Sunday, 12 February 2017 00:00

ሶማሊያ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ፕሬዚዳንት መርጣለች

Written by 
Rate this item
(10 votes)

   የዚያድ ባሬን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ እንደ አገር መቆም ተስኗት አሳር መከራዋን ስትቆጥር የዘለቀቺው፣ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የጽንፈኛ ቡድኖች ጥቃት፣ ድርቅና ርሃብ እየተፈራረቁ ያደቀቋት ሶማሊያ፤ ከ25 አመታት በኋላ ሰሞኑን ታሪካዊ የተባለውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አከናውናለች፡፡በሙስና የታማው፣ በሽብር ስጋት የታጀበው፣ ተስፋ የተጣለበትና ለወራት የዘለቀው የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት፣ ባለፈው ረቡዕ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡የተረጋጋች አገር፣ የተሻለ ኑሮ፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም፣ ብልህና አዋቂ መንግስት፣ ከትናንት የተሻለ ነገ የናፈቀው የሶማሊያ ህዝብ፣ ነገውን የሚወስንለትን ወሳኝ ሰው፣ ቀጣዩን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ለማወቅ ጓጓ፡፡“ማን ይሆን ተረኛው?...” ሲል ጠየቀ፡፡
“ፎርማጆ ነው!...” አለ የምርጫ ውጤቱ፡፡
የሶማሊያ ዘጠነኛው ፕሬዚዳንት በመሆን መንበረ ስልጣኑን ለመረከብ የተመረጠው ወሳኙ ሰው፣ ፎርማጆ ነው፡፡
“ሶማ-አሜሪካዊ”ው ፎርማጆየምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በርካታ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን፣ ምርጫውን በተመለከተ ያወጧቸው ዘገባዎች ርዕሶች ተመሳሳይና ስላቅ ቢጤ ያዘሉ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ዘገባዎች ከአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ስም ጋር፣ የጥምር ዜግነት ባለቤትነታቸውንም ጭምር በማጉላት የተቀናበሩ ናቸው፡፡እርግጥ ነው...
ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ያልተለመደ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ህግ ግን የሌላ አገር ዜግነት ያለው ሶማሊያዊ በፕሬዚዳንትነት እንዳይወዳደር የማያግድ ነውና፣ ጉዳዩ ከጊዜያዊ ግርምት አልፎ ፖለቲካዊ ጥያቄ አላስከተለም፡፡ በምርጫው ያሸነፉት የሶማሊያና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የ55 አመቱ ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2011 በነበሩት ስምንት ወራት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ፎርማጆ፣ በ1993 በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ በ2009 ደግሞ ከስቴት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ፣ በፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡በዋሽንግተን የሶማሊያ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉትና የአራት ልጆች አባት የሆኑት ፎርማጆ፤ እ.ኤ.አ ከ1985 አንስቶ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ
ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውም አሁንም ድረስ በአሜሪካ ነው የሚገኙት፡፡
“አዲሲቷን ሶማሊያ እፈጥራለሁ፣ በጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ ላይ እዘምታለሁ፣ ከአለም አንደኛ አድርጎ ስማችንን በአጉል የሚያስጠራውን ሙስናን በቁርጠኝነት እዋጋለሁ!...” ሲሉ ቃል ገብተዋል፤ ፎርማጆ ድላቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፡፡ድምጽ 100 ሺህ ዶላር ይሸጣል!...
የሶማሊያ ምርጫ ስርዓት በአንዳንድ አገራት ቢሰራበትም፣ ከተለመዱት የምርጫ ስርዓቶች ወጣ ያለ ነው፡፡
በመጀመሪያ የአገሪቱ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች፤ የፓርላማ አባላትንና ሴናተሮችን ይመርጣሉ፡፡ እነዚሁ ተመራጮች በተራቸው፣ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት ለቀረቡ ተወዳዳሪዎች ድምጻቸውን ይሰጣሉ፡፡ በሶስት ዙር በሚሰጥ ድምጽ በሚደረግ ማጣሪያም
አሸናፊው ፕሬዚዳንት ይለያል፡፡በዚህ መልኩ በተከናወነው የዘንድሮው ምርጫም 14 ሺህ ያህል የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የመረጧቸው 329 የፓርላማ አባላትና ሴናተሮች፣ በተወዳዳሪነት ለቀረቡት 21 ዕጩዎች ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡በስተመጨረሻም...
በስልጣን ላይ የቆዩትና ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ይቀጥላሉ የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ሃሰን ሼክ ሙሃሙድ 97 ድምጽ በማግኘት ሽንፈትን ሲያስተናግዱ፣ ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፎርማጆ ፎርማጆ 184 ድምጽ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡ይህም ሆኖ ግን...
ታሪካዊ የተባለው ምርጫ በሙስና መታማቱ አልቀረም፡፡ተቀማጭነቱ በሞቃዲሾ የሆነው ማርካቲ የተባለ የጸረ ሙስና ተቋም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት፤ በምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ፣ መራጮች በገንዘብ ተደልለው ድምጻቸውን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብሏል፡፡በዚህ መልኩ በሙስና ድምጻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የህዝብ ተወካዮች፣ የመራጭነት መብታቸውን ከመገፈፍ አንስቶ እስከ ግድያ የሚደርስ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው እንደተዛተባቸውም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡አንዳንድ የህዝብ ተወካዮች ለአንድ የፓርላማ አባል ድምጻቸውን ለመስጠት፣ እስከ 30 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በሙስና መልክ እንደተሰጣቸውና፣ በፕሬዚደንትነት ለመወዳደር የቀረቡ አንዳንድ ዕጩዎች በበኩላቸው፤ የፓርላማ አባላቱ እንዲመርጧቸው  እስከ 100 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ መደለያ (ጉቦ) እንደሰጡም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ አውሮፕላን ጣቢያ - ምርጫ ጣቢያበአለማችን የምርጫ ታሪክ በአውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ የተከናወነ የመጀመሪያው ምርጫ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል - የሰሞኑ የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፡፡የአገሪቱን አንድ ሶስተኛ ግዛት ያህል ተቆጣጥሮ የሚገኘው ጽንፈኛው ቡድን አልሻባብ፣ የሽብር ጥቃት በመፈጸም ምርጫውን ሊያስተጓጉል ይችላል ተብሎ በመሰጋቱ ሳቢያ፣ የምርጫ ስነስርዓቱ በሞቃዲሾ በሚገኝ የፖሊስ አካዳሚ ቅጽር ግቢ ውስጥ እንዲደረግ ነበር የታሰበው፡፡ በኋላ ላይ ግን፣ የተሻለ የጸጥታ ሁኔታና የተጠናከረ ጥበቃ ያለበት ስፍራ መፈለግ እንዳለበት ተወሰነ፡፡ በዚህም መሰረት ምርጫው በአገሪቱ እጅግ የተጠናከረ ጥበቃ ያለበት ስፍራ እንደሆነ በተነገረለት የሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡አልሻባብ የምርጫ ሂደቱን ለማወክ መሞከሩ አይቀርም የሚለው ስጋት እንቅልፍ የነሳው የአገሪቱ መንግስት፣ በሞቃዲሾ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለ8 ሰዓት ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ ከማድረግ ባለፈ፣ የሞቃዲሾ አውሮፕላን ጣቢያም መጪም ሆነ ሂያጅ አውሮፕላንን ላያስተናግድ ተዘግቶ ነው የዋለው፡፡ህዝቡ ፈንድቋል...
የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን በመዲናዋ ሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት በደስታ ሲፈነጥዙ ታይተዋል፡፡ በፎርማጆ ማሸነፍ የፈነደቁ ወታደሮችም በደስታ ተኩስ፣ ሞቃዲሾን ሲያደምቋት አምሽተዋል ተብሏል፡፡ሰውዬው ምንም እንኳን የዳሮድ ጎሳ አባል ቢሆኑም፣ የተሻለች አገርን ተስፋ ያደረጉ ሶማሊያውያን ግን፣ ጎሳ ሳይለዩ አደባባይ በመውጣት ለፕሬዚዳንቱ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡ በኬንያ ዳባብ የስደተኞች ካምፕ የሚገኙ በርካታ ሶማሊያውያንም ደስታቸውን እንደገለጹ ተዘግቧል፡፡



Read 5045 times