Monday, 30 January 2017 00:00

እንዴት ተጠነሰሰ? ዛሬ የት ደረሰ?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

“አገር በቀል የልብ ልዕለ ህክምና የሚሰጥ ቡድን እያዋቀርን ነው”

በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል የማቋቋም ሀሳብ የተጠነሰሰው የዛሬ 40 ዓመት ገደማ በ1970 ዓ.ም በአሜሪካ ነው፡፡ በልብ ህክምና ሙያ ለመሰልጠን (ስፔሻላይዝድ ለማድረግ) በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁበትን የትምህርት ማስረጃና የወደፊት ፍላጎታቸውን የሚገልጽ ሀሳብ ለኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ ያቀርባሉ፡፡
ቃለ-መጠይቅ ያደረጉላቸው ፕሮፌሰር ኢጂኒ ዶይል፤ “የምንቀበለው 10 ሰዎችን ነው፡፡ አንተ የተቀመጥከው 10ኛ ላይ ነው፡፡ ባቀረብከው ማመልከቻ ውስጥ ጥሩና ደስ የሚሉ ነገሮች አይቻለሁ፡፡ ስላቀድካቸው ነገሮች ከአንደበትህ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ እውነት ትምህርትህን ስትጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ፣ በልብ ህክምና ትሰራለህ?” በማለት ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም “አዎ!” በማለት መለሱ፡፡
ፕሮፌሰሯም፣ “ኢትዮጵያ ተመልሰህ የልብ ሆስፒታል በሌለበት፣ መሳሪያ በሌለበት፣ ባለሙያ በሌለበት፣ እንዴት ነው የልብ ህክምና እሰራለሁ የምትለው?” ሲሉ ደግመው ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም፤ “መላ እፈልጋለሁ - I will find a way” ሲሉ መለሱ፡፡
እቤት ሲመለሱ ፊታቸው ላይ የመከፋትና የኀዘን ስሜት ይነበብ ስለነበር ባለቤታቸው፤ “ምነው ተከፋህ? አልተቀበሉህም እንዴ?” በማለት ጠየቋቸው፡፡ “መቀበሉንስ ተቀብለውኛል፡፡ ነገር ግን አራት ነገሮች አርግዤ መጣሁ” አሏቸው፤ ዶ/ር በላይ አበጋዝ፡፡
 የፀነሷቸው አራት ነገሮችም፡- የልብ ሆስፒታል መገንባት፣ ውድና ልዩ የሆኑትን የልብ ህክምና መሳሪያዎች ማሟላት፣ የሰው ኃይል (ካርዲዮሎጂስት) ማፍራትና ሆስፒታሉ በገንዘብ አቅም ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ናቸው፡፡ ይዘግይ እንጂ የዶ/ር በላይ አበጋዝ ራዕይ እውን ሆኗል፡፡ ሆስፒታሉ፣ በኢትዮጵያ ህዝብና በሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲ ትብብርና ድጋፍ ተሰርቶ በ2001 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ ውድ የሆኑት ዘመናዊ የልብ ቀዶ ህክምና መሳሪያዎች፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ በሆነው “ቼይን ኦፍ ሆፕ ዩኬ” ተሟልቷል፡፡ የልብ ቀዶ ሀኪሞች (ካርዲዮሎጂስቶች) የሚኒያፖሊስ የልብ ቀዶ ሀኪም በሆኑት በዶ/ር ቪብ ክሸንትና ታዋቂ በሆነው የህንድ ናርያና ሆስፒታል ሰልጥነዋል፡፡ የአገልግሎቱን ቀጣይነትም ለማረጋገጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከሊዝ ነፃ በሰጠው ቦታ ላይ የሚከራዩ ህንፃዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ዶ/ር በላይ፣ የቆየ እርግዝናቸውን ተገላገሉ ማለት ይቻላል፡፡
አቶ ሕሩይ ዓሊ፤ የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ዳይሬክተር፣ የሆስፒታሉ አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ ሕሩይ፣ ስለ ልብ ማዕከሉ አመሰራረት፣ እስካሁን ምን ተግባራት እንዳከናወነ፣ አሁን ስላለበት ደረጃ፣… የነገሩኝን ላጫውታችሁ፡፡
በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማኅበር ከተመሰረተ የቆየ ቢሆንም፣ ህጋዊ ፈቃድ ያገኘው ዶ/ር በላይ ከአሜሪካ ከተመለሱ ከ6 ዓመት በኋላ ነው፡፡ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከሉ ስራ የጀመረው ህጋዊ እውቅና ሳያገኝ በፊት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ውስጥ ዶ/ር በላይ በግላቸው ከውጭ አገራት ጋር እየተነጋገሩ፣ 108 ህፃናት ልከው አሳክመዋል፡፡ ማኅበሩ ፈቃድ እንዳገኘ፣ ልዕልት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ነው፣ ኮንቴይነር ገጣጥምና አራት ሰዎች ይዞ ስራ የጀመረው፡፡ በዚያን ጊዜ ዶ/ር በላይ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ይሰሩ ነበር፡፡ በትርፍ ሰዓታቸው ወደ ማዕከሉ እየመጡ በሀኪምነት ይሰራሉ፡፡ የቀሩት ሶስቱ ሰዎች ነርሷ፣ ጸሐፊዋና የጥበቃ ሰራተኛው እንደነበሩ ገልጻለች - በማዕከሉ ለ26 ዓመታት የሰራችው ሲስተር ሰላምነሽ ወ/ማርያም፡፡
ማኅበሩ፣ ኮንቴይነር ውስጥ ሆኖ 2300 ህፃናት ወደተለያዩ አገሮች (በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች፣ አውሮፓ፣ እስራኤል) እየላከ ያሳከመ ሲሆን እዚያው ኮንቴይነር ውስጥ እያለ፣ የልብ ኦፕራሲዮን ማድረጊያ መሳሪያዎች ከውጭ በዕርዳታ ስላገኘ፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል ውስጥ 300 ህፃናት ኦፕራሲዮን መደረጋቸውን፣ አዲሱ የልብ ህክምና ሆስፒታል ከተመረቀበት ዕለት አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ2500 በላይ ህፃናት በሆስፒታሉ ኦፕራሲዮን መደረጋቸውንና ህይወታቸው መለወጡን አቶ ሕሩይ ተናግረዋል፡፡
“የመጀመሪያው እርግዝና ሆስፒታሉን መስራት ነበር፡፡ ለዚህም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች (አንድ ብር ለአንድ ልብ፣ ቶምቦላ) ተዘጋጅተው ነበር፡፡ “አንድ ብር ለአንድ ልብ”፣ ድርጅቱ፣ እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚዘልቅ መዋቅር ስላልነበረው ስኬታማ አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በመጨረሻ ዕድል ከእኛ ጋር ስለነበረች ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርገው፣ ሆስፒታሉ እውን ሊሆን ችሏል ብለዋል፡፡ ሁለተኛው እርግዝና፣ ኦፕራሲዮን ማድረጊያ መሳሪያዎች እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ሕሩይ፤ “እነሱም ውጭ አገር ባሉ ተባባሪ ድርጅቶቻችን አማካይነት ተሟልተዋል። ይህ ሆስፒታል አሁን ሁለት የኦፕራሲዮን (ኦአር) ክፍል፣ ሁለት የልብ ችግሮች በጨረር መፍትሄ የሚያገኙበት ክፍል፣ 10 የፅኑ  ህሙማን ማገገሚያና መከታተያ (አይሲ) አልጋዎች፣ ዋርድ ላይ ደግሞ 15 አልጋዎች አሉት፡፡ ሁለተኛው እርግዝና ተሟላ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ እግርዝናዎች (ሆስፒታሉን መገንባትና መሳሪያዎችን ማሟላት) ናቸው፤ረዥም ጊዜ የፈጁት” በማለት አብራርተዋል፡፡
“ሶስተኛው እርግዝና፤ የሰው ኃይል ማሟላት፣ የልብ ኦፕራሲዮን አድራጊ (ካርዲዮሎጂስቶች) ማፍራት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የልብ ህክምና አዲስ ጅምር በመሆኑ፣ በአገር ውስጥ በቂ የልብ ህክምና አድራጊዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ውጭ አገር ልከው ሀኪሞችን ማሰልጠን ነበረባቸው፡፡ “የትኛው አገር ጥራት ያለውና ስልጠና እንደሚሰጥና የተሻለ እንደሆነ ጥናት ተደርጎበት፣ ሰልጣኝ ሀኪሞችን በመምረጥ የጤና ጥበቃ ድጋፍ ተደርጎበት፣ በአሁኑ ወቅት ሁለት የአዋቂ፣ አራት የህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና አድራጊ ሀኪሞች፣ ሁለት ሰመመን ሰጪዎች፣ ሁለት ፐርፊዩዢኒስቶች (ልብ ኦፕራሲዮን ሲደረግ ልብና ሳንባ እንዲቆሙ ተደርገው ተግባራቸውን የሚፈጽመው መሳሪያ ነው፡፡ ፐርፊዩዢኒስቶች መሳሪያውን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ናቸው)፣ አንድ የአይሲ ዶክተር አለን፡፡ ከአራት ወር በኋላ ለሦስት ዓመት ስልጠና የተላኩ ሀኪሞች ይመጣሉ። ያን ጊዜ የተሟላ አገር በቀል ባለሙያዎች አሉን ማለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አራተኛው እርግዝና፤ የሆስፒታሉን አገልግሎት ዘላቂነትና ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው፡፡ “እኛ ለምንሰጠው አገልግሎት ገንዘብ አናስከፍልም፡፡ የካርድ እንኳ የሚባል ነገር የለም፡፡ የልብ ኦፕራሲዮን በነፃ ነው፤ ለታካሚዎች ምግብ የምናቀርበው ከራሳችን ነው፡፡ የምንሰጠው የህክምና አገልግሎት ዝቅተኛ ዋጋ ያስከፍላሉ ከሚባሉ ሆስፒታሎችና አገራት ጋር ቢነፃፀር፣ ከመጀመሪያ አንስቶ እስካሁን የሰጠነው አገልግሎት 1.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ይህ ሆስፒታል ከተሰራ በኋላ ደግሞ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት በነፃ ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ ይህ በነፃ የሚሰጡት አገልግሎት ከውጭ አገር ተለምኖ በሚገኝ ገንዘብ እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ “ይህን ትልቅ ገንዘብ ሁልጊዜ በልመና ማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን ዘላቂነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ ገንዘብ የምናገኝበትን መንገድ ማመቻቸት የግድ ይላል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ብስራተ ገብርኤል አካባቢ፣ ከሊዝ ነፃ በሰጠን ቦታ ላይ ፕሮጀክት ነድፈን፣ እያንዳንዳቸው G-5 የሆኑ 3 ህንፃዎች መገንባት ጀመርን፡፡ የህንፃዎቹ ጠቅላላ ግምት ከ60-65 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ሁለቱ ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል፡፡ አንዱ ግንባታው አልቋል፡፡ የማጠቃለያ (ፊኒሽንግ) ሥራ ይቀረዋል፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች ተጠናቀው ሲከራዩ፣ ከ80-90 በመቶ ዓመታዊ በጀታችንን ይችልልናል። በአሁን ወቅት ከውጭ ዕርዳታ የምናገኝ ከሆነ፣ መሳሪያ እንዲገዙልን ነው የምናደርገው፡፡ መንግስት እያደረገልን ያለው ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ነው። አየር መንገድ ከድሮ ጀምሮ ለህፃናቱ ነፃ ቲኬት በመስጠት፣ ጤና ጥበቃ ሚ/ር የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚ/ር በዕርዳታ የምናገኘውን መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንድናስገባ በመፍቀድ…. እያደረጉልን ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት አመሰግናለሁ” ብለዋል - አቶ ሕሩይ፡፡
ሆስፒታሉ አገልግሎት እንዲሰጥ የታሰበው ለሕፃናት የልብ ሕሙማን ነው፡፡ አሁን ግን ለአዋቂዎችም አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሆስፒታሉ ሲመረቅ የተፈጠረ እንደሆነ አቶ ሕሩይ ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹በወቅቱ በአገሪቱ የአዋቂም ሆነ የህፃናት ልብ ሕክምና የሚሰጥ ተቋም አልነበረም። ኢትዮጵያ ደግሞ የትላልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ከተማ ነች፡፡ ሆስፒታሉ ሲመረቅ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ አገሪቷ የአዋቂ የልብ ሕክምና መስጫ የላትም፤ እስኪሠራ ድረስ ማድረግ የምትችሉት ነገር ካለ? በማለት ለዶ/ር በላይ አበጋዝ ለቦርድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ዶ/ር በላይ፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ ቦርድ መወሰን አይችልም፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤው ይቅረብ›› አሉ፡፡ ጥያቄው ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቦ፣ ከሆስፒታሉ አልጋና ሀብት 25 በመቶ ለአዋቂዎች፣ 75 በመቶ ለሕፃናት እንዲሆን ተወሰነ፡፡
አሁን ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ እየሠራ አይደለም፡፡ አንዱ ምክንያት የሰው ኃይል ያለመሟላት ነው፡፡ ይህ ችግር ውጭ አገር እየተማሩ ያሉ ሐኪሞች ከ4 ወር በኋላ ሲመጡ ይወገዳል። ትልቁ ችግር መድኃኒቶችንና አላቂ ዕቃዎችን፣ (“ፋርማስቲካል ኮንስዩምኤብልስ” የሚባሉትን) አገር ውስጥ ማግኘት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል፣ በ4 ሠራተኞች ጀምሮ በአሁን ወቅት፣ ላቦራቶሪ ቴክኒሻን፣ ራዲዮግራፈር፣ ሜዲካል ኢንጂነር …ሳይጨምር በአጠቃላይ 11 የልብ ሐኪሞች (ካርዲዮሎጂስት)፣ 51 ነርሶችና ከድጋፍ ሰጪዎች ጋር 116 ሠራተኞች አሉት፡፡
በአገር ደረጃ የሌለ ተቋም ለመመስረት የረዥም ጊዜ ራዕይ ሰንቀው፣ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ሆስፒታል ለማቋቋም፣ የዕድሜያቸውን እኩሌታ ያህል ሲሰሩና ሲደክሙ ስለቆዩት ዶ/ር በላይ አበጋዝ፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው ምን ይላሉ?
ሁሉም ያነጋገርኳቸው ሰዎች ስለ ዶ/ር በላይ ለማውሳት አቅሙና ችሎታው እንደሌላቸው ነው የሚገልጹት፡፡  አቶ ሕሩይ ሲናገሩ፤ ‹‹ዶ/ር በላይ፣ ከሠራተኛ በፊት ቀድመው ይገባሉ፡፡ ከሠራተኛ በኋላ ይወጣሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹን 4 እና 5 ዓመታት ከዚህ የሚወጡት ከምሽቱ አራትና አምስት ሰዓት ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ደሞዝ አንከፍላቸውም፣ ለሥራ እየነዱ ለሚመጡበት መኪና አንድም ቀን ነዳጅ ሞልተን አናውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ፈረንጆች ለስራ ጉዳይ ሲመጡ፣ የገንዘብ ችግር ስለነበረብን ከኪሳቸው ነበር የሚጋብዙት፡፡
“ሆስፒታል ከተገነባ በኋላ ሐኪሞች አውሮፓ አሜሪካ አያውቁም ነበር፡፡ እሳቸው ሄደው፣ ሰዎች አናግረው፣ ተልዕኮ አዘጋጅተውና ቃል አስገብተው ሲመጡ ድርጅቱ የአውሮፕላን አይከፍላቸውም ነበር፡፡ ሆስፒታሉን እራሳቸው ፀንሰው፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብና ከሼህ መሐመድ ሁሴን ጋር የወለዱት ስለሆነ፣ ከአብራካቸው ከተወለዱት ሁለት ልጆቻቸው ለይተው የሚያዩት አይመስለኝም፡፡”
የሕፃናት ሐኪም የሆነው ዶ/ር ዓሊ ዓውድ፣ “ያለ ዶ/ር በላይ ያላሰለሰ ጥረትና ድካም የዚህ ሆስፒታል ግንባታ እውን አይሆንም ነበር” ይላል፡፡ ዶ/ር ዓሊ፤ ሆስፒታሉን ከተቀላቀለ አራት ዓመት እንደሆነው ተናግሯል፡፡ ሦስቱን ዓመት በህንድ፣ ባንግሎር የልብ ሕክምና ማዕከል ሲማር፣ አንዱን ዓመት በሆስፒታሉ ሲሰራ መቆየቱን አስረድቷል፡፡ ‹‹ይህ ሆስፒታል በዶ/ር በላይ ተነሳሽነትና አስተባባሪነት በኢትዮጵያ ሕዝብ የተሠራ ነው፡፡ የልብ ሕክምና ማዕከሉ በአገሪቱ የመጀመሪያው ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር በላይ አበጋዝ፤ ይህን በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የልብ ሕክምና ውድ ነው፡፡ በትንሹ ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር የሚያስከፍል ነው፤ እስከ ሚሊዮን ብርም ይደርሳል፡፡ በገንዘብ አቅም ማነስ ውጭ አገር ሄደው መታከም ለማይችሉ ህፃናት፤ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ህክምና በአገር ውስጥ እንዲካሄድ ፈር ቀዳጅ ስለሆኑ ከልብ ሊመሰገኑ ይገባል ባይ ነኝ›› ብሏል፡፡
ዶ/ር መሐመድ በድሩ፤ በሆስፒታሉ የአዋቂ የልብ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም ነው፡፡ ይህ ሆስፒታል የሚሰጠው አገልግሎት ከሌሎች ሆስፒታሎች የተለየና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሕክምና እንደሆነ የጠቀሰው ዶ/ር መሐመድ፤ አንደኛ የልብ ቀዶ ሕክምና ሲሆን ሁለተኛው ኢንተርቬንሽን የሚባለው ነው፡፡ ኢንተርቬንሽን ማለት የልብን ደም ስሮች መከፈትም ሆነ መዘጋት ወይም የተለያዩ የልብ ችግሮችን፣ ልብ ሳይከፈት ያለ ቀዶ ሕክምና የማከም ዘዴ ነው፡፡ የልብ ኦፕሬሽን እንሠራለን፡፡ ኦፕሬሽኑን የምንሠራው እንደ ኢንተርቬንሽኑ ሁልጊዜ አይደለም። ተልዕኮ አዘል ነው፡፡ ተልዕኮ አዘል በቀጠሮ፣ በዓመት ሦስት ወይም አራት ጊዜ ከሌሎች አገሮች ከሚመጡ ሐኪሞች ጋር በመቀናጀት፣ በተፈጥሮ የሚከሰት ወይም ከጊዜ በኋላ የሚመጣ ችግሮችን እየቀረፍን ነው ብሏል፡፡
ዶ/ር መሐመድ ስለ ሆስፒታሉ መሥራች ሲናገር፡- ‹‹ስለ ዶ/ር በላይ መናገር ይከብዳል። ከአሜሪካ ሲመለሱ በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ለማቋቋም አስበውና ቆርጠው የተነሱ ሰው ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናቸው የሆስፒታሉ ግንባታ እውን ሆኖ በማየታቸው ሀውልታቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ በልብ ሕክምና ሆስፒታሉ ውስጥ ከመሥራትና በመሳሪያ ከማሟላት በተጨማሪ የሰው ኃይሉን ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ እሳቸው ናቸው ት/ቤቱንና በጀቱን በማፈላለግ እንድንማር ያደረጉን፡፡ አሁን በሆስፒታሉ የሚሰራበት ሲስተም እሳቸው የፈጠሩት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እሳቸው የሚሰሩትን መስራት ሳይሆን ማሰቡም ይከብዳል። በሕይወታቸው ካሰቡት በላይ የተሳካላቸው ሰው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ሆስፒታሉ፣ መሳሪያውና የሰው ኃይሉ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ማነቆ ሆኖ በሙሉ አቅማችን እንዳንሠራ ያገደን “ኮንሱዩመብልስ” የሚባሉት አላቂ ዕቃዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ከተወገዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ የልብ ሕክምና አገልግሎት ያገኛል ብዬ አምናለሁ›› ሲል አጠቃሏል፡፡
ሲስተር ሰላምነሽ ወ/ማርያም የሥራ ዕድሜዋን ያሳለፈችው ከዶ/ር በላይ ጋር በመሥራት ነው፡፡ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃው፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በኮንቴይነር ቢሮ ሲሰራ፣ ሲስተር ሰላምነሽ በ1983 ዓ.ም ተቀጠረች፡፡ ከአራቱ መሥራቶች አንዷ ነች፡፡ ሕፃናትን ወደተለያዩ አገራት ይዛ በመሄድ አሳክማለች፡፡ የአንድ ጊዜ ገጠመኟ ይገርማል፡፡ የ3 ወር ጨቅላ ልጇን እቤት ጥላ፣ የሚታከሙ ህፃናትን ይዛ ሄደች፡፡ ታክመው የዳኑትን ወደ አገር ቤት እየላከች፣ አዲስ የሚታከሙ ህፃናትን እየተቀበለች፣ አንድ ዓመት ከ10 ቀን በእስራኤል ቆይታ፣ 56 ሕፃናትን ማሳከሟን ገልፃለች፡፡
ዶ/ር በላይ አበጋዝ፡- ጠንካራ ሠራተኛ፣ ሩህሩህና ሐቀኛ መሆናቸውን ሰላምነሽ ትናገራለች። ሐቀኝነታቸው ስትገልፅም፤ ዶ/ር በላይ፤ ስለ ሕፃናቱ ሕክምና ከውጭ አገር ሆስፒታሎች ጋር የተነጋገሩበትን የስልክ ሂሳብ ከኪሳቸው ነው የሚከፍሉት፡፡ ታክስ ያልተከፈለበት ደረሰኝ (ቢል) ሲመጣላቸው፣ ታክሱ ልምን አልተጨመረበትም? በማለት ተቆጥተው፣ ታክሱን እንደሚከፍሉ ገልጻለች፡፡

Read 2509 times