Monday, 30 January 2017 00:00

ድርድር ወይስ ውይይት?

Written by  ያሬድ ከፍያለው
Rate this item
(1 Vote)

የአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ለተቃዋሚዎች (እኔ “አማራጭ የፖለቲካ ሀይሎች” ማለቱን እመርጣለሁ) ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ብዙዎች ይስማማሉ። አማራጭ ኃይሎቹ  በተለያዩ መድረኮች ምህዳሩ እንዲሰፋ ገዥውን ፓርቲ ሲማጸኑ ቆይተዋል፤ በምህዳሩ መጥበብ ሳቢያ ሊከተሉ  የሚችሉ ችግሮችን በመጥቀስም ጭምር።  እንደ ብዙዎቹ እምነት፣ ገዥው ፓርቲ ለረጅም ጊዜያት  ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ቁርጠኝነት  ባለማሳየቱ፣ በየደረጃው የሚገኙ ደጋፊዎቹ አማራጭ ኃይሎችን ሲያዋክቡ ቆይተዋል።  በቅርቡ ግን ገዥው ፓርቲ ከአማራጭ  ኃይሎች ጋር ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ ለማዘጋጀት መወሰኑ በብዙዎች ዘንድ ተስፋን ፈንጥቋል። አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎቹ ለመገናኛ ብዙኃን (አዲስ አድማስ ጥር 13 ቀን 2009 እትምን ጨምሮ)  በሰጡት መግለጫ፤ በገዥው ፓርቲ በኩል ቅንነቱ ካለ መድረኩ የፖለቲካ ምህዳሩን  የሚያሻሽሉ ስምምነቶች ይደረሱበታል የሚል ተስፋ አላቸው። አንዳንዶቹ መድረኩ የድርድር መንፈስ እንዲኖረው ሲፈልጉ፣ ሌሎች  ደግሞ  በቅድሚያ ከገዥው ፓርቲ ጋር  በቅድመ ሁኔታዎች ላይ መግባባት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።  
የመድረኩ ይዘት የውይይት ይሁን የድርድር ገና የተለየ አይመስለኝም። ሆኖም የሁለቱ (ውይይት እና ድርድር) መሰረታዊ ይዘታቸው የሚታወቅ በመሆኑ ለውጤታማነታቸው አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን መናገር የሚከብድ አይሆንም።  በእኔ እምነት ውይይት ሰጥቶ መቀበልን  የማይጠይቅ በመሆኑ የመሳካት እድሉ ሰፊ ነው። ድርድር ግን  በባህሪው ሰጥቶ መቀበልን ይፈልጋል። ለድርድር ገዥውም ሆነ አማራጭ ኃይሎች የሚቀበሉትና የሚሰጡት  መሰረታዊ ነገር ያስፈልጋቸዋል። 
የመድረኩ ይዘት የድርድር ከሆነ ኢህአዴግ አይሸራረፉም ብሎ  ደጋፊና ታማኝ አባሎቹን እስከማጣት የደረሰባቸው የፖለቲካ ባህል፣ አሰራር፣ አላማዎቹንና ግቦቹን ለድርድር ማቅረብን ሊጠይቀውም ይችላል። ከተሳካ  ለተቃዋሚ ኃይሎች ትልቅ ድል ይሆናል። ነገር ግን መነሳት ያለበት ጥያቄ አለ፤ የድርድር እድል ሊኖር ይችላልን? የሚል። በእኔ እምነት የድርድር መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ስለሌሉ የድርድር እድሉ ዜሮ ነው።  መግባባት ካለ የሚሆነው ኢህአዴግ ቅንነቱ አይሎ አሊያም በአርቆ አሳቢነት ምህዳሩን ለማስተካከል ምክር ይጠይቃል፤ አማራጭ ኃይሎቹ የምህዳሩን ውስንነቶች ይዘረዝራሉ፤ ምክክሮችም ይደረጋሉ። በዚህም መሰረት ገዥው ፓርቲ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት አስገብቶ በፓርቲ ደረጃ የተስማማባቸውን እርምጃዎች ይወስዳል። 
በዚህ መነሻነት አማራጭ ሃይሎቹ ሊያቀርቡዋቸው የሚገቡ የሚሻሻሉ  የአሰራር፣ የህግና የተቋማዊ አደረጃጀት ጉዳዮችን ለማየት እንሞክራለን።
የመጀመሪያ መሆን ያለበት ገዥው ፓርቲ፤ “ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ብቸኛ ሀዋርያ ነው” በሚለው እምነትና አሰራር ምትክ፣ “አማራጭ ሃይሎች ለሃገሪቷ እድገት ጉልበት ናቸው” ወደሚል እምነት መሸጋገሩ ላይ እራሱም ሆነ አማራጭ ሀይሎቹ እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ለውጡን እውን ለማድረግም የሚወሰዱ ዝርዝር እርምጃዎች ሊቀመጡ ይገባል። ለውጡን  ለመለካት እንዲቻልም  ሊመዘኑ የሚችሉ መለኪያዎች መድረኩ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ የውጤቱ መዛኝ አካልና የምዘናው ወቅትም ከወዲሁ ስምምነት ሊደረስበት ያስፈልጋል። ይህም ከዚህ በፊት ሲታዩ የቆዩ «ምህዳሩን አስፍቻለሁ» የሚለው የገዥው ፓርቲ  መግለጫና  «ስቃይ ላይ ነን» የሚለው የአማራጭ ሃይሎች አቤቱታ፣ በመረጃ ላይ ብቻ  እንዲመረኮዝ ያግዛል። ምናልባት ከተከሰተ ማለት ነው።
ሌላው የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የእምነት ማህበራት ከተጽዕኖ ውጭ እንዲመሰረቱና እንዲተዳደሩ፣ ከወከባና ጫና ነጻ እንዲሆኑም  ማድረግ ሊሆን ይገባል። የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የሰራተኞች፣ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግድ፣ የሰብአዊ መብት፣ የእምነት፡ የባህል ማህበራትና ሌሎችም ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው እንዲቋቋሙና እንዲተዳደሩ ማድረግ ላይ መነጋገር ይጠበቅባቸዋል። በተመሳሳይ ለውጡን  መገምገም እንዲቻል  ሊመዘኑ የሚችሉ መለኪያዎች በሚለኩበት ጊዜ ጭምር  ሊቀመጡ ይገባል። መዛኙ አካልም ከወዲሁ ስምምነት ሊደረስበት ይገባል።
የፖለቲካ አመለካከት ከሃገር ወገናዊነት በታች ስፍራ እንዲኖረው የሚያደርግ የፖለቲካ  ባህል እንዲዳብር መስራት ሌላው ይሆናል። ለምሳሌ በመንግስት ተቋማት የሚኖር ቅጥር፣ እድገት፣ ሹመት፣ የትምህርትና ስልጠና እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ብቃትና ዜግነትን ብቻ ያማከለ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ነው።  የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች የማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን እንዲችሉ፣ ካልፈለጉም በሃገራቸው ፍሬዎችና እድሎች የመጠቀም እኩል መብት ያላቸው  መሆኑ ላይ ገዥው ፓርቲ በእምነትም ሆነ በአሰራር ቁርጠኝነት እንዲያሳይ የሚያደርጉ እርምጃዎች ላይ ጠንካራ ውይይት ሊደረግ ይገባል።  የሚጠበቁ ውጤቶችም ሊለኩ በሚችል መልኩ ሊቀመጡ  ያስፈልጋል። በተመሳሳይ ለውጡ ሊመዘንባቸው የሚያስችሉ የህግና የአሰራር መለኪያዎች በጊዜ ሰሌዳ መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡  
ምርጫ ቦርድ በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ላይ ካለው ወሳኝነት አንጻር የቦርዱ አባላት አሰያየም፣ የጽ/ቤቱ  አደረጃጀት፣ የሃላፊዎችና ሰራተኞች ቅጥር  ሌላው  የውይይት ርዕስ ሊሆን የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ተመሳሳይ ለውጡን  ለመገምገም እንዲቻል  ሊመዘኑ የሚችሉ መለኪያዎች ሊበጁ ያስፈልጋል። መዛኙ አካልና የምዘናው ወቅትም እንዲሁ።
በፍትህ ስርዓቱ ነጻነት ላይ በሚታዩ ጉድለቶች ዙሪያ በተመሳሳይ ውይይት ያስፈልጋል። ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ በሃገራችን የተለመደው ገዥ ፓርቲ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ያለው ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት በሃገሪቱ ውስጥ ለሚታዩ ብዙ ችግሮች መንስኤ በመሆኑ መለያ ሊበጅለት ያስፈልጋል። የመንግስት ተቋማትም  የተጣለባቸውን ሃላፊነት ከመወጣት ውጭ ገዢ ፓርቲውንና የፓርቲ አመራሮችን ዘላለማዊነት ለማጽናት  መትጋታቸውን እንዲያቆሙ መደረግ አለበት። በመከላከያና በጸጥታ አካላት ዙሪያም ውይይቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል።   እዚህ ላይ የሌሎች ሃገራት ተመክሮ ቀርቦ  ሊመከርበት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የፍትህና የጸጥታ ኃይሎች፣ ስልጣን ላይ ላለው ገዥ ፓርቲ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ወደ መንግስትና ህዝብ አገልጋይነት  ይሸጋገራሉ።

Read 1457 times