Monday, 30 January 2017 00:00

የክፋት ማስታወሻዬ (ወግ)

Written by  ሌ.ግ
Rate this item
(0 votes)

 ሁሉም ነገር ድንገት ግልፅ ሆኖልኛል፡፡ ወለል ብሎ ታይቶኛል፡፡ ማድበስበስ፣ መታሸት አያስፈልግም፡፡ አንድ እውነት ብቻ ነው ያለው … መጀመሪያ እውነቱን ከተቀበልሁ በኋላ ነው ኑዛዜና ፍትሐት የሚከተለው፡፡ ያወቅሁትን እውነት እንዳልሰማሁት… በጭንቅላቴ ውስጥ ኡ.ኡ! ብሎ እየጮኸ ልክድ፣ ክጄው በህልውና መቀጠል አልችልም፡፡
አዎ እኔ ክፉ ሰው ነኝ፡፡ በቃ እኔ ነኝ ሰይጣን፡፡ እኔ ክፉ ሰው ነኝ፡፡ ‹ድንገት ክፉ መሆኔን ደረስኩበት› እያልኩ አይደለም፡፡ ከመጀመሪያውም ክፉ መሆኔን ተቀበልኩት ነው ያልኩት፡፡
አንድ እውነት ብቻ ነው ያለው፤ ስሙም ‹‹ውበት›› ይባላል፡፡ ታሪክ እውነት አይደለም፡፡ ታሪክ ዣክ ሩሶ እንዳለው፤ ‹‹ ከብዙ ውሸቶች መሀል የተሻለውን፣ እውነት መሳዩን አወዳድሮ የመምረጫ ጥበብ ነው››
ታሪክም ሳይንስም የግለሰብ አይደሉም፡፡ … ሳይንስና ታሪክ የመተዳደሪያ አገልግሎት አበርካች ናቸው፡፡ ውበት የሰው ናት… ከሰውም ደግሞ የግለሰቡ፡፡ ለቁሳቁስ አለም የማይረባ፣ ለግለሰብ ብቻ የሆነ፣ ብቸኛ እውነት “ውበት” ነው፡፡  
እና ውበት የማይበትን አእምሮዬን ለተለያዩ ውሸቶች ከመጀመሪያው በመሸጥ ነው ክፉ የሆንኩት፡፡ አለም አይደለችም የክፋት መናኸሪያ፤ … ሰይጣን ከአለም ውጭ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል አይደለም ክፋትን በምድር ላይ የሚያሰራጨው፡፡
እኔ ውበትን ለመመልከት ስጠየፍ ወይ ስፈራ ነው የሰይጣን ስራ የሚጀምረው፡፡
እና አምኛለሁ፤ እኔ የእውነት ክፉ ነኝ፡፡ በክፋቴ ንብርብር አይኔ በሞራ ተደፍኗል፡፡ ማየት ሳልችል ነው የማሰላስለው፡፡ ሀሳዊ መሆኔን የሚገልፁ … ‹‹ምን እያደረክ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ቀብሬ መኖር እንደማልችል እንደማላውቅ ሁሉ፣ አይኔን ጋርጄ እመላለስ ነበር፡፡
ውበት እየሞተ እንደሆነ እያማረርኩኝ … ገዳዩን ባህሪዬን ግን አብሬው እኖራለሁኝ፡፡ የእውነት ገዳዮች ታላላቅ ስልጣን ላይ ተቀምጠው አጀንዳ የሚሽሩና የሚያፀድቁ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ የእውነት ገዳይ፡- እውነት ምን ማለት እንደሆነ የማያውቀው ሊሆን ፈፅሞ አይችልም፡፡ የተፈጥሮ ገዳይ ፍጡር ሊሆን እንደማይችለው፡፡ የሀይማኖት ገዳይ ምዕመን አይደለም፡፡ ሀይማኖትን በምዕመኑ ነፍስ ውስጥ ውበት ዘርቶ፣ እውነት ብሎ እንዲያምንበት ማድረግ የሚችሉ እያሉ … ተራ ምዕመን ለእምነቱ ማሽቆልቆል ወይንም መምከን ተጠያቂ ሊሆን እንዴት ይችላል?
አዎ እኔ ክፉ ነኝ፡፡ ብቸኛው የሰው አንጡራ ሀብት … ‹‹ውበት›› እንደሆነ ጠንቅቄ እያወቅሁኝ… … ሀብቱ ከምድረ ገፅ ለመጥፋት ለአደጋ መጋረጥ እየገባኝ ምንም አስተዋፅኦ አላደረኩኝም፡፡ ‹‹ምን ይደረጋል?!›› ብዬ አእምሮዬን አጣጥፌ ተቀመጥኩኝ።
እርግጥ ክፉ ማለትማ ሰው የገደለ፣ የዘረፈ፣ ያሳደደ ነው ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ማሳደድ መዝረፍና መግደል … ‹‹ውበት›› እና ‹‹እውነት›› ሆነው የመተዳደሪያ ደንብ እስኪሆኑ ዝም ብሎ የታዘበው የእውነትና የውበት ፈጣሪው ክፋት … ከተግባሩ አድራጊዎች የበለጠ ነው፡፡
ፍልስፍና የእውነት ማፈላለጊያ ጥበብ ነው። ሐይማኖት መልካምን የማመላከቻ ጥበብ ነው። ውበት ግን ሁሉንም ጥበብ ማጠቃለያው ነው። ፍልስፍና እውነትን ላለመጨበጥ ሆን ብሎ  የሚጠበብ ከሆነ፣ ሀይማኖት መልካምን ከመጨበጥና ከማስጨበጥ ተገልሎ እኩይን እንደ ማስፈራሪያ በመስበክና በስልጣኑ ላይ ዘላቂ ሆኖ መቀጠል እንዲችል ብቻ የሚያልም ከሆነ፣ ጥበብ ከውበት ውስጥ የሰውን እውነት ጠቅልላ በማሳየት ፋንታ አስቀያሚነትንና ሰቆቃን በማምረት የሰውን መንፈስ መረበሽ ከሆነ …. ከዛ በመከተል የሚመጡ አውሬዎች የእነዚህ መነሻ ውጤቶች ናቸው፡፡
እኔ ጥበብን ማየት እችላለሁ (ወይንም እችል ነበር!) በአእምሮዬ ግዛት መጀመሪያ ያላሰላሰልኩትን በአይኔ ብቻ ማየት አልችልም፡፡ ምዕመኑ ከሀይማኖቱ ፈጣሪዎች … ርዕዮተ አለሙ ከፈላስፋዎቹ እንደሚመጣ ሁሉ … በአይኔ የማየውም በአዕምሮዬ አቅም ወይንም ብስለት አንፃር የተቃኘ ነው፡፡
ክፋቴ የሚጀምረው አእምሮዬን ችላ ከማለት ነው፡፡ አእምሮ በባለቤቱ ምርጫ የሚሰራ ነገር ነው … በተሰራ አእምሮ የተስተዋለ አለም በቀላሉ ወደ ውበት ሊለወጥ ይችላል፡፡ “አእምሮ የእግዜር ሬዲዮ” ነው፤ ይላሉ ሀሳባዊያኑ ፈላስፎች፡፡ ምናልባትም አባባላቸው የእውነት ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አእምሮ “የእግዜር ሬዲዮ” ቢሆንም የአእምሮው ባለቤት ነው ለተገቢ (adequate) አገልግሎት እንዲውል የሚያዘጋጀው፡፡ የሬዲዮውን ሞገድ ከፍ ላለ እውነት መሳቢያ ወይንም ከወለል በታች ለወረደ ድንቁርና የሚያጨው የአእምሮው ባለቤት ነው፡፡
“የእግዜርን ሬዲዮ” ለቡና ወሬና ርካሽ ጥላቻ ማዋሌ ነው ክፉነቴ፡፡ የእኔ ክፋት ስውር ነው፤ ስውር ከመሆኑ የተነሳ ከራሴም ግንዛቤ ተሰውሮ ቆይቷል፡፡ ከራስ ግንዛቤ የሚሰወር ክፋት አደገኛ ደረጃ የደረሰው አይነት ነው፡፡ ክፉነቱን፤ በራስ መተማመንና በሀሳዊ ልበ ሙሉነት ለውጦ ባለቤቱን ሲያጭበረብረው እድሜ ልክ ሊኖር ይችላል፡፡
እኔ ግን ደረስኩበት፡፡ የስነ ልቦና ችግር ብዬም አላድበሰብሰውም፡፡ ክፉ ነኝ፡፡ እውነት ስትገደል ፈዝዤ የተመለከትኩኝ፣ ውበት ማየት ቀስ በቀስ እንዲያቅተኝ አድርጌ፣ ነፍሴን በተራ አዙሪት ውስጥ የከተትኩኝ ነኝ፡፡ “የኔ ብቻ ጥፋት አይደለም፤ የሁላችንም ነው” ብዬ ደግሜ ራሴን አልደልልም፡፡
እኔ ስለ ራሴ ተጠያቂ ነኝ፡፡ ወንጀሌም ክፋት ነው፡፡ ክፋት በራሴ ላይ፤ ክፋት በእውነት ላይ። ክፋት በውበት ላይ … ክፋት በሰው ልጅ መጪ ዘመን ላይ …፡፡
ፈላስፎቹ ናቸው ማጥፋት የሚጀምሩት የሚለውን አልቀበልም፡፡ ከሎጂክ በፊት ከሰው ጋር የተፈጠረው “intuition” ነው፡፡ ከፈላስፋዎቹ መከሰት ቀድሞ ውበትን የመገንዘብ ጥበብ በሰው ልጆች ዘንድ ነበር፡፡ ከአስር ሺ ዓመታት በፊትም፣ ሰው የዋሻ ግድግዳ ላይ ስዕል ይስል ነበር፡፡ እሳት ዳር ተቀምጦ ተረት ይናገር ነበር፡፡ ሀይማኖት ራሷ ከጥበብ ማህፀን ውስጥ የተወለደች ነች፡፡ በውበት ውስጥ ሁሉም አለ፡፡ “ሁሉም” የሚለውን ቃል “እውነት” የሚለው ቃል ይጠጋዋል፡፡ እውነት ግን የተጠጉትን ሁሉ ላያቅፍ ይችላል፡፡
እና ውበትን ማየት፣ ማድነቅና ለመፍጠር መፍጨርጨር ውስጥ ሁሉም ቅድመ ዕውቀቶች በተለያየ መጠን ተጠናቅረዋል፡፡ ስለዚህ ጥበበኛ ለተጠያቂነት ከሌሎቹ ይቀድማል፡፡ ተጠያቂ ነው፡፡
ግን አሁን በዚህ ዘመን ጥበበኛ የመሆን ወይንም ውበትንና እውነትን የሚፈጥር ባይኖርም እንኳን የመፍጠር አቅሙ ግን አሁንም አብሮት አለ፡፡ “የእግዜር ሬዲዮ” አገልግሎቱ ተዛብቶ፣ በተለያየ አሳሳች ተደናቁሮ ሞገዱ ቢደበዝዝም … በትክክለኛ መንገድ የሚገለገልበት ከመጣ ግን ነገርዬው ስራውን ይሰራል፡፡
እናም ሼክስፒር በድጋሚ የማይፈጠረው፣ እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ወይንም የዘመን መንፈስ ስላልዋጀው ወይንም ውብ ነገርን መስራት ፋሽኑ ስላለፈበት ሳይሆን … እንደኔው የውበት አቅማቸውን የከዱ ብዙዎች በእውነት ማመን ስላቆሙ ነው። በውበት ማመን ያቆሙት እነ እንትና …ወይ… እነ እከሌ አይደሉም፡፡ ከራሴ በላይ የሚጠቆምበት ተጠያቂ የለም፡፡
ሼክስፒር የቋንቋ አጠቃቀሙ ወይንም የሚገልፅበት መንገድ አይደለም ስራዎቹን የማይደገሙ ያስመሰላቸው፡፡ መነሻው አእምሮውን ያደረጀበት አቅም ነው፡፡ በፅሁፍ የገለፃቸው ምስሎች … መጀመሪያ በአእምሮው ውስጥ ተጠብቦ የጨረሳቸው ናቸው፡፤
“ውበት የማድነቅ አቅምን ወይም የፈጠራ አቅምን “አቦ” ናቸው የሚሰጡት እያሉ ሲያምኑ፣ አብሬ ማመኔ ነው ክፉነቴ፡፡ ጥበብ አቦ ሰጡኝ እንዳልሆነ የማወቅ አቅሜን በዝንጋኤ መሰንከሌ ነው ክፉነቴ፡፡
በራሴ አቅም ላይ ምን ያህል ልከፋ እንደምችል አለማወቄ … ከተጠያቂነት ነፃ አያደርገኝም፡፡ በተለያየ ምክኒያት፣ በተለያየ ዘመን፣ በተለያየ አዙሪት ውስጥ ወድቀው በተፈጥሮ የተሰጣቸውን አቅም ያዘናጉ ሁሉ፣ በሰውነት ሚዛን ይበልጥም በራሳቸው ላይ ሸፍጥ የፈፀሙ ክፉዎች ናቸው፡፡
ክፋቴን በዚህ አተያይ ማማረሬ፣ ኑዛዜና ፍትሀት የማድረግ አባዜ ተጠናውቶኝ ሳይሆን … ምናልባት የራሴ አእምሮ ወደ ላይ መመንደግ ባይሆንለት እንኳን … እንደ አጀማመሩ ወደ በለጠ አዘቅት እንዳይንደረደር ለማስታወስ ያገለግለኝ ይሆናል በሚል ነው፡፡  

Read 1262 times