Sunday, 05 February 2017 00:00

የዓለማችን ዝነኞች እና የትራምፕ የስደተኞች እገዳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ምን አይነቱ ነውር የማያውቅ አሳማ ነው!...” - ሪሃና
     “ያሉት ከሚጠፋ፣ የወለዱት ይጥፋ!...”
ብለዋል - ትራምፕ፡፡
በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ላይ፣ “ከተመረጥኩ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እከለክላለሁ” ሲሉ የከረሙት አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ፤ በለስ ቀንቷቸው ባሸነፉና ወደ ነጩ ቤት ሰተት ብለው በገቡ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ፣ ቃላቸውን ጠብቀው ያሉትን አደረጉና ብዙዎችን አስደነገጡ፡፡
“የአገሬንና የህዝቤን ደህንነት ለመጠበቅና ሰርጎ ገብ ሽብርተኞችን ለመከላከል ስል፣ ለማንኛውም አገር ስደተኞችና ለሰባት አገራት ዜጎች በጊዜያዊነት ድንበሬን ዘግቻለሁ!...” በማለት፣ በብዙዎች ዘንድ የሚወራ እንጂ የማይተገበር ተደርጎ የተወሰደውን አስደንጋጭ ነገር ማድረጋቸውን በይፋ አወጁ፡፡
ትራምፕ ባለፈው አርብ በሰባት የተለያዩ አገራት ላይ የጣሉት የጉዞ ገደብ፣ ብዙዎችን በድንጋጤ ክው ያደረገ አነጋጋሪ፣ አስደንጋጭ፣ አከራካሪ አለማቀፍ ክስተት ሆነ፡፡ ጉዳዩ የሰባቱ አገራትና የአሜሪካ አልያም የስደተኞችና የተወላጆች ብቻ ጉዳይ አልሆነም፡፡ የአለማችንን ህዝቦችና የአለማችንን መንግስታት ያነጋገረና ድንበር ሳያግደው ርቆ በመጓዝ በየጓዳው የገባ ሰሞንኛ ጉዳይ ሆነ፡፡
የትራምፕ ውሳኔ በአለማችን ፖለቲከኞች ብቻም ሳይሆን በመዝናኛው መስክ የአለማችን ከዋክብት ዘንድም ድንጋጤንና ቁጣን ፈጥሯል። ከእውቅ የሆሊውድ ተዋንያን እስከ አለማቀፍ የሙዚቃ ከዋክብት፣ በርካታ የአለማችን ዝነኞች በትራምፕ አስደንጋጭ ውሳኔ ዙሪያ አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
የአለማችን ዝነኞች ለትራምፕ ውሳኔ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ መገናኛ ብዙሃን ካወጧቸው ዘገባዎች በጥቂቱ እንጨልፍ!...
ከቀናት በኋላ በሎሳንጀለስ በደማቅ ሁኔታ ለሚከናወነው ታላቁ የኦስካር ሽልማት ከታጩት መካከል አንዱ ነው - ዳይሬክተሩ አስጋር ፋራዲ፡፡
“ዘ ሴልስማን” በሚለው ፊልሙ ለሽልማት የታጨውና ያቺን ልዩ ቀን በጉጉት ሲጠብቅ የሰነበተው ዳይሬክተሩ አስጋር ፋራዲ፤ ያቺ ልዩ ቀን ከመድረሷ በፊት ያልጠበቀውን መርዶ ሰማ፡፡ በዚያች ቀን በሎሳንጀለስ ተገኝቶ፣ የጓጓለትን ሽልማት መቀበል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ኢራናዊ ነው። ኢራናዊ ደግሞ፣ በትራምፕ ትዕዛዝ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለ የሽብር ተጠርጣሪ ነው፡፡
ዋታኒ - “ማይ ሆምላንድ” በሚለው ፊልሟ በዘንድሮው ኦስካር፣ በዘጋቢ ፊልም ዘርፍ ለሽልማት የታጨቺው ሶርያዊቷ ሃላ ካሚልም፣ ትራምፕ በክፉ አይናቸው ካዩዋት አገር የተገኘች ናትና፣ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ እንድትገኝ አይፈቀድላትም፡፡ በዚህ አስደንጋጭ ውሳኔ ክፉኛ ማዘኗን ገልጻለች- ሃላ ካሚል፡፡
የትራምፕ ውሳኔ ካስደነገጣቸውና ካሳዘናቸው የአለማችን ዝነኞች መካከል ትጠቀሳለች - ዝነኛዋ ድምጻዊት ሪሃና፡፡ ድምጻዊቷ ትራምፕ ውሳኔውን ባስተላለፉ በነጋታው፣ ጉዳዩን በተመለከተ በትዊተር ባሰራጨቺው ጽሁፍ፣ “አስቀያሚ ነገር ነው!... የሰማሁት ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነው!... አይናችን እያየ፣ አሜሪካ እየጠፋች ነው!...” ብላለች፡፡
ሪሃና ይህን ብላ አላበቃችም...
“ምን አይነቱ ነውር የማያውቅ አሳማ ነው!...” ስትል ጋሼ ትራምፕን በገደምዳሜ ወርፋቸዋለች፡፡
ታዋቂው የሆሊውድ የፊልም ዳይሬክተር ማይክል ሙር በበኩሉ፣ “በመላው አለም የምትገኙ ሙስሊም ጎረቤቶቻችን ሆይ፡ እኔ እና በአስር ሚሊዮኖች የምንቆጠር ሌሎች አሜሪካውያን ይቅርታ እንጠይቃችኋለን፡፡ አብዛኛው የአሜሪካ ህዝብ ለዚህ ሰውዬ ድምጹን አልሰጠም!...” በማለት በትዊተር ገጹ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ጆን ሌጀንድ በበኩሉ፤ “እኛ አሜሪካውያንና ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ያለን ራዕይ ፍጹም ተቃራኒ ነው!...” ብሏል፤ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በተከናወነው የፕሮዲዩሰርስ ጊልድ ሽልማት ስነስርዓት ላይ ባደረገው ንግግር፡፡
በዚያው ዕለት የሙዚቃ ኮንሰርቱን ለአድናቂዎች ያቀረበው ድምጻዊው ብሩስ ስፕሪንግስተን በበኩሉ፤ “አሜሪካ የስደተኞች አገር ናት፡፡ የሰውዬው ውሳኔ ኢ-ዲሞክራሲያዊና ከአሜሪካ እሴቶች ውጭ ነው!...” በማለት በትራምፕ ውሳኔ ማዘኑን ገልጧል፡፡
“ወደ አሜሪካ የመጣሁት ከ32 አመታት በፊት ነው፡፡ በዚህች አገር ነዋሪ በመሆኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ያፈርኩት ግን፣ ትናንት ነው!...” በሚል በትራምፕ ውሳኔ ማግስት በትዊተር ሃዘኑን የገለጸው ደግሞ፣ “ዘ ቲፒንግ ፖይንት” በሚለው መጽሃፉ የሚታወቀው ደራሲ ማልኮም ግላድዌል ነው፡፡
የተርሚኔተሩ ድንቅ ተዋናይና የቀድሞው የካሊፎርኒያ ገዢ አርኖልድ ሽዋዚንገርም በትራምፕ ውሳኔ መከፋቱን አልደበቀም፡፡ “ይህ እጅግ የለየለት እብደት ነው!... ደደቦች ተደርገን እንድንቆጠር የሚያደርግ አጉል ውሳኔ ነው!...” ብሏል ሽዋዚንገር ከ”ፒውፕል መጋዚን” ጋር ሰኞ ዕለት ባደረገው ቃለ ምልልስ፡፡
“ስደተኞች ሽብርን ሽሽት ርቀው የሚጓዙ እንጂ፣ ሽብርተኞች አይደሉም” የሚለው መረር ያለ ምላሽ ደግሞ፣  የአሜሪካዊቷ ድንቅ የፊልም ተዋናይ የኬሪ ዋሽንግተን ነው፡፡ ዝነኞች ምንም ይበሉ ምን፣ትራምፕ ግን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለአሜሪካውያን ቃል የገቡትን ሁሉ ሳያጓድሉ እንደሚፈጽሙና አሜሪካንን ዳግም ታላቅ እንደሚያደርጓት በአገኟት አጋጣሚ ሁሉ ከመናገር ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡ ለመተግበርም ወደ ኋላ እንደማይሉ ሰሞኑን በግልጽና በድፍረት አሳይተዋል።

Read 992 times