Sunday, 05 February 2017 00:00

ከአሜሪካ የሚባረሩ ኢትዮጵያውያን ካሉ፣ መንግስት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

     ‹‹በኢትዮጵያ ጉዳይ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል››
     የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት አዲስ የስደተኞች ፖሊሲ፣ ከሀገሪቱ የሚባረሩ ኢትዮጵያውያን ካሉ መንግስት የፖለቲካ ልዩነት ሳያደርግ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ትናንት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ላይ፣ በአሜሪካ የሚገኙ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚጠሉና በትጥቅ ትግል ጭምር የታገዘ ተቃውሞ የሚያደርጉ ቢሆኑ እንኳ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ለመኖር ቢፈልጉ መንግስት እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበላቸው አስታውቀዋል፡፡
“ኢትዮጵያ እንኳን የራሷን ዜጎች የሌሎች ሀገራት ዜጎች ተቀብላ ታስተናግዳለች” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ምናልባት ተታለውም ይሁን የተሻለ ህይወት ለመፈለግ በሚዲያ በግልፅ የኢትዮጵያን መንግስት የሚያጥላሉ ቢሆንም የሚናገሩትን ሳይሆን ልባቸውን ነው የምናየው” ብለዋል፡፡
“እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን ይጠላሉ የሚል አቋም የለንም ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ ‹‹ተገደው ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ ከሆነና የፖለቲካ ፍላጎት ካላቸው፣ በፈለጉት ሠላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ሆነው አላማቸውን ማራመድ ይችላሉ›› ብለዋል፡፡
“አመለካከታቸውን ቀይረው ሃገራችን ተሽላናለች ብለው የሚመጡ ካሉም መንግስት ከመቀበል ወደ ኋላ አይልም” ብለዋል፤ ሚኒስትሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ዶናልድ ትራምፕ ከሚከተሉት ፖሊሲ አንፃር አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበላሻል የሚል እምነት
መንግስት እንደሌለው ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የትራምፕ መንግስት ለራሱ ጥቅም ሲል የተሻለ የንግድ ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ሆና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ትሰራለች፤ በአፍሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ስላላት ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ ይቀንሳል የሚል ስጋት የለብንም ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ መንግስት ከዚህ ቀደም የነበረው በኢትዮጵያ የአሜሪካ የውስጥ ጣልቃ ገብነት፣ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል የሚል እምነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

Read 6237 times Last modified on Monday, 06 February 2017 08:18