Sunday, 05 February 2017 00:00

በ3ሺ ሜትር መሰናክል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• ‹‹በልምምድ እና በውድድር መድረኮች ያለው የቡድን ስራ፤ መተጋገዝ እና የስራ ፍቅር በአርዓያነት  የሚጠቀስ  ነው፡፡›› አትሌት ሶፊያ አሰፋ
• ‹‹ሴቶቹ በተደጋጋሚ ውድድሮች በመሳተፍ ብርቱ ፤ ንፁህ ስፖርተኞች፤ በቡድን ስራቸው ይመሰገናሉ፡፡… ‹‹ በቀሪ   ህይወቴ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የላቀ ውጤት በውድድሩ እንዲመዘገብ፤ አዲስ ትውልድ እንዲፈጠር    እፈልጋለሁ…›› ሻምበል እሸቱ ቱራ

    አትሌት ሶፊያ አሰፋ በ2012 እኤአ ላይ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ተካሂዶ በነበረው 30ኛው  ኦሎምፒያድ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ያገኘችው ውጤት፤ ከነሐስ ወደ ብር ሜዳልያ እንዲያድግ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የወሰነ ሲሆን ሽልማቱን ሰሞኑን ስትረከብ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በርቀትአይነቱ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች ምርጥ ሆናለች፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከ32 ዓመታት በፊት በሞስኮ ኦሎምፒክ ሻምበል እሸቱ ቱራ ከተመዘገበው የነሐስ ሜዳሊያ የላቀ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ስለሚመዘገብ ነው፡፡ አትሌት ሶፊያ 3ሺ ሜትር መሰናክል የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያዋን ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ከወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ የተቀበለችው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድሪሚላይነር ሆቴል በተካሄደ  ልዩ ስነስርዓት ነው፡፡
በ30ኛው ኦሎምፒያድ በ3ሺ ሜትር መሰናል በአንደኛነት  የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋ የነበረችው ሩሲያዊቷ አትሌት ዮሊያ ዛራፖቫ ‘’ስትሪዮድ ትሪናቦል’’ የተሰኙ የተከለከሉ ንጥረ ነገሮች ወስዳ በመገኘቷ ውጤቷን ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውጤቷን ለመሰረዝ  እንደወሰነ ታውቋል፡፡ በውሳኔው መሰረትም በለንደኑ ኦሎምፒክ ሁለተኛ ወጥታ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ቱኒዚያዊቷ አትሌት ሀቢባ ጋራቢ ከሩሲዊቷ አትሌት ተመላሽ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ፤ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሶፍያ አሰፋ በሁለተኛ ደረጃ የብር ሜዳልያው እንዲሁም  ኬንያዊቷ አትሌት ሚልካ ቼሞዝ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በለንደን ኦሎምፒክ አግኝታ የነበረችው የነሐስ ሜዳልያ  ወደ የብር ሜዳልያ አድጎላት ሽልማቱን ከተረከበች በኋላ ለስፖርት አድማስ በሰጠችው አስተያየት የብር ሜዳሊያውን በወቅቱ ማግኘት ብችል ደስታዬን እጥፍ ያደርገው ነበር ያለችው አትሌት ሶፊያ፤ ከአራት ዓመታት በኋላም ያገኘሁት ክብር በ3ሺ ሜትር መሰናል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ መመዝገቡ፤  የተሻለ ውጤት ለአገሬ ለማምጣት የሞራል ብርታት ይሆነኛል ብላለች፡፡ በሌላ በኩል በ3ሺ ሜትር መሰናክል ለመሮጥ ብዙ አትሌቶች ትኩረት አለመስጠታቸው እነሱን የሚተካ ትውልድ እንዳይታጣ የሚያሰጋት መሆኑን ስትገልፅ፤ ኬንያውያን የውድድር አይነቱን እንደባህላቸው በመቁጠር በየዓመቱ ተተኪ ወጣት አትሌቶችን የሚያፈሩ በመሆናቸው በውጤት የበላይነት እንደፈጠረላቸው መገንዘቧን በመጥቀስ ነው። በ3ሺ ሜትር መሰናክል ጥሩ ጤንነት እና የአካል ብቃት ያለው ማንኛውም አትሌት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል እና እንደሌሎች የሩጫ መደቦች በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ተመጣጣኝ የገንዘብ ሽልማት የሚገኝበት መሆኑንም ትመክራለች፡፡
አትሌት ሶፊያ አሰፋ በ3ሺ ሜትር መሰናል መሮጥ የጀመረችው ከ8 ዓመታት በፊት ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባክ ክለብን ስትቀላቀል ብዙ አትሌት ባልነበረበት በዚሁ ርቀት በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከተሳተፈች  እና 3ኛ ደረጃ ካገኘች በኋላ በርቀትአይነቱ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ 3ሺ ሜትር መሰናክል   የ3ሺ ሜትር መሰናክል ፈታኝነት በውድድሩ ክብደት ብቻ የሚገለፅ አይደለም ስትል ለስፖርት አድማስ የተናገረችው ሶፊያ ለውድድር አይነቱ በትራክ፤ በጎዳና ላይ እና በተራራማ ስፍራዎች ሳምንቱን ሙሉ የሚሰራው ልምምድ ከአሰልጣኝ ድጋፍ ባሻገር የግል ጥረት እና ትጋት የሚጠይቅ መሆኑን በማስረዳት ነው። በርቀት አይነቱ ካላት ሰፊ ልምድ በመነሳት ለስፖርት አድማስ በሰጠችው ተጨማሪ አስተያየት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለቱም ፆታዎች በሚገኙ አንጋፋና ወጣት አትሌቶች መካከል  በልምምድ እና በውድድር መድረኮች ያለው የቡድን ስራ፤ መተጋገዝ እና የስራ ፍቅር በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነም ተናግራለች፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ታሪክ በፈርቀዳጅ ታሪካቸው የሚታወሱት እና  በብሄራዊ ቡድኑ የርቀቱ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ሻምበል እሸቱ አትሌትሶፊያ የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያዋን በተረከበችበት ስነስርዓት ላይ ከነበሩት ታዳሚዎች ይገኙበታል፡፡ ሻምበል እሸቱ ቱራ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት  ባለፉት  5 ዓመታት በዓለም ሻምፒዮና፤ በኦሎምፒክ፤ በሌሎች አህጉራዊ ሻምፒዮናዎች እና በዳይመንድ ሊግ ላይ ጠንካራ ተሳታፊ ለሆኑት የ3ሺ ሜትር መሰናክል አትሌቶች በተለይ ለሴቶቹ ሶፍያ አሰፋ፤ ህይወት አያሌው እና እቴነሽ ዲሮ ልዩ አድናቆት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ሶስቱ የ3ሺ ሜትር መሰናክል ሴት አትሌቶች በተደጋጋሚ ውድድሮች በመሳተፍ ብርቱ፤ ንፁህ ስፖርተኞች፤ በቡድን ስራቸው የሚመሰገኑና የርቀት አይነቱ ተምሳሌት እንደሆኑ ያስመሰከሩ ናቸው›› በማለት የተናገሩት ሻምበል እሸቱ ቱራ ‹‹ቀሪ ህይወቴን በ3ሺ ሜትር መሰናክል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የላቀ ውጤት እንዲመዘገብ፤ አዲስ ትውልድ እንዲፈጠር፤ በተለይ በወንዶች በኩል ውጤታማት እንዲመጣ ከፍተኛ ዓለማ ይዣለሁ›› ይላሉ። ለዚህም የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑን አመራርነት የቀድሞ አትሌቶች እያከናወኑ መሆናቸውና ለስፖርቱ ባላቸው ቅርብት የሚያደርጉት ንቁ ክትትል የፈጠረው መበረታታት አስተዋፅኦ ሻምበል እሸቱ ቱራ ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል፡፡
ሻምበል እሸቱ ቱራ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በዋና አሰልጣኝነት ስለሚሰሩበት 3ሺ ሜትር መሰናክል ሲናገሩ ‹‹ከሩጫ የውድድር አይነቶች ከባዱ ነው፡፡ በትራክ ላይ 35  ጊዜ መሰናክል ይዘለላል፤ ከእነዚህ መሰናክሎች 7 ጊዜ ውሃ እየተንቦጫረቁ ማለፍ አለ፡፡ በየዝላዮቹ ትራኩን በመምታት መወዳደርም ፈታኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የርቀት አይነቱ በውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን በልምምድ መርሃ ግብሩ ጠንክሮ የመስራት ትጋት ያስፈልገዋል፡፡›› ይላሉ። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ለመሮጥ አትሌቶች  ብዙም የመሮጥ ፍላጎት አለማሳየታቸው ተገቢ አለመሆኑን ለስፖርት አድማስ ሲያስረዱም ‹‹የ3ሺ ሜትር መሰናክል የሚወዳደር አትሌት ለብዙ ውድድሮች ብቁ መሆን ይችላል፡፡ በአገር አቋራጭ፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች፤ በ3ሺ ሜትር ነፃ ውድድር እንዲሁም በግማሽ ማራቶን መወዳደር እንደሚችል ይታወቃል።  በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደብዙዎቹ የሩጫ ውድድሮች አትሌቶችን በገንዘብ ሽልማት ተጠቃሚ የሚያደርግም ነው። ስለዚህም አትሌቶች  ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው ያስፈልጋል›› የሚል ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡
አትሌት ሶፍያ አሰፋ እድሜዋ 29 ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ምርጥ ሰዓቷ 9፡09.84 ሲሆን በ2013 እኤአ ላይ በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳልያ የተጎናፀፈችሲሆን በ2015 እኤአ ደግሞ በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡ በ2014 እኤአ ደግሞ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሞሮኮ ማራካሽ የብር ሜዳልያ ነበራት፡፡
በ3ሺ ሜትር መሰናክል  በ4 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ያሸነፈችበት ታሪክ ይጠቀሳል፡፡ በተያዘው የውድድር ዘመን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ባላት ውጤት  በኦልአትሌቲክስ ድረገፅ መሰረት በ1334 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም በሁሉም የሴቶች ውድድሮችደግሞ በ1337 ነጥብ 51ኛ ላይ የምትገኘው አትሌት ሶፊያ አሰፋ ቀጣይ ትኩረቷ የአገር አቋራጭ ውድድር መሆኑን ለስፖርት አድማ በመጨረሻም ተናግራለች፡፡ ከሳምንት በሀኋላ በሚካሄደው የጃንሜዳ አገር አቋራ ላይ ለመሳተፍ እና ጠንካራ ውጤት ለማኘት እንደምትፈልግ ስትናገር ከተሳካላ ዘንድሮ በኡጋንዳ ካምፓላ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ አገሯን በመወከል ውጤታማ የመሆን እቅድ አለኝ በማለት ነው፡፡

Read 2644 times