Print this page
Sunday, 05 February 2017 00:00

የተሻሻለው የትራፊክ ህግ ፀደቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(39 votes)

- የመንጃ ፈቃድ እስከማሰረዝ የሚደርሰው የተሻሻለው ህግ በቅርቡ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፡፡
                  - በየዕለቱ ከ7 ሰዎች በላይ በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ፡፡
        በአገሪቱ በከፍተኛ መጠን እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስና በአደጋው የሚከሰተውን የሰዎች ሞት ለማስቀረት እገዛ እንደሚያደርግ የተነገረለት የተባለው የተሻሻለው የትራፊክ ህግ ፀደቀ፡፡
የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ አዲሱ የተሻሻለው ህግ፣ በሚመለከታቸው አካላት ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡
የተሻሻለው አዲሱ የትራፊክ ደንብ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን የሚያጠፋና ሪከርድ የተመዘገባቸው አሽከርካሪዎች የመንጃ ፍቃዳቸውን ለመሰረዝ የሚያስችል ደንብ ተካቶበታል፡፡
የትራፊክ አደጋዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸውና ሁኔታዎች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረውን የትራፊክ ህግ መፈተሸና ማሻሻያችን ማድረግ በማስፈለጉ ምክንያት የማሻሻያ ህጉ እንዲፀድቅ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ለትራፊክ አደጋዎች መከሰት ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ የተባሉት እንደ አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የትራፊክ መብራቶችን መጣስና በተሽከርካሪ ጉዳት አድርሶ ማምለጥ ከህግ ተጠያቂነት በተጨማሪ በወንጀል ክስም ቅጣት እንደሚያስከትል የተሻሻለው ህግ ያመለክታል፡፡ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የተባለው አዲሱ የተሻሻለው ህግ በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚውልና በተከታታይም የህብረተሰቡንና የአሽከራካሪዎችን ግንዛቤ ለማዳበር የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
 በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ7 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን ከሚደርሱት የትራፊክ አደጋዎችም 85 ፐርሰንት የሚሆነው በአሽከርካሪው ችግር የሚከሰት መሆኑ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው  በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አለማቀፍ የሹፌሮች ቀን በዓልን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት የሚከበረውና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንና የሹፌሮች ማህበር ባዘጋጀው በዚህ በዓል፣ የትራፊክ ህጎችን አክበረው ለሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ክብር ለመስጠት የሚያስችሉ ፕሮግራሞች የሚካሄዱ ሲሆን ሹፌሮችንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ የፓናል ውይይት ይካሄዳል፣ የአመቱ ምርጥ አሽከርካሪም ይሸለማል ተብሏል፡፡  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየደረሰ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት የአዲስ አበባ  ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፤ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ሁሉም ዜጎች በተለይም አሽከርካሪዎች ብዙ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

Read 16999 times