Sunday, 05 February 2017 00:00

አቶ ልደቱ አያሌው፡- በፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ላይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የፖለቲካ ድርድር እንዲካሄድ ሲጠይቁ ከነበሩ ፖለቲከኞች አንዱ አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው። በድርድሩ አስፈላጊነትና ሊያስገኝ የሚገባው ውጤት፣ የፓርቲዎች በአንድነት ለድርድር መቅረብና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች አቶ ልደቱ ተከታዩን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
                • በድርድሩ የኢህአዴግን ጥልቅ ተሃድሶ በተግባር እንፈትሸዋለን
                • ሥርዓቱ ከፖለቲካ ሙስና ካልወጣ፣ ከኢኮኖሚ ሙስና ሊወጣ አይችልም
                • ህዝቡ ድርድሩን በቅርበት መከታተልና ጫና መፍጠር አለበት
     ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር የጀመሩት ድርድርና ውይይት ፋይዳው ምንድን ነው?  ምንስ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል?
እንደሚታወቀው አሁን ሀገሪቱ የምትተዳደረው በመደበኛ ህግ አይደለም፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ አጠቃላይ የስርአቱንና የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ቀውስ በመፈጠሩ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ቀውስ ሲፈጠር ሌላ መንገድ የለም፡፡ የህብረተሰቡን ጥቅምና ፍላጎት ከሚወክሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመደራደርና በመወያየት ነው መፈታት ያለበት፡፡ ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ ይሄ ነው፡፡ ስለዚህ አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፓርቲዎች አንድ ላይ ቁጭ ብለው መወያየት፣ መከራከርና ተደራድሮ አንድ ውጤት ላይ መድረስ ያለባቸው ጊዜ ላይ መሆናችንን የሚያሳይ ወቅት ላይ ነው፤ በዚህ የተነሳ በድርድሩ አስፈላጊነት ላይ ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡
አሁን በድርድሩ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ምን ያህል የህዝብ ውክልናና የመደራደር አቅም አላቸው?
ምን ያህል ውክልና አላቸው የሚለው እንግዲህ በቁጥር ለመመለስ አይችልም፡፡ ግን እያንዳንዱ ፓርቲ ይስፋም ይጥበብም የየራሱ ማህበራዊ መሰረት አለው፡፡ ህዝባዊ ድጋፍም መጠኑ ከፓርቲ ፓርቲ ሊለያይ ይችል ይሆናል፡፡ ግን ዋናው ቁም ነገር አሁን ባሉት ፓርቲዎች ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ አለ ወይ? ነው፡፡ አሁን ባሉት ፓርቲዎች ህብረተሰቡ ተስፋ ቆርጦ ሊሆን ይችላል፡፡ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ እንዳለ ይታያል፡፡ ግን ይሄ ስህተት ነው። ተስፋ ተቆርጦ ምንድን ነው የሚደረገው? ወዴትስ ነው የሚኬደው? ተስፋ ሊቆረጥ አይገባም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ደካማ ከሆኑ፣ ደካማ የሆኑት በአንድ በኩል ህብረተሰቡ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡ ጠንካራ ፓርቲ የመፍጠር ጉዳይ የማንም አይደለም፤ የህዝቡ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ አልነበረበትም፡፡ ይሄ ህዝብ እንደ ህዝብ የበቃ ከሆነ፣ ለሱ አስተሳሰብና ፍላጎት የሚመጥኑ ፓርቲዎችን መፍጠር መቻል አለበት፡፡ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ አሁን ያሉት ፓርቲዎች ደካማ ስለሆኑ፣ ከእነሱ ምንም አልጠበቅም ብሎ ቁጭ ማለት፣ የአንድን ህዝብ ተሸናፊነትና ደካማነት ነው የሚያሳየው እንጂ ትክክለኛ አቋም አይደለም፡፡
ይሄ ህዝብ እርግጥ ነው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስፋ አጥቷል፡፡ እርግጥ ነው አሁን እኛን ጨምሮ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ግን እኛም ደካማ የሆንነው ያለምክንያት አይደለም፤ የለውጥ ኃይል የሆነ ህዝብ ገና ስላልተፈጠረ ነው፡፡ ህዝቡ “ለጥቅሜ ለፍላጎቴ የሚቆም ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር አለብኝ” በሚል የበኩሉን አለማዋጣቱ ነው ዛሬ ላይ ደካማ ያደረገን። ገንዘብ፣ እውቀት፣ ጉልበት ----- ቢያዋጣና “ይሄ ጉዳይ ለምንፈልገው ለውጥ ምትክ የሌለው ወሳኝ ነው” ብሎ አምኖ ቢንቀሳቀስ፣ ጠንካራ ተቃዋሚዎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ፓርቲዎች የሉም ከተባለ ዞሮ ዞሮ የሚያሳየው የህብረተሰባችንን ድክመት ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ አማራጭ አይሆንም፡፡ ያለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይህቺ ሀገር የትም ልትደርስ አትችልም፡፡ በፓርቲዎች ያልተወከለ የፖለቲካ አስተሳሰብ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ ህብረተሰቡ ይሄን አውቆ የእሱን አስተሳሰብ፣ አመለካከት ሊወክል የሚችል ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር መጠየቅ አለበት፡፡ በተግባርም መታገልና ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ያ ሲሆን ነው፣ አንድ ህዝብ የለውጥ ኃይል ነው የሚባለው፡፡
ተቃዋሚዎች በድርድር መድረኩ ላይ እንኳ በአንድነት ለመሰለፍ አለመፈለጋቸውና እርስ በእርስ ከመናቆር አለመውጣታቸው------ህዝቡን ተስፋ አያስቆርጥም?
 ኢዴፓ ይሄን በመረዳት ነው መግለጫ አውጥቶ የነበረው፡፡ 22 ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር በተናጠል ተደራድረው ውጤት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው። ይሄ ሁሉ ፓርቲ ከኢህአዴግ ጋር የሚያደርገው ድርድር፣ እውነቱን ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። ውጤትም አያመጣም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ፓርቲዎች በሚያቀራርባቸው ጉዳይ----ለምሳሌ የሰብአዊ መብት ጉዳይ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ የሚዲያ፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ፣ የተቋማት ነፃነት የመሳሰሉት የጋራ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ዙሪያ በአንድነት ቆመን ብንደራደር፣የተሻለ ውጤት ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ መግለጫ ስናወጣም ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ በጎ ምላሽም እየተገኘበት ነው፡፡ ስድስት ፓርቲዎች አንድ ላይ ሆነን አቋማችንን ለመግለፅ ተስማምተናል፡፡ ሌሎቹ 11 ፓርቲዎች ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ አሁን በሶስት ቡድኖች ተከፍሎ መደራደር ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ በአንድ እንኳ ባይሆን በሁለት ቡድን ብንወከል ደግሞ የበለጠ ጥሩ ውጤት ያመጣል፡፡ ከተቃዋሚዎች በዚህ በኩል ከጠበቅነው በላይ በጎ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ቢቻል አንድ መሆንና ከኢህአዴግ ጋር መደራደር፣ ካልተቻለ ደግሞ ተቃዋሚዎች ሁለት ቡድን ሆነው፣ ከኢህአዴግ ጋር ቢደራደሩ የተሻለ ነገር ይፈጠራል ብዬ አምናለሁ፡፡
“በኦሮሚያ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኦፌኮ ሊቀመንበርን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ አመራሮች በእስር ላይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አለ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባሉበት ከገዢው ፓርቲ ጋር መወያየትና መደራደር ዋጋ አይኖረውም” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
 እነዚህ የተጠቀሱት ነገሮች መኖራቸው እንደውም ድርድሩን የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ ድርድሩ ያስፈለገው ችግሮች ስላሉና መፈታት ስላለባቸው ነው፡፡ የፖለቲከኞች መታሰርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያሳየን፣ የድርድር አስፈላጊነትን ነው እንጂ ለድርድሩ እንቅፋት ወይም ቅድመ ሁኔታዎች መሆን የለባቸውም፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ ድርድር ምን ያህል ቁርጠኛ ነው የሚለው ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ “ከሰማይ በታች ባለ ማንኛውም ነገር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ” ብሏል፡፡ ይሄ ከሆነ እነዚህንና ሌሎች የሀገሪቱ ችግሮችን የድርድሩ አጀንዳ አድርጎ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ግን ገና ድርድሩ ሳይጀመር ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ የታሰሩ ፖለቲከኞች መኖርና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድርድሩን የበለጠ አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡
በምርጫ 2002 ድርድር ተደርጎ ነበር፡፡ ያመጣው ውጤት አለ? የአሁኑስ --- ተስፋ አለው?
እስካሁን የነበሩት ድርድሮች አላማቸውን በትክክል አሳክተዋል ማለት አይቻልም፡፡ በድርድር ሂደቶቹ የተገኙ አንዳንድ በጎ ነገሮች ቢኖሩም፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደፊት ወስዶ፣ ህዝቡን በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የስልጣን ባለቤት በማድረግ ረገድ ግን ያን ያህል ፋይዳ የነበራቸው አይደሉም፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ በኩል ሁልጊዜ ድርድሮቹን ለፕሮፓጋንዳና ለሚዲያ ፍጆታ ለመጠቀም እንጂ ከልቡ እዚህ ሀገር የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ፍላጎት አላየንበትም።  ግን ይሄ አንዴ ሆኗል ተብሎ ተስፋ መቁረጥና መቀመጥ አያስፈልግም። ሁሌ መፈተሽ አለበት። እውነተኛ ድርድር እንዲካሄድ ሁሌ ግፊት ማድረግና የኢትዮጵያን ህዝብ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የስልጣን ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ አሁን በህዝብ ፊት “ተለውጫለሁ፤ጥልቅ ተሃድሶ እያደረግሁ ነው” ብሏል፡፡ ይሄን በተግባር እንፈትሸዋለን ማለት ነው፡፡
ከዚህ ድርድር ውጤት ይገኛል፤ተስፋ አለው ነው የሚሉት?
እሱን እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፤ ምክንያቱም ኢህአዴግ አንዳንድ ጊዜ የሚናገራቸውን ነገሮች ስናይ ከልቡ የተለወጠ አይመስልም። “አሁንም የኢትዮጵያን ችግሮች የማውቃቸው እኔ ብቻ ነኝ” የሚል አስተሳሰብ እናያለን፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ባለበት ሁኔታ፣”ድርድሩ ውጤታማ ይሆናል ወይ?” የሚለውን ለመመለስ ያስቸግራል። ድርድሩ ውጤት አያመጣም ብሎ መደምደምም ተገቢ አይሆንም፡፡ ውጤቱን በኋላ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ሂደት ከምንም በላይ ህዝቡ ለድርድሩ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ ይሄ ድርድር የሚካሄደው ለማንም አይደለም፤ ለህዝቡና ለሀገሪቱ ነው፡፡ ችግሮችንና ቅራኔዎችን ለመፍታት ነው ነው። ይሄ ከሆነ ህዝቡ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊከታተለው ይገባል፡፡ ከህዝቡ አሁን የሚጠበቀው ከሂደቱ ኢንፎርሜሽን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት አይደለም። ተቃዋሚውም ገዥውም ፓርቲ ከህዝብ ጥቅም አንፃር በኃላፊነት ስሜት እንዲደራደሩና ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡም የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ከየአቅጣጫው ጫና ማሳረፍ አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነና የፓርቲዎች ብቻ ጉዳይ አድርጎ ህዝብም ሚዲያውም የሚያየው ከሆነ፣ ድርድሩ ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም ወገን በቅርበት መከታተልና ጫና መፍጠር አለበት፡፡
ቀደም ሲል ህዝቡ ድጋፍ አላደረገም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ አደረጃጀቶች በሌሉበት፤ፓርቲዎች ህዝቡን ባላደራጁበት፣ ህዝቡ ሲባል የትኛው አካል ነው?
 ህዝብ ሲባል ሁሉም ህዝብ ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ 90 ወይም 100 ሚሊዮን ህዝብ ቢኖር፣ በተለያየ መልኩ በሃይማኖት ሊሆን ይችላል፣ በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሊሆን ይችላል ወይም በሲቪክ ማህበራት ሊኖር ይችላል-----ይብዛም ይነስም የተደራጀ የህብረተሰብ ክፍል አለ። ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የትምህርት ተቋማት፣ ሚዲያዎች አሉ፤ እነዚህ አካላት ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃንም አሉ፤ እነዚህ አካላትም ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ አልተደራጀም፣ ብዙው የገጠር ነዋሪ ስለሆነ ብዙም ግንዛቤው የለውም ልንል አንችልም፡፡ በርካታ የህብረተሰብን አመለካከትና ጥቅም የሚወክሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ገዥው ፓርቲ አሁን በራሱ ጊዜ ለድርድር ጥሪ ያቀረበበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ይሄ በሀገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ አደገኛ መሆኑን የተረዱ ኃይሎች ኢህአዴግ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ስለዚህ ከህብረተሰቡ ወኪሎች ጋር ቁጭ ብለን ካልተደራደርን በስተቀር ውሎ አድሮ የራሳችንም ሆነ የሀገሪቱን ህልውና ይፈታተናል በሚል ግንዛቤ ተነስተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ከሆነ እሰየው ነው። ወይም ደግሞ “አሁን ችግር ተፈጥሯል፤ ቢያንስ ለጊዜው ጉዳዩን ሊያረጋጋልን ይችላል” የሚል የፖለቲካ ጨዋታ ተፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁለቱ የትኛው ነው? ለሚለው ወደፊት የምናየው ይሆናል።
ተቃዋሚዎች በምን ጉዳይ ነው ሊደራደሩ የሚገባቸው? የድርድሩ ግብስ መሆን ያለበት ምንድን ነው?
መያዝ ያለባቸው አጀንዳዎች በየፓርቲው የሚቀርቡ መሆን አለባቸው፡፡ ግን ዋናው ግብ መሆን ያለበት ሳይደመር ሳይቀነስ፣ የዚህ ድርድር ውጤት የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ በራሱ የስልጣን ባለቤት መሆን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር መሆን ይኖርበታል፡፡ ዋናው ግብ ይሄ ነው፡፡ ወደዚያ ግብ በሚያደርሱን ጉዳዮች ላይ ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ነፃና ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት ያስፈልጉናል፤ ሚዲያ ያስፈልገናል፣ ሠብአዊ መብት መከበር አለበት፣ የፕሬስ መብት መከበር አለበት፡፡ ህዝቡ በነፃነት መደራጀት አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደምረው ነው ወደ ዋናው ግብ ሊያደርሱን የሚችሉት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ወደ ውይይት መጥተው መግባባት ላይ መደረስ አለበት፡፡ የመጨረሻው ውጤት በምርጫ የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤት ማድረግ መሆን አለበት፡፡
መንግስት “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሃገሪቱ ሠላም አስፍኗል” የሚለውን ከመደጋገሙ የተነሳ አንዳንድ ወገኖች አዋጁ ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚመጣ ሠላም በየትኛውም ሃገር ኖሮ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ሊኖር አይችልም፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጠረውን ቀውስ አግባብ ባለው የህግ አካሄድ ሳይሆን በጉልበት ማርገብ ችሏል፡፡ ይሄ ማለት ሠላም ተፈጥሯል ማለት አይደለም፡፡ ሠላም የሚፈጠረው በጥይት ሳይሆን በድርድር ውስጥ ነው፡፡
ጥያቄ ያነሱ ሰዎች፣ እስካሁን የተሰጣቸው መልስ የለም፡፡ በተቃውሞ እንቅስቃሴ ተሳትፎ የነበራቸው በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች እስር ቤት ነው የገቡት፡፡ በዚህ ሁኔታ ሠላም ተፈጥሯል ማለት ቀልድ ነው፡፡ አሁን ዘላቂ ሰላም አይደለም የተፈጠረው፡፡ እርግጥ ነው ድርድር፣ ውይይት እንዲካሄድ አንፃራዊ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ ይሄን ጊዜያዊ መረጋጋት በአስቸኳይ ተጠቅመን፣ ዘላቂ ውጤት ሊያመጣ ወደሚችል ድርድር ነው መግባት ያለብን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሠላም መጥፋት ዋና ማሳያ ነው እንጂ የሠላም መስፈን ምልክት አይደለም፤ሊሆንም አይችልም፡፡ ሌላውም አለም የሚረዳው በዚህ መልኩ ነው፡፡
ምንም ስራ ባልተሰራበት ይሄ አስቸኳይ አዋጅ ቢነሳ፣ተመልሰን ወደ ነበርንበት ቀውስ እንደምንገባ ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ለችግሩ መሰረታዊ መፍትሄ አልተሰጠም፡፡ መፍትሄ ባልተሰጠበት ሁኔታ ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡ አንዳንድ የመንግስት ካድሬዎች በየሚዲያው ‹‹ሠላም ተፈጥሯል›› የሚሉት የተለመደና የትም የማያደርስ አባባል ነው፡፡ ይልቁንስ ከዚህ ወጥተው ወደ እውነተኛ ድርድር መግባት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ መፍትሄ ወደ ማምጣት መሄድ አለባቸው፡፡ ያ ካልሆነ የሃገሪቱ ችግር እየተባባሰ ሄዶ፣ አጠቃላይ ህልውናዋን የሚፈታተን አደጋ ነው የሚያጋጥመን። በህልውና የመቀጠልና ያለ መቀጠል ጥያቄ ውስጥ ነው አሁን ያለነው፡፡
ወደ ዘላቂ መፍትሄዎች የሚያመራ አቅጣጫ ተይዟል ማለት ይቻላል?
ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ተጀምሯል፡፡ ግን ድርድሩ በዋናነት ተጀመረ የሚባለው፣ በአጀንዳዎች ላይ መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ ህዝቡም ምን ያህል የኔ ጉዳይ ነው ብሎ ይከታተለዋል የሚለውም ይወስነዋል፡፡ ሚዲያውም በሃላፊነት መከታተልና መዘገብ አለበት፡፡ የሃገሪቱ እጣ ፈንታ በፓርቲዎቹ ድርድር ላይ ነው ያለው፡፡ ይሄን መድረክ በአግባቡ ካልተጠቀምን፣ ይህቺ ሃገር ተመልሳ ወደ ብጥብጥ ልትገባ ትችላለች፡፡
በእርስዎ ግምገማ መሰረት፣መንግስት ችግሮችን በአግባቡ ለይቶ፣ ምላሽ ለመስጠት እየተጋ ነው?
ይህ አገር 25 ዓመት ሙሉ በመድብለ ፓርቲ ስርአት እየተመራ ነው፣ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ከተባለ በኋላ፣ የህግ የበላይነት ሰፍኗል ከተባለ በኋላ፣ ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ መረጋጋትና ሠላም አጥቶ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመተዳደር ለምን በቃ? የሚለውን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንደኔ በድርድሩም ላይ “ይሄ ለምን ሆነ?” የሚለው ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡ በዚህ ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ ካልተገኘ፣ የድርድሩ ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ------ የራሳቸው አባባሽ ሁኔታ አለባቸው፡፡ መሠረታዊው ችግር ግን እሱ አይደለም። መሰረታዊ ችግሩ የፖለቲካ ሙስና መኖሩ ነው፤ የኢኮኖሚ ሙስናውንም የፈጠረው እሡ ነው፡፡ እንደ መንግስት የሚካሄድ የፖለቲካ ሙስና ስላለ ነው የኢኮኖሚ ሙስና የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሙስና ሳይፈታ የኢኮኖሚ ሙስና እንፈታለን ቢባል ዋጋ የለውም፡፡ አሁን ኢህአዴግ እየነካካው ያለው የፖለቲካ ሙስናውን ተንተርሳ የመጣችውን የኢኮኖሚ ሙስና ነው፤ ከዋናው መሠረታዊ ችግር ሸሽቷል፡፡ ስለዚህ ይሄ በድርድሩ እንዲነሳ እንፈልጋለን፡፡ የኢኮኖሚ ሙስና መኖሩን አምኖ፣ ችግር ነው ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ግን ዋናውንና መሰረታዊውን የፖለቲካ ሙስና እስካሁንም ችግር ነው ብሎ አላመነም፡፡ ይሄን ማመን አለበት፡፡ አምኖ ካልተቀበለ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት አይችልም። በድርድሩ ለፖለቲካ ሙስና ትኩረት መሰጠት አለበት፤ ኢህአዴግ “ለምንድን ነው በዙሪያዬ የሰበሰብኩት ሰው ሁሉ በሙስና የተጨማለቀው?” የሚለውን መጠየቅ አለበት፡፡ አብዛኛው ጥቅም ማጋበስ የሚፈልግ እንጂ ህዝቡን ለማገልገል ብሎ የመንግስትን ሥልጣን የያዘ አይደለም፡፡ ይሄን ሃይል ይዞ የትም መድረስ አይችልም፡፡ ሰዎች የመንግስት ሰራተኛና የህዝብ ባለስልጣን መሆን ያለባቸው በፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ብቻ አይደለም፡፡
ለሃገርና ለህዝብ ቆሜያለሁ የሚል ፓርቲ፣ ለሃገር ጥቅም ሲባል ስልጣኑንም የሚያጣ ከሆነ በጸጋ መቀበል መቻል አለበት፡፡ መጀመሪያ የራሱን የስልጣን የበላይነት ማስጠበቅ የሚለው፣ ከዚህ በኋላ አያስኬድም፡፡ የህዝብ ወገንተኝነት ቅድሚያ ስልጣንን ማስጠበቅ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለበት፡፡

Read 2576 times