Monday, 30 January 2017 00:00

በ12 ወራት 90 ሺህ ናይጀሪያውያን ህጻናት ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አለማቀፉ ማህበረሰብ እየጨመረ ለመጣው የናይጀሪያ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 90 ሺህ ያህል የአገሪቱ ህጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡
በአገሪቱ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ተገቢውን ድጋፍ ባለማግኘት በአለማቀፍ ደረጃ ቀዳሚው እንደሆነ ያስታወቀው ተቋሙ፤አሸባሪው ቡድን ቦኮ ሃራም ከሚያደርሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ስደቶችና መፈናቀሎች የአገሪቱን 450 ሺህ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጠቂ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሞ፣ ተገቢው ድጋፍ ካልተደረገ በመጪዎቹ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ በየቀኑ በአማካይ 240 ህጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
ቦኮ ሃራም በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው የሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰባት ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ከአነዚህ የአገሪቱ ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት እንደሆኑም አመልክቷል፡፡
የምግብና የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችና ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ ቢሄድም፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ ተገቢ ምላሽ አልሰጠም ያለው ዩኒሴፍ፤መንግስታትና ለጋሾች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

Read 1143 times