Sunday, 05 February 2017 00:00

ትውልደ ኢትዮጵያዊው፤ በቢዮንሴ ፎቶ አለማቀፍ ዝናን አትርፏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ነፍሰ ጡርነቷን የሚያሳየው ፎቶ በተወዳጅነት ክብረወሰን ይዟል

     ታዋቂዋ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፣ ነፍሰ ጡር መሆኗን ለአድናቂዎቿ በማብሰር ባለፈው ረቡዕ በኢንስታግራም ድረ-ገጽ በኩል ያሰራጨቻቸውን አነጋጋሪና ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፉ ፎቶ ግራፎች ያነሳው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የፎቶ ግራፍ ባለሙያ አወል ርዝቁ፣ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈ የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ቢዮንሴ ከባለቤቷ ጄይዚ መንታ ልጆችን በማርገዟ የተሰማትን ደስታ በመግለጽ፣ በኢንስታግራም ያሰራጨቻቸው እርግዝናዋን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እጅግ በሚገርም ፍጥነት የአለምን ትኩረት የሳቡ ሲሆን፣ አንደኛው ፎቶ በአንድ ቀን ጊዜ ውስጥ ከ8.2 ሚሊዮን በላይ ‹‹ላይክ›› በማግኘት በኢንስታግራም ታሪክ ከፍተኛውን ተወዳጅነት በማትረፍ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን የአለም የድንቃ ድንቆች መዝገብ ተቋም አስታውቋል፡፡
ያልተመዱትና እርግዝናዋን በግላጭ የሚያሳዩት ፎቶግራፎች አለማቀፍ መነጋገሪያ መሆናቸውን ተከትሎ፣ ፎቶግራፎችን ያነሳው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፎቶ ግራፈር አወል ርዝቁ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ ታላላቅ የአለማችን መገናኛ ብዙሃንም እሱንና ለአመታት የዘለቀውን የስነ-ጥበብ ታሪኩን በተመለከተ በስፋት በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ የተወለደውና በአሜሪካ ያደገው የ28 አመቱ አወል ርዝቁ፤ በዋናነት የፎቶግራፍ ባለሙያ ቢሆንም፣ ተቀማጭነቱን በሎሳንጀለስ በማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኝ ሰአሊ፣ ቀራጺና የአጫጭር ፊልሞች አዘጋጅ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ ከአሜሪካው ኮፐር ዩኒየን ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ2010 በፋይን አርትስ የመጀመሪያ ዲግሪውን መቀበሉንና እ.ኤ.አ በ2014 ከታዋቂው የል ዩኒቨርሲቲ በፋይን አርትስ ሁለተኛ ዲግሪውን ማግኘቱንም አስታውሷል፡፡
ኒውዮርክ በሚገኘው ሚዩዚየም ኦፍ ሞደርን አርት እና በሌሎች የአሜሪካ ሙዚየሞችና ጋለሪዎች የፎቶግራፍና ሌሎች የስነ-ጥበብ ስራዎቹን በግልና በተናጠል በኢግዚቢሽን መልክ ለተመልካቾች ያቀረበው አወል፤ ከዚህ በፊትም ቢዮንሴን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን ታዋቂ ድምጻውያንን አስገራሚ ፎቶግራፎች በማንሳት ይታወቃል፡፡
በአነጋጋሪ ፎቶ ግራፎች የታጀበው የቢዮንሴ የእርግዝና ዜና በትዊተር ድረገጽ በከፍተኛ ፍጥነት የተሰራጨ ሲሆን፣ ረቡዕ ዕለት ብቻ በየደቂቃው በአማካይ 17 ሺህ ጊዜ ስለጉዳዩ ትዊት መደረጉንና የትዊተር ተከታዮቿ ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ 93.1 ሚሊዮን መድረሱን ሲኔት ድረገጽ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2008 በትዳር የተሳሰሩት ታዋቂዎቹ የዓለማችን ዝነኛ ድምጻውያን ቢዮንሴ እና ጄይ ዚ፣ ከሶስት አመታት በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸውን ብሉ ኢቪን ወልደው ለመሳም በቅተዋል፡፡

Read 2874 times