Sunday, 05 February 2017 00:00

‹‹አረና›› የወልቃይትንጉዳይ እወያይበታለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

   በ‹‹ኤፈርት›› ጉዳይም እወያያለሁ ብሏል
       ዛሬ እና ነገ በመቀሌ 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያካሄደው አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለፍትህ ፓርቲ፤ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ውዝግብ ላይ፣ ከጎንደር በተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችና በ‹‹ኤፈርት›› ጉዳይ ላይ አተኩሮ እንደሚወያይ አስታወቀ፡፡
የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብርሃ ደስታ ስለ ጉባኤው ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ አረና ክልላዊ ፓርቲ ቢሆንም ፕሮግራሞቹና አጀንዳዎቹ ሀገራዊ መሆናቸው ጠቁመው፤ በዛሬው እለት ነባሩ ስራ አስፈፃሚ የጉባኤውን አጀንዳዎች በዋናነትም ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች አጀንዳ እንዲሆኑ መካተታቸውን  አስታውቀዋል፡፡
በጉባኤው በወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚመከርና ፓርቲው እስካሁን የተከተለው የፖለቲካ ስልት ምን ውጤት እንዳመጣና ለወደፊት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመዋሃድ የሚከተለውን አዲስ የፖለቲካ ስትራቴጂ እንድሚነድፍ አቶ አብርሃ አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በነበረው የህዝብ ተቃውሞ ስለተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችም አበክሮ ይመክራል ያሉት የሥራ አስፈፃሚው፤ ተፈናቃዮቹ ያለምንም እርዳታ በየቤተክርስቲያኑና በየጎዳናው ወድቀው በልመና ተሰማርተው እንደሚገኙና የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየተንከባከባቸው አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤው በተለየ ሁኔታ ስለ ወልቃይት ማንነት ጉዳይ፣ ስለ ሃገሪቱ የብሄር ፖለቲካ፣ ስለ መሬት ባለቤትነት፣ ስለ ተፈናቃይ እርሶ አደሮች ካሳ፤ ስለ ሃገርና ህዝብ አንድነት እንዲሁም ፓርቲው ከህወኃት አባላት ጋር በቀጣይ ስለሚኖረው ግንኙነት… ውይይት በማድረግ  አዳዲስ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አብርሃ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አረና የመድረክ አባል ሲሆን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት በሚፈጠርበት ጉዳይ  ላይ እንደሚወያይና ከመድረክ ጋር የነበረው ግንኙነትም እንደሚገመገም ታውቋል፡፡
ፓርቲው ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በመላው ትግራይ የአባላት ቁጥሩ ማደጉን የጠቆሙት አቶ አብርሃ፤ በቀጣይም አባላትን የማደራጀት አዲስ ስልት እንደሚነደፍ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው በክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ የዘለቀ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት እንዳለውም  ጠቅሰዋል፡፡
‹‹በስሩ በርካታ ገንዘብ አመንጪ ተቋማትን የያዘው “ኤፈርት” የተሰኘው ተቋም የትግራይ ህዝብ ነው ቢባልም ፓርቲያቸው፤ የሚጠቀሙበት የህውሓት ባለስልጣናት ናቸው ብሎ እንደሚያምን የተናገሩት አቶ አብርሃ፤ የ‹‹ኤፈርት›› ጉዳይ በጉባኤው ላይ በስፋት ከሚመከርባቸው አጀንዳዎች አንዱ ይሆናል ብለዋል፡፡
‹‹በቀጣይ ምርጫ አረና ካላሸነፈ፣ ‹‹የኤፈርት እጣ ፈንታ ምን ይሆናል›› በሚለው ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግበት አስታውቀዋል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያም ለመጪው 3 ዓመታት ፓርቲውን የሚመሩ የስራ አስፈፃሚ አባላትን ጨምሮ ሊቀመንበርና ምክትል/ሊቀ መንበር ይመረጣሉ ተብሏል፡፡

Read 5846 times Last modified on Monday, 06 February 2017 08:14