Sunday, 05 February 2017 00:00

እናትህ የላከችህን ሳይሆን ገበያው የሰጠህን ነው የምታገኘው

Written by 
Rate this item
(12 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት የመሞቻው ቀን በመቃረቡ የንብረቱን ውርስ ለልጆቹ ለመስጠት፤ ሦስቱን ልጆቹን ወደ አልጋው ጠራቸው፡፡ ከዚያም፤
‹‹ከእናንተ መካከል በጣም ብስልና ብልህ ለሆነው ልጅ ርስቴን፣ ሀብቴንና ንብረቴን ላወርስ እፈልጋለሁ፡፡ እጅግ ብልሁን ልጅ የምለየው፤ ለምጠይቀው ጥያቄ የተሻለውን መልስ ለሚመልስልኝ ነው፡፡ ትስማማላችሁ?›› አለ፡፡
ሦስቱም በአንድ ድምፅ፣ ‹‹አዎን፡፡ እንስማማለን›› አሉ፡፡
‹‹እንግዲያው ጥያቄዬን ስሙ፡፡ ይሄን ያለንበትን ቤት ባንድ ጊዜ ግጥም አድርጎ የሚሞላ ቀላል ነገር ፈልጋችሁ፣ በ3 ቀን ውስጥ አምጡ››
ልጆቹ ጥያቄውን እያሰላሰሉ ወጡ፡፡
በሦስተኛው ቀን፤ ሶስቱም የሚመስላቸውን መልስ ይዘው መጡ፡፡ የመጀመሪያው ልጅ፤ ‹‹አባቴ ሆይ! በጣም ቀላል ግን በቀላሉ ይሄን ቤት የሚሞላ ነገር ብዬ ያሰብኩት ጥጥ ነው፡፡ ጥጥ ለመሸከም አይከብድም፡፡ ቤታችንን ግን ዳር እስከ ዳር ይሞላዋል›› አለ፡፡
ሁለተኛው ልጅ ቀጠለ፡-
‹‹አባቴ ሆይ! ለእኔ የመጣልኝ ሀሳብ፤ ቀላል ሆኖ ይሄን ቤት በቀላሉ የሚሞላ ጭድ ነው፡፡ ለሸክም አይከብድም፤ ግን ከጥግ እስከ ጥግ ቤታችንን ይሞላዋል›› አለ፡፡
ሦስተኛውና የመጨረሻ ትንሹ ልጅ ተነሳና፤
‹‹አባቴ ሆይ! ወንድሞቼ ያሉት ልክ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ዳር እስከ ዳር አንድም ክፍተት ሳይኖረው ላይሞላው ይችላል፡፡ እኔ ያመጣሁት ሀሳብ ግን ምንም ጥርጥር የለውም፤ ቤቱን በደንብ ይሞላዋል! ይኸውም፤ ይቺ አንዲት ሻማ ናት! ይቺ ሻማ ስትበራ  እየቀለጠች ቤቱን ብርሃን በብርሃን ታደርገዋለች፡፡ ይዤ ለመምጣት ግን ኪሴ ውስጥ ማስቀመጥ ብቻ ነው ያስፈለገኝ፡፡ ወንድሞቼ ራሳቸው ይፍረዱ›› ብሎ ተቀመጠ፡፡
አባት፤
‹‹እህስ? ወንድሞቹ ምን ትላላችሁ?›› ብለው ጥያቄውን ለሌሎች አጋሩ፡፡
ሁለቱም ታላላቅ ወንድሞች ለትንሹ ወንድማቸው ፈረዱና፤ ‹‹ከዚህ የተሻለ ጥበብ የተሞላ መልስ የለም!›› ብለው አፀደቁለት፡፡
*    *    *
ዕውነት የሆነን ነገር አምኖ መቀበልን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ትንሹ ወንድማቸው ያቀረበውን ሀሳብ ታላላቆቹ መቀበላቸው እጅግ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል! መሸነፍን ሳይፈሩ የተሻለውን ሀሳብ ማፅደቅ!!
አስተዋይና ብርሃናማ ትውልድ ለአገር መድህን ይሆናል፡፡ ማናቸውም ችግር ሲፈጠር መፍትሔውን ለመፍጠር ይተጋል፡፡ መከራ በቀላሉ አይረታውም፡፡ ከህይወት ይማራል፡፡ ከትምህርት ቤት ያገኘውን ዕውቀት መሬት ላይ ይተገብራል። እንዲህ ያለውን ትውልድ ለመጎናፀፍ ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል፡፡ ያም ሆኖ ጨለምተኛ ሆነን አናስበውም፡፡ በሂደት ይወለዳል፡፡ በሂደት ያድጋል፡፡ አንድ ቀን ባለፀጋ ያደርገናል፡፡
ሁልጊዜ አገርን ሊታደጉ የሚችበት በመጀመሪያ ጥቂቶች ናቸው እያደር ብዙሃን ይሆናል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ከባድ ድካምንና ታከተኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መሥራትን የግድ ይላል፡፡ ሃምሳ ዓመት የፈጀውን የንጉሡን ዘመን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ማስተዋል ነው፡፡
የምንታገለው ከአድርባይነት ጋር ነው፡፡ የምንታገለው ከሥራ  አጥነት ጋር ነው። የምንታገለው ከሥርዓተ አልበኝነት ጋር ነው፡፡ የምንታገለው ከምንደኝነት ጋር ነው።  የምንታገለው ከግብረገብ አልባነት ጋር ነው፡፡ የምንታገለው ከጅምላ ድህነት ጋር ነው፡፡ ትግሉ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ የአሁኑ ትውልድ እንደ ወጣት ረዥም መንገድ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ከጠባብነት እስከ ትምህክተኝነት ድረስ የተንሰራፋውን ችግር በዋዛ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ውስብስብም ነው፡፡ በዚህ ላይ ፀረ ዲሞክራሲነትና ሙስና እንዲሁም ኢ -ፍትሐዊነት ሲተከልበት ምን ያህል ሥር የሰደደ መከራ እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ፅናት ይፈልጋል፡፡ ደፋር እርምጃ ይጠይቃል፡፡ ጥልቅ ዕውቀት ይሻል፡፡
ጉዟችን ወዴት ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የግንባታ አፈፃፀም ማነስ በሰፊው ይሰማል፡፡ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ አለመናበብ አንዳንዴም መወዛገብም ይሰማል፡፡ የመካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ዝቅተኛ መሆን ይነገራል፡፡ መመሪያዎች ይቀረፃሉ እንጂ ተግባራዊነታቸው ደብዛዛ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች እንኳ በአቅል አልተሠሩም፡፡ በቂ ቦታም አጥተዋል። የከተማ ነዋሪውም በአግባቡ አይጠቀምባቸውም፡፡ በአጠቃላይ ከወሬ ያለፈ ሥራ የለም እየተባለ ነው፡፡ ጥልቅ ተሐድሶው ጥልቅ ዐይን ያስፈልጋዋል፡፡ ከአንገት በላይ የሆነ ነገር ፍሬው አመርቂ አይሆንም፡፡ ብዙ የሥራ ሰዓት ባክኖበታልና ውጤቱ በጥኑ መገምገም ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የምናየው ያው ቤት ያፈራውን ነው፡፡ የአገር አቅም የፈቀደውን ነው የምናየው፡፡ ‹‹እናትህ የላከችህን ሳይሆን ገበያው የሰጠህን ነው  የምታገኘው›› የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ገበያው እንዲጠናከርና እንዲሰፋ ማድረግ የእኛው ፋንታ ነው፡፡

Read 5865 times