Sunday, 12 February 2017 00:00

የአ.አ ከተማ አስተዳደር የአውቶቡስ ዴፖና ጋራዦችን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በ1.4 ቢሊዮን ብር ሊያስገነባ ነው

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፤ ዘመናዊ የአውቶቡስ ዴፖና ጋራዦችን በ1.4 ቢሊዮን ብር ሊያስገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ጽ/ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፤ የከተማ መስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን እንደሆነ ጠቅሶ፣ በሦስት አበይት ጉዳዮች  (የትራንሰፖርት መሠረተ ልማት ማስፋፊያ፣ የብዙኃን ትራንስፖርት አቅርቦት ጥራትና የትራፊክ
ደኅንነት ፍሰት ማሻሻል) ላይ አተኩሮ በመሥራት ላይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የብዙኃን ትራንስፖርት ማሻሻል የሚቻለው የአውቶቡሶችን አቅርቦት በመጨመር ብቻ ሳይሆን የቀረቡትን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መልኩ
መጠቀም ሲቻል መሆኑን የጠቀሰው ጽ/ቤቱ፤ ለዚህም በከተማዋ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ጋራዦችን የያዙ፣ በተቀናጀ መልኩ ከአንድ ቦታ ስምሪት የሚሰጡ፣ የአውቶቡሶችን ንፅህናና ደህንነት የሚያስጠብቁ ዴፖዎችን መገንባትና ለሁሉም የብዙኃን ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅቶች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው ብሏል፡፡በመንገድ መሰረት ልማት ማስፋፋት ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት፣ የመንገድ ሽፋንና ጥራት ማሻሻል፣ የተለያዩ የመኪና ማቆሚያዎችን መገንባትና ማስፋፋት፣ መናኸሪያዎችንና ተርሚናሎችን መገንባት፣ ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ዴፖዎችና ጋራዦችን
መገንባትና የመሳሰሉት እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ የአውቶቡሶች ዴፖዎችና ጋራዦች በሚገነቡበት ስፍራዎች ትናንት የከተማዋ ከንቲባ ክቡር ዲሪባ ኩማ፤ የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው ታውቋል።
የአውቶቡስ ዴፖዎቹና ጋራዦቹ የሚገነቡት በአቃቂና በሸጎሌ ሲሆን ግንባታውን ለማከናወን በ1.4 ቢሊዮን ብር ወጪ ጨረታውን ያሸነፈው በኮንስትራክሽን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያው፣ በ20 ወራት ግንባታውን አጠናቅቆ ለማስረከብ ተዋውሏል ተብሏል፡፡
ዴፖዎቹ እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ ከ250 እስከ 300 አውቶቡሶች ማቆም የሚችሉ ሲሆን በውስጣቸው የተሟላ ዘመናዊ ጋራዥ፣ የአውቶቡስ ማጠቢያና ማድረቂያ፣ የነዳጅ ማደያዎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የሠራተኞች መዝናኛ ሕንፃዎች እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡

Read 1272 times Last modified on Saturday, 11 February 2017 12:52