Sunday, 05 February 2017 00:00

ጆኒ ዲፕ ለመጠጥ በወር 30 ሺህ ዶላር ያወጣል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የቅንጦት ኑሮ የሚገፋው ተዋናዩ፣ የወር ወጪው 2 ሚ. ዶላር ነው
     “ፓይሬትስ ኦፍ ዚ ካረቢያን” በሚለው ድንቅ ፊልም የሚታወቀው ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ጆኒ ዲፕ፣ ለመጠጥ በወር 30 ሺህ ዶላር እንደሚያወጣና በተለያዩ የቅንጦት ነገሮች በየወሩ በድምሩ በአማካይ 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሚረጭ የዘገበው ቢቢሲ፤ ይህ ያልተገባ አባካኝነቱ ለከፋ የገንዘብ ቀውስ እየዳረገው እንደሚገኝ መነገሩንም ገልጧል፡፡
የጆኒ ዲፕ የቢዝነስ ማናጀሮች፣ግለሰቡ እንዳሻው በሚበትነው የገንዘብ አወጣጡ ሳቢያ ለከፋ ቀውስ እየተዳረገ እንደሚገኝ ማስታወቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 14 ያህል እጅግ ውድ የመኖሪያ ቤቶችንና 12 የውድ ንብረቶች ማከማቻ ቤቶችን ለመግዛት ብቻ ከ75 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን መግለጻቸውን አስረድቷል፡፡
የተዋናዩ የቢዝነስ ማኔጅመንት ቡድን አባላት ይህንን መረጃ ይፋ ያደረጉት፣ ግለሰቡ ተገቢውን ግብር በወቅቱ ባለመክፈል ለከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ዳርገውኛል፤ በወጉ አላስተዳደሩልኝም በሚል በአባላቱ ላይ የ25 ሚሊዮን ዶላር ክስ መመስረቱን ተከትሎ እንደሆነም ዘገባው ገልጧል፡፡  
የቡድኑ አባላት በበኩላቸው፤ የጆኒ ዲፕ ዝርክርክነትና ገንዘብ አባካኝነት ራሱን ለቀውስ እየዳረገው እንደሚገኝ በመግለጽ፣ በወር 30 ሺህ ዶላር በማውጣት ከውጭ አገራት ገዝቶ ያስገባቸውን የወይን መጠጦችና ለግል አውሮፕላኑ ያወጣውን 200 ሺህ ዶላር ጨምሮ ያለአግባብ ያወጣቸውን ወጪዎች ዘርዝረው ይፋ አድርገዋል፡፡

Read 1596 times