.ም የሞተውን ታላቁን የድርሰት ሰው ቶሎይስቶይን የማያውቅ የድርሰት ገምጋሚ፣ ቴአትሮቻችንን ቢጥል ምን ይገርማል። ቴአትር የማያውቁ ሰዎች ቴአትር ከገመገሙ ቴአትር ሞቷል በለኛ፡፡”
የመዝገብ ቤት ባልደረባው አንገቱን እየነቀነቀ “ጌታው እኛ የታዘዝነው፣ አቶ ሊዮ ቶሎይስቶይ ለሚባሉ ሰው አስፈርማችሁ ስጡ ተብለን ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ ሞተዋል እያሉ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ከዐቅማችን በላይ ነው፡፡ አለቆቻችንን ያነጋግሩ” አለው፡፡
ወዳጄም እያዘነም፣ እየተበሳጨም፣ እየተገረመም መጣና ተረከልን፡፡
አንድ መምህሬ “ጥበብ በነጋድያን እጅ ስትወድቅ ሸቀጥ፣ በሹመኞች እጅ ስትወድቅ ቀልድ፣ በሆዳሞች እጅ ስትወድቅ ዳቦ፣ በምንደኞች እጅ ስትወድቅ የሥራ ልብስ፣ በዐዋቂዎች እጅ ስትወድቅ ዘውድ ትሆናለች” ይሉ ነበር፡፡ ጥበብን የማያፈቅራት ሰው እንኳን ሊገመግማት ሊያደንቃት አይችልም፡፡ ታዋቂው ባለቅኔ መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ቅኔ ተቀኝቶ ሲወርድ፣ እንኳን ቅኔ ሊያውቅ ቋንቋው ያልቀናለት ሹም ያገኘውና ‹ይበል ነው› ይለዋል። መጋቤ ምሥጢርም “አንተ ከሰማኸውማ ምኑን ቅኔ ተቀኘሁት” አለ አሉ። ጥበብ መጀመሪያ ፍላጎት፣ ከዚያም ዕውቀት፣ ቀጥሎም ተመስጦ፣ በመጨረሻም አንክሮ ትሻለች። ጥበብን የተማረ ሁሉ አይደርስባትም፡፡ ‹አይቴ ብሔራ ለጥበብ - የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው› እያለ የሚፈልጋት እንጂ፡፡ ጥበብን የተሾመባት ሁሉ አያውቃትም፡፡ ‹ወበአይቴ ተረክበ አሠረ ፍኖታ - የጎዳናዋ ፍለጋ በወዴት ተገኘ› ብሎ የሚመረምራት እንጂ፡፡ ጥበብን ባለ ገንዘብ አይገዛትም፤ ‹መኑ ዐደወ ባሕረ ወተሣየጣ በወርቅ ቀይሕ - ባሕሩን ተሻግሮ በቀይ ወርቅ የገዛት ማነው?› እያለ በአንክሮ የሚከተላት እንጂ፡፡ ጥበብን ምንደኛ ቅጥረኛ አይደርስባትም፣ ‹ወመኑ ዐርገ መልዕልተ ደመናት ወአውረዳ - ከደመናት በላይ ወጥቶ ያወረዳት ማነው?› እያለ የሚመሰጥ እንጂ፡፡
የንጉሡ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ አማች ደጃዝማች ካሣ፣ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ይሾማሉ፡፡ ዕውቀት በሹመት ይገኝ ይመስል፣ ደጃዝማቹ በዩኒቨርሲቲ በር እንኳን ሳያልፉ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ሕዝቡን አስደነቀው፡፡ በዚህ ጊዜ፡-
ላም እሳት ወለደች
ወንፊት ውኃ ቀዳ
ሺ ግመል አለፈ በመርፌ ቀዳዳ
በሰንበሌጥ ቁጣ ወደቀ አሉ ዋርካ
ተከካ አልተከካ
ተቦካ አልተቦካ
ተሳካ አልተሳካ
የምንቸገረኝ ቤት ሁል ጊዜ ፋሲካ
በትእዛዝ ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ፡፡
 ተብሎ ተገጠመ ይባላል፡፡
አንዱ ጓደኛችንም ተርጓሚውን እንዲህ አለው፤ “ለምን ‹ለቶልስቶይ፣ ባለበት› ብለህ ደብዳቤ አትጽፍለትም፡፡
ይድረስ ለሊዮ ቶሎይስቶይ፡፡ ይኼው ከስምንተኛው ሺ መድረሳችን ታወቀ፡፡ ለዕውቀት ያልደረሱ፣ ለመብል ያላነሡ፣ በትእዛዝ ሊቅ፣ በድጋፍ ምሩቅ የሆኑ፣ አበል የሚሰበስባቸው፣ ጥበብ የማይገዳቸው የሀገሬ ሹማምንት መፈጠርህንም፣ መሞትህንም ሳያውቁ፤ በሞትክ በመቶ ስድስት ዓመትህ ከመዝገብ ቤት መጥተህ ደብዳቤ እንድትወስድ ጽፈውልሃል፡፡ ክቻልክ የገነትን ጠባቂ መልአክ አስፈቅደህ ናና፣ ደብዳቤህን ፈርመህ ውሰድ፡፡ ምናልባት የቀበሌ መታወቂያ ይቸግርህ ከሆነ፣ ምርጫ ሲደርስ ከመጣህ ማውጣቱ ይቀልሃል፡፡ የቤት ምዝገባ ሰሞን ግን እንዳትመጣ፡፡ አሳዛኙ ነገር ከ70 ዓመት በፊት ጽፈኸው ዓለምን ጉድ ያሰኘህበት ድርሰትህ፣ በቴአትር ቤታችን ገምጋሚ ኮሚቴ፣ ከልማታዊነትና ከሕዝባዊ ከብሔር ብሔረሰቦች መብት አንጻር ማረሚያ ስለተሰጠው፣ እርሱን አስተካክለህ እንደገና ለማሳተም መሬት ላይ መቆየት የግድ ሊሆንብህ ነው፡፡ ያውም ድርሰትህ የኋላ ዘመን መሆኑ ከታወቀ፣ የነፍጠኛና የጉልተኛ ድርሰት ነው ከመባል ከተረፈልህ ነው፡፡ ስትመጣ ስሙን እንጂ ድርሰቱን ብዙም ለማናውቀው የሀገርህ ሰው ለፑሽኪን ያሠራንለትን አደባባይ ትጎበኛለህ፡፡”   

Read 3866 times