Sunday, 05 February 2017 00:00

ሞሮኮ ከ33 አመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ህብረት ተመለሰች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ላለፉት 33 አመታት ከአፍሪካ ህብረት አባልነቷ ተገልላ የቆየቺው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው 39ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በተደረሰው ውሳኔ መሰረት ወደ አባልነቷ መመለሷን ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የህብረቱ አባል አገራት ከምዕራባዊ ሰሃራ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ባለፈው ማክሰኞ ጠንከር ያለ ክርክር ካደረጉ በኋላ በደረሱት ስምምነት ሞሮኮ 55ኛዋ የህብረቱ አባል ሆና ዳግም እንድትቀላቀል ወስነዋል፡፡
“በስተመጨረሻም ወደ ቤታችን ተመልሰናል” ብለዋል የሞሮኮው ንጉስ ሞሃመድ ስድስተኛ፣ ህብረቱ አገሪቱ ወደ አባልነቷ እንድትመለስ መወሰኑን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፡፡ ሞሮኮ ዳግም የህብረቱ አባል ለመሆን ባለፈው አመት ሃምሌ ወር ላይ ባቀረበቺው ጥያቄ መሰረት፣ በህብረቱ አባል አገራት በተሰጠ ድምጽ ወደ አባልነቷ መመለሷ የተነገረ ሲሆን አገሪቱ ከሶስት አስርት አመታት በኋላ ወደ ህብረቱ አባልነቷ ለመመለስ ጥያቄ ማቅረቧ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማድረጓን ያሳያል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ በ1984  የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሞሮኮ ስር ትተዳደር ለነበረቺው ምዕራባዊ ሰሃራ፣ ራሷን የቻለች አገር ሆና መቀጠል የምትችልበትን እውቅና መስጠቱን ተከትሎ፣ ሞሮኮ ከህብረቱ አባልነቷ መውጣቷንና ለ33 አመታት ያህል ብቸኛዋ የአፍሪካ ህብረት አባል ያልሆነች አፍሪካዊት አገር ሆና መቆየቷን ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውሷል፡፡

Read 1313 times