Sunday, 05 February 2017 00:00

ለደመወዝ ጭማሪ ማጸደቂያ ለሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎችየተሰጠው 50ሺ ብር ጉቦ እንዲመለስ ታዘዘ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

  • ድርጊቱን ያጋለጡት፣ “የሥራ ዋስትናችን ለስጋት ተጋልጧል” እያሉ ነው
                      • የማጸደቂያ ‘ስጦታው’ በሌሎችም አድባራት የተለመደ መሆኑ ተጠቁሟል

      በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የደብረ ተኣምራት ጻድቃኔ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሠራተኞች፤ ለተፈቀደላቸው የደመወዝ ጭማሬ ማጽደቂያ በሚል፣ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊ በስጦታ ለመክፈል፣ የተጠየቁትን የ50 ሺሕ ብር ጉቦ(የሁለት ወራት ጭማሬ) ማጋለጣቸውን ተከትሎ፤ ገንዘቡ እንዲመለስላቸው ታዘዘ፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ፣ ዋና ጸሐፊ፣ ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥርና የገንዘብ ቤት ሓላፊ፤ “ደመወዙን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጸድቀን ያመጣነው የስጦታና የማጸደቂያ ገንዘብ ከፍለን በመሆኑ የታኅሣሥና የኅዳር ወር ጭማሬያችሁን 50 ሺሕ ብር ለእኛ ትለቁልናላችሁ፤” እንዳሏቸው አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡
“ለምን እንለቅላችኋለን?” ብለው መጠየቃቸውን የጠቀሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ “እንዲህ ዓይነቱ ነገር በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት የተለመደና የሚደረግ መሆኑን ታውቃላችሁ፤ ይህ ብር ካልተከፈለ ደመወዙ ሊጸድቅ አይችልም፤” በማለት ሓላፊዎቹ እንደመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎቹም፣ በወቅቱ የሓላፊዎቹን ምላሽ በአንድ ድምፅ ቢቃወሙም፣ የኅዳር ወር ጭማሬያቸው ብር 25ሺሕ፣ ለሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ እና ለሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊ አቶ ገብረ ሕይወት አስገዶም ስጦታ ተቀንሶ በባንክ መከፈሉን አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይም፣ የታኅሣሥ ወሩ ብር 25ሺሕ ሊቆረጥባቸው በመታሰቡ፣ በቀጥታ ደብሩ ለሚገኝበት የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ማመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነትም፣ አቤቱታውን ተቀብሎ በመደባቸው ልኡካኑ በማጣራት ድርጊቱ ሕገ ወጥ መሆኑን ገልጾ፤ ከሠራተኞቹ የደመወዝ ጭማሬ ላይ በስጦታ የተወሰደባቸው ገንዘብ፣ ለሁሉም ካህናትና ሠራተኞች ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተመላሽ እንዲሆንና የአፈጻጸሙ ሪፖርት እንዲገለጽለት የደብሩን አስተዳደር አሳስቧል፤ ደብሩም በሕግ አግባብ እንዲመራ የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት አሳስቧል፡፡ ይህም ሆኖ፣ “ድርጊቱን በማጋለጣችን ከሥራ ለማዘዋወርና ለማገድ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ይይኑ ደብሩ ድረስ በመምጣት ከጽ/ቤቱ ሓላፊዎች ጋር በመሆን መክረውብናል፤” ያሉት ካህናቱና ሠራተኞቹ፣ “ቀጣይ የሥራ ዋስትናችንም ለስጋት ተጋልጧል፤”  ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት በጻፉት አቤቱታ አመልክተዋል፡፡
ለተፈጸመባቸው በደል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የተማፀኑ ሲሆን፤ በደብሩ ሓላፊዎች የተፈጸመው የሙስና ወንጀል የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ በመሆኑ እንዲጣራና ጥፋተኞችም ለሕግ እንዲቀርቡ በአቤቱታቸው ጠይቀዋል፡፡

Read 6533 times