Monday, 30 January 2017 00:00

የፌስቡክ መስራች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት አልወዳደርም አለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በተለያዩ ድረገጾች የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመሆን ዕቅድ አለው የሚል መረጃ በስፋት ሲሰራጭበት የከረመው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ መረጃው ሃሰተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ዙክበርግ በቅርቡ ባልተለመደ ሁኔታ ፖለቲካ ቀመስ አስተያየት መስጠቱን ተከትሎ፣ ወደ ፖለቲካው አለም የመግባትና ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንዳለው የሚጠቁሙ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ መሰንበታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ግለሰቡ ግን ሰሞኑን ከአንድ ድረገጽ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ መረጃውን ማስተባበሉን ዘግቧል፡፡
“የሚወራው ነገር ሃሰት ነው፡፡ እኔ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ የለኝም፡፡ ሙሉ ትኩረቴን የማደርገው የፌስቡክን ማህበረሰብ በመገንባትና ከባለቤቴ ጋር ባቋቋምነው ቻን ዙክበርግ ኢኒሺየቲቭ የተሰኘ ድርጅት አማካይነት የበጎ አድራጎት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው” ብሏል ዙክበርግ፡፡
ዙክበርግ ለፕሬዚዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንደሌለው ያስታውቅ እንጂ፣ ወደ ፖለቲካ የመግባትም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመስራት እቅድ ይኑረው አይኑረው በግልጽ ያለው ነገር እንደሌለ ዘገባው ገልጧል፡፡
ዙክበርግ ፕሬዚዳንት የመሆን እቅድ አለው የሚለውን ጭምጭምታ ያጠናከረው ደግሞ፣ የፌስቡክ ኩባንያ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በቅርቡ ባደረገው ማሻሻያ፣ ዋና ስራ አስፈጻሚው በፖለቲካዊ ምርጫ የመወዳደር መብት እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ ማስተካከሉ ነው ተብሏል፡፡

Read 1539 times