Monday, 30 January 2017 00:00

ሶማሊያ ለ10ኛ ተከታታይ አመታት በሙስና አለምን መርታለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ኢትዮጵያ በሙስና ከ176 የአለማችን አገራት 68ኛ ደረጃን ይዛለች

     ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ አመታት በሙስና ክፉኛ በመዘፈቅ አለምን ስትመራ የዘለቀቺው ሶማሊያ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016ም ቀዳሚነቷን ማስጠበቋን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም አስታውቋል፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የአመቱ የዓለማችን የሙስና ሁኔታ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ጥናቱ ከተሰራባቸው የአለማችን 176 አገራት በሙስና 68ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም ጠቁሟል፡፡
ተቋሙ በአለማችን ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋባቸው አገራት በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ፡- ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ኮርያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ያገኙ ሲሆን  ሶርያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ጊኒ ቢሳኦ እና ቬንዙዌላ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የዓለማችን 176 አገራት መካከል ዴንማርክና ኒውዚላንድ እጅግ አነስተኛው ሙስና የሚታይባቸው ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ ፊንላንድና ስዊድን በሁለተኛና በሶስተኛነት መቀመጣቸውን ገልጧል። አነስተኛ ሙስና ያለባቸው የአለማችን አገራት ተብለው የተዘረዘሩት ቀሪዎቹ አገራት ደግሞ፣ ስዊዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ሲንጋፖር፣ ኒዘርላንድስ፣ ካናዳና ጀርመን ናቸው፡፡
ሙስና መጠንና ስፋቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም የአለማችን አገራት እንደሚታይ ያስታወሰው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፤ በርካታ የአለማችን አገራት ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በ2016 መሻሻል ከማሳየት ይልቅ የባሰ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

Read 1249 times