Sunday, 05 February 2017 00:00

የሃሳቦች ቫይረስና አንቲ ቫይረስ?!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

 “Ted Talks” በሚል ርዕስ የሚስተናገዱ የምዕራባዊያን የሀሳብ እርሾዎችን አነፍንፌ ለመከታተል እሞክራለሁኝ፡፡ ሁሉም ሀሳቦች አስገራሚ ናቸው፡፡ አንዳንድ የሚያስደነግጡም አይጠፉባቸውም፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን የሰው ልጅ በመጪው ዘመናት ወደዬት አቅጣጫ በማምራት ላይ እንዳለ አመልካች ናቸው፡፡
ፕሮግራሙ “ምርጥ” ብሎ የሚያምንባቸውን የሀሳብ ዘረ መሎች በአለም ዙሪያ ባሉ አእምሮዎች ውስጥ ማስረፅ ዋናው አቋሙ መሆኑን “ሎጎው” ላይ ይገልፃል፡፡ ልብ ብዬ መርሆውን አላስተውለውም ነበር፡፡ በስምምነት ህግ የተቀበልናቸው አዝማቾች አሉ፡፡ እውቀትን ማሰራጨት ሰናይ መሆኑን እንዲሁ በደፈናው እንስማማለን፡፡ እውቀት ምን እንደሆነ ማወቅ ካቆምን የቆየን ቢሆን እንኳን!
በዚሁ በ “Ted Talks” የሀሳብ ማሰራጫ ጣቢያ፣ ዳን ዳኔት የሚባል ሰውዬ ያቀረበው ጥናት ግን ለብዙ ቀናት እንዳሰላስል አስገድዶኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ፤ በተለይ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ጠቅልሎ የገለፀው ስለመሰለኝ ነው በሀሳብ የተብሰለሰልኩት፡፡ ባቀረበው ሀሳብ መዋጤ በገለፀው ሀሳብ መጠቃቴን ይገልፃል፡፡
“We Spread Ideas” በሚል ባንዲራ ስር በሚመላለስ የ“Ted Talks” ፕሮግራም ላይ ፈላስፋው ዳን ዳኔት ቀርቦ ሀሳብን ማሰራጨት ምን ማለት እንደሆነና በየዋህነት ሁላችንም እንደምናምነው የተሰራጨ ሀሳብ ሁሉ መልካም ላይሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃል፡፡ መጀመሪያ ግን ገለፃውን ለመረዳት “ሜም” (Meme) የምትለዋ ቃል ቁልፍ ናት፡፡ ሜም፤ በኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ላይ በሰፈረ ፍቺው፡- “A cultural unit (an idea or value or pattern of behavior) that is passed from one generation to another by non genetic means (as by imitation) ይላል፡፡ ዝቅ ይልናም፡- memes are the cultural counter part of genes ብሎ ይጨርሳል፡፡
ይኼንን የመዝገበ ቃላት ፍቺ ከተንቀሳቃሽ ስልኬ የዲክሽነሪ አፕሊኬሽን ላይ ነው ያገኘሁት። በ1960 እ.ኤ.አ በፊሊፒንስ የቅጂ መብት ስር የታተመውን የዌብስተር መዝገበ ቃላት አገላብጬ “meme” የሚለውን ቃል ማግኘት ያልቻልኩት … ቃሉ የተፈጠረው በ1976 እ.ኤ.አ በመሆኑ ምክኒያት ነው፡፡ “The Selfish Gene” የሚለው የሪቻርድ ዶውኪንስ የመጀመሪያ መፅሀፍ ከመታተሙ በፊት ቃሉ አገልግሎት ላይ አልዋለም ነበር፡፡ እርግጥ “meme” እነማን ቃላት ጋር ዝምድና እንዳለው “Memory” የሚሉ ነባር ቃላትን የሚያውቅ ሁሉ መጠርጠር አያዳግተውም፡፡
ሪቻርድ ዳውኪንስ በመፅሐፉ ላይ ለዚህ ቃል የበየነው ትርጉም “Replicating Idea” የሚል ነው፡፡ በመፅሐፉ ላይ የሰዎችን ባህላዊ ምንነት ለመፍታት ይጥራል፡፡ በጥረቱም ባህል እየተወራረሰ የሚቀጥል ሀሳብ ነው ይለዋል፡፡ እንስሳት የዘረ መል ንድፋቸውን ከአባት ወደ ልጅ በመዋለድና በመተካካት እንደሚያስቀጥሉት፣ የሰው ልጅ ደግሞ በእውቀት በኩል የሀሳብ ዘረ - መል እየተወራረሱ ባህል አንፀው ይቀጥላሉ ማለቱ ነው፡፡
እንግዲህ ትዝ ይለኝ ከሆነ፣ ዶውኪንስ በእንስሳት አለምም እንደ ባህል መሰል ውርርስ እንዳለ ያጣቅሳል፡፡ ለምሳሌ፤ ከአንድ እሩቅ ስፍራ የመጣ ወፍ ተጉዞ የደረሰበት ቦታ አስቀድመው ከነበሩ በዝርያ ከሚመስሉት ወፎች ጋር የዜማ ልዩነት እንደሚኖረው ይገልፃል፡፡ ወፉ ግን አዲስ ባረፈበት “ቀዬኤ” በቂ ጊዜ ሲያሳልፍ፣ ይዞ የመጣውን ዜማ አዲስ ለአረፈበት አካባቢ ያወርሳል፤ ከእነሱም ወስዶ የራሱን ዜማ ይከልሳል፡፡  መጤው ወፍ ብቻ ሳይሆን ነባሮቹም ወፎች መጤው ወፍ ይዞ በመጣው ባዕድ ዘይቤ የቀድሞ ቅላፄያቸው ይበረዛል፡፡ ምናልባት በወፎች አንፃር ከተመለከትነው የባህል ውርርስ ማለት ትርጉሙ ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡
ሰዎችን በተመለከተ ግን እንደ ወፎቹ የዜማ ውርርስ የሀሳብ ውርርስ ነው የሚካሄደው። ዘረ - መል በመራቢያ አካላት አማካኝነት ነው የሚተላለፈው፤ ባህል ግን ሀሳብን በማስተላለፊያ አውታር የሚባዛ ነው፡፡
ከመፅሐፍት ጀምሮ ሬዲዮው፣ ቴሌቪዥኑ አሁን ደግሞ ቀድሞ ከነበሩት ሀሳብ ማስተላለፊያዎች እጅግ በበለጠ መጠን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በእያንዳንዳችን እጅ ውስጥ ገብቷል፡፡
ቃላት የሀሳብ ዘረ መል ንድፍ መፃፊያ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ ቃላት “Meme” ናቸው፡፡ ምስል ወይንም ፎቶ “Meme” ነው፡፡ የሀሳብ ንድፍን እንደ ድሮው ባህር አቋርጦ በመሄድ በቀጥታ ማስተማር በአሁኑ የቴክኖሎጂ ዘመን አስገዳጅ አይደለም፡፡
ከአንድ የዓለም አፅናፍ በተቀመጠበት ሆኖ ሌላ ዓለም አፅናፍ ያለ ሰው ላይ ሀሳብን ማራገፍ ይቻላል፡፡ በእጃችን ያለው ስልክ የማሰራጫ ወይንም የመቀበያ መሳሪያ ነው፡፡ አሰራጪውም ይሁን ተቀባዩ ግን በቀጥታ ወደ አእምሮ ለማስገባት የሚያደርገው ሙከራ ነው፡፡
እርግጥ እነ ሪቻርድ ዳውኪንስ ባህል (የሀሳብ ቅብብሎሽ) መሰረታዊ የሆነውን የተፈጥሮ ንድፍ ማለትም የዘረ መል ሽግግርን አይለውጠውም ባይ ናቸው፡፡ በሀሳብ ምክኒያት የሚመጣ የባህል ማንነት በዘረ መል (በተፈጥሮ ከተነደፈ) ውስጠኛው ማንነት የተለየ ነው ማለታቸው ነው፡፡
ፈላስፋው ዳን ዳኔት ግን በተፈጥሮ የተሰጠውን የዘረ መል ተልዕኮ ውጫዊ የሆነው ሀሳብ ወይንም ባህል እንደ “ፓራሳይት” ተጣብቆ ከማንነት ትርጉሙ ሊያሰናክለው ይችላል ይላል፡፡ (“only man can subordinate his genetic interest to other interests”)
ሀሳብ ከፓራሳይት ጋር ያለውን ተመሳሳይነት ለማሳየት የአንዲት ጉንዳንን ጥናት ያነሳል፡፡ ጉንዳኗ በተደጋጋሚ አንድ ሳር ላይ ወጥታ ጫፍ ድረስ ስትጓዝ ትቆይና፣ ጫፍ ደርሳ ስትወድቅ ትታያለች። ከወደቀች በኋላ በድጋሚ ተነስታ ያንኑ ተግባሯን ትደግማለች፤ መውጣትና መውደቁን፡፡
ሳይንቲስቶቹ ምን ሆና እንደሆነ ሲመረምሩ ፓራሳይት በራስ ቅሏ ውስጥ ያገኛሉ፡፡ ጉንዳኗ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ የሚያዛት ፓራሳይቱ መሆኑን ይደርሱበታል፡፡ የጉንዳኗ የተፈጥሮ ግብ በፓራሳይቱ “ሀይጃክ” ተደርጓል … እንደማለት ነው፡፡
ዳን ዳኔት በዚህች ጉንዳን መነሻነት ስለ ሰው ይጠይቃል፡፡ ሰውስ እንደ ፓራሳይት በውስጡ ገብቶ፣ ተቆጣጥሮት እንደ መኪና የሚነዳው ተዋህሲያን ይጣባው ይሆን? ሲል ይጠይቃል። መልሱ አዎ ነው፡፡ ግን ሰውን የሚጣባው (የሚቆጣጠረው) ተዋህሲያን ፓራሳይት ሳይሆን ሀሳብ ነው፡፡ ሀሳብ ወይንም ፅንሰ ሀሳብ፡፡ ወይንም የፅንሰ ሀሳብ ክምችት የሆነው ባህል፣ ሀሪሶት፡፡ ወይንም የባህል ትልቁ ግማድ የሆነው ሀይማኖት … የሰውን ግብ የሚሾፍሩት እነዚህ ሀሳቦች ናቸው፡፡
እነዚህ የሰውን አእምሮ በጥልቅ ወይንም በቁንፅል ለመቆጣጠር የተዘጋጁ የሀሳብ ዘረ መሎች በዳውኪንስ ቋንቋ “Meme” ተብለው ይጠራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ይሄንን የሀሳብ ስርጭትና ቅኝ ግዛት በቀላሉ የማከናወኛ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ጥርጊያ ይከፍታል፡፡ … የተሻለ እየሆነ እየረቀቀ ይቀጥላል፡፡
ስለዚህ እኔ ማን ነኝ? ወይንም የማን ነኝ? ብሎ ደጋግሞ መጠየቅ አስፈላጊና የመጠየቂያ ጊዜውም አሁን ነው፡፡ (ትንሽ ለጥያቄው ማርፈዳችን ግልፅ ቢሆንም!)
ዳን ዳኔት ይቀ    ጥልና፤ “Guns, Germs and Steel” የሚል የ “Jared Diamond”ን መፅሐፍ ያነሳል፡፡ መፅሐፉ በጥንታዊ ቅኝ ግዛት ዘመን፣ ቅኝ ገዢዎች ተገዢዎችን ይዘው በመጡት መሳሪያ (ጠብ መንጃ፣ ብረት) ከጨፈጨፉት ይበልጥ …ቅኝ ገዥዎቹ በሰውነታቸው ውስጥ ተሸክመው በመጡት “ጀርም”፣ በሽታ … የሀገር ቤቱን (Native) ህዝብ ለመፍጀት ዋነኛ ምክኒያት ስለመሆኑ የሚተነትን ነው፡፡ ባህር ተሻግረው የመጡት ፈረንጆች ከጀርሙ ጋር በመቆየታቸው በሽታውን የመቋቋሚያ ብቃት ካዳበሩ ቆይተዋል፤ … የሀገር ቤቱ ቅኝ ተገዢ ግን ከበሽታው ጋር ትውውቅ ስለሌለው በቀላሉ ይጠቃል፤ ተጠቅቶም እንደ ቅጠል ይረግፋል፡፤
ዳን ዳኔት ይኼንን መፅሐፍ ማንሳት የፈለገው በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ቅልጥፍና ምክኒያት ከፈረንጆቹ (ከሰለጠኑት) ሀገሮች ወደ አልሰለጠኑት የሚላከውን ቅኝ ገዢ ሀሳብ፣ ከቅኝ ግዛት ዘመን በሽታና እልቂት ጋር ሊያያይዘው ስለፈለገ ነው፡፡
ከመጀመሪያውም ሀሳብን ለራስ ግብ የሚጠቅም እስካልሆነ ድረስ እንደ ጉንዳኗ የራስን ማንነት የሚያጠፋ ፓራሳይት ነው … ሲል እንደነበር ዳን ዳኔትን ጠቅሻለሁ፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን ጀርም ይዘው ሄደው ቅኝ የተገዙትን ሰዎች ለመፍጀት ፈልገው ወይንም በባዮሎጂ ጦር መሳሪያ እናጥቃው ብለው አልነበረም ባህር የተሻገሩት፡፡ ከእነሱ አካል ጋር ተላምዶና የመጉዳት አቅሙ ደክሞ የሚኖር ምቶ ተስማምቶ ጀርም … በሌላ፣ ስፍራ ልምድ የሌለው ህዝብ ላይ ገዳይ በሽታ እንደሚሆነው ሁሉ … በሀሳብም ረገድ ፈረንጆቹ ክፉና ደጉን ለይተው ደካማ እና ጠንካራ ጎኑን መዝነው ተስማምተው አብረው የተጓዙት ፀንስ ሀሳብ ወይንም የሀሳብ ባህል እኛ በተለየ የባህል ወይንም የአስተሳሰብ እርከን ላይ ለምንኖረው እንደ ገዳይ ጀርም ሊሆንብን ይችላል፡፡
ሀሳብ ጠቃሚም ሆነ ጎጂ ጀርም ለመሆን ቀድሞ ከነበረው (ውስጣችን ተጣብቶን እንደ ጉንዳኗ ሲነዳን ከነበረ) የራሳችን ባህላዊ ሀሳብ ጋር ምን ያህል ይናበባል? ወደምንፈልገው ግብ ነው የሚመራን ወይንስ እንደ ጉንዳኑ “ሀይጃክ” አድርጎን እንደ እብድ በትርጉም የለሽ ውሃ ቅዳ ውሀ መልስ አዙሪት አሳብዶ ያስቀረናል? … የሚለው ጥያቄ ነው ወሳኙ፡፡
ዲሞክራሲም የሀሳብ አይነት ነው፡፡ ፕሩላሪዝምም ሀሳብ ነው፡፡ ነፃነትም የሀሳብ አይነት ነው፡፡ … ሁሉም የሀሳብ አይነት ወይንም የመረጃ አይነት መልካም ወይንም ጎጂ ፓራሳይት ሊሆን ይችላል፡፡ መጀመሪያ ያቀድነው ምን ማድረግ ነው? … ምንድን ነን? ወደ ምን ለመድረስ ነው የምንፈልገው? … በሚል ቅድመ ጥያቄ የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡
የሚሰራጭብንን መጠነ ብዙ መረጃ … ወይንም ሀሳብ ወይንም “Meme” ዝም ብለን ከመዋጣችን (መቅዳታችን) በፊት የሀሳብን ጥቅም ከራሳችን ጥቅም አንፃር መዝኖ የማጥለያ የ “Purpose” ሶፍትዌር በውስጣችን እንደ ጋሻ ማደርጀት ግድ ይላል፡፡ … የዚህን ሶፍት ዌር ትርጉም እኔ “Morality” ብዬ ነው የምጠራው፡፡ ሶፍትዌሩን ኢሜኑኤል ካንት ጥሩ አድርጎ ተንትኖታል፡፡ ካንት ተነተነው እንጂ አልፈጠረውም፡፡ ፈጣሪው እግዜር ነው፡፡ ግብረ ገብን እንደ ቅድመ ሳቢያ እና ውጤት (before perception or medium of perception which are time and space) ያልያዘ አእምሮ … በተለያየ የሀሳብ ጀርም መጠቃቱ አይቀርም፡፡
ቴክኖሎጂ ሳይንስ ነው፡፡ ሳይንስ የራሱ የሆነ ግብረ ገብ የለውም ይላሉ፤ እንደ በትራንድ ረስል መሰሎቹ “Humanist” ፈላስፎች፡፡ ስልክ ቴክኖሎጂ ነው፤ ስልክ ሳይንስ ነው፡፡ በስልኩ ውስጥ የሚሰራጨውን የቫይረስ ሶፍትዌር በአንቲቫይረስ ሶፍትዌር እንደምንከላከለው ሁሉ ለአዕምሮ ታቅደው የሚሰራቹ ጎጂ ሶፍትዌሮችን ሁሉ አፕዴት እያደረግን የምንከላከልበት የእውነት፣ ግብረ ገብ፣ ቅንነት … ወዘተ የመሰሉ  “መልካምን የሚያጎለብቱ እኩይን የሚከለክሉ” የሀሳብ ደጀኖች ሊኖሩን ይገባል፡፡
ካልሆነ በግለሰብ የምንነት ትርጉማችንም ላይ ይሁን እንደ ማህበረሰብ ያገለግሉናል ብለን በምንመካባቸው የጋራ ጥቅሞቻችን ላይ አደጋ መጋረጡ የማይቀር ይሆናል፡፡  

Read 2819 times