Sunday, 12 February 2017 00:00

የርዕዮት ዓለም ውልደት፣ ሞትና ትንሳኤ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(4 votes)

የርዕዮት ዓለም ውልደት
በሰው ልጅ የነፃነት የትግል ታሪክ ውስጥ የፈረንሳይ አብዮት የጉልላቱን ሥፍራ እንደሚይዝ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡ ጭቁን ፈረንሳዊያን እኩልነት፣ ወንድማማችነትና ነፃነትን የመሳሰሉ የፖለቲካ አጀንዳዎችን እንደ ሰንደቅ በአደባባይ እያውለበለቡ፣ በወቅቱ የነበረውን ቅምጥል የፊውዳል ሥርዓት ከሥሩ በመመንገል ለተቀረው ዓለም ፋና ወጊ መሆን ችለዋል፡፡
የፈረንሳይ አብዮት ይዞት ብቅ ካለው               ፀጉረ ልውጥ የፖለቲካ አጀንዳ ጎን ለጎን ርዕዮት ዓለም /ideology/ የተባለውን ጽንሰ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በ ዲ አንቶኒዮ ዴስቲቱዩት ዲ ቲሬሲ ጠንሳሽነት እንዳስተዋወቀ የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ። የአብዮቱ አቀንቃኝ ዲ ቲሬሲ፤ ርዕዮት ዓለምን በአምክንዮ ከሚመራ ፖለቲካዊ ስርዓት ጋር አወዳጅቶ ነው የተነተነው፡፡ የዕውቀትና የሥልጣን ምንጭ የነበረው የጥንቱ የጠዋቱ ዕምነት፣ ግብዓተ ቀበሩ ስለተፈጸመ፣ ልክ እንደ ሳይንሱ ሁሉ የፖለቲካውም ዓለም ሊመራበት የሚገባ አንድ ወጥ አምክኖዊያዊ መርህ ያስፈልገዋል በሚል እሳቤ ርዕዮት ዓለም /ideology/ ሊወለድ ችሏል፡፡
ምንም እንኳን ርዕዮት ዓለምን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቀው ፈረንሳዊው ፈላስፋ አንቶኒዮ ዲ ቲሬሲ ቢሆንም ትክክለኛውን ታሪካዊ ፈር በማሲያዝና ሁለንተናዊ ትንተና በማቅረብ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጀርመናዊው ቁስ አካላዊው ፈላስፋ ካርል ማርክስ ነው፡፡ ካርል ማርክስ ርዕዮት ዓለምን ከመደብ ባህሪ ጋር ያቆራኘዋል፡፡ በካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ የላብ አደሩና የከበርቴው መደብ ማዶ ለማዶ፣ በተጻራሪ ኢኮኖሚያዊ እርከን ላይ ይሰለፋሉ። የርዕዮት ዓለም ዋንኛ ግብ የላብአደሩን ንቃት መስለብ ነው፡፡ ላብአደሩ ከከበርቴው/ከቡርዣው/ የሚጣልለትን ዳረጎት፣ አሜን ብሎ እንዲቀበል እውነታውን ማጥበረበር ወይም “ፎልስ ኮንሸስነስ” መፍጠር የርዕዮት ዓለም ተቀዳሚ ሥራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ላብ አደሩ በከበርቴው የኢኮኖሚ መደብ የሚዘወርን ስርዓት በአብዮት ገርስሶ፣ አዲስ ሕዝባዊ ሶሻሊስታዊ ስርዓት ሲዘረጋ፣ ርዕዮት ዓለምም በእዛው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያከትማል፤ይላል ካርል ማርክስ፡፡
ካርል ማርክስ ያስተዋወቀው ርዕዮት ዓለም እንዳከተመ በአደባባይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞገተው፣ አሜሪካዊው ዳንኤል ቤል በ1960 ዎቹ መባቻ ላይ ነበር፡፡ በእዚያ ዘመን በምዕራባዊያን መካከል ያለው የርዕዮት ዓለም ልዩነት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በመጣፍ፣ ቤል የርዕዮት ዓለምን መፈራረስ በይፋ ለማወጅ ተሽቀዳደመ፡፡
የኢኮኖሚ መደብን /class/ የሙጥኝ ያለው የማርክስ ርዕዮት ዓለማዊ ትንተና፣ የሃያኛው ክፍለ ዘመንን ውጥንቅጥ ነባራዊ ሁኔታ የመግለጽ አቅም የለውም፡፡ የሃያኛው ክፍለ ዘመን የሰው ዘር ከማርክስ የመደብ ባህሪያት በላቀ ደረጃ ስሜቱን ሰቅዞ የሚይዘው ሌላ ማንነትን አዳብሯል፡፡ የዘመናችን የሰው ዘር ከካርል ማርክስ የኢኮኖሚ መደብ ይልቅ  በጾታ ማንነቱ፣ በዘር ቅርርቡ የበለጠ መሰባሰብን ይመርጣል፡፡ የማርክስ የመደብ ማንነት በእዚህ ዘመን እዚህ ግባ የሚባል ሥፍራ የለውም። ስለዚህ ርዕዮት ዓለምን ለመተንተን እንደ ዋንኛ መሣሪያ ልንጠቅምበት አይገባም፡፡ በማለት ማርክሳዊ የርዕዮት ዓለም ትንተና አፈር መልበሱን ይፋ ሊያደርግ ችሏል፡፡
የቤል የርዕዮት ዓለም ማክተመ ትንተና /end of idology thesis/ ይበልጥ የጎመራው በፍራንሲስ ፍኩያማ የታሪክ መቋጫ ትንታኔ /end of history thesis/ ነበር፡፡ በ1989 እንደ ጎሮጎሮሳዊያን ዘመን አቆጣጠር፣ የቀዝቃዛው ጦርነትን ማብቃት ተከትሎ ፉኩያማ አንድ አነጋጋሪ ድርሳን ይዞ ብቅ አለ፡፡ ሊኅቁ በእዚህ አነጋጋሪ ድርሳኑ፣ የርዕዮት ዓለም ሹክቻ ጊዜው ያለፈበት ጉዳይ እንደሆነና የሊብራሊዝም ርዕዮት ዓለም ያለምንም ተቀናቃኝ በሁሉም የዓለማችን ጥግ እንደሚንሰራፋ ያትታል፡፡
ፍኩያማ የተናገረው ገና ከአፉ ሳይወድቅ ድፍን የዓለም ሕዝብን ያሸማቀቀው የሽብር ጥቃት በወረሃ መስከረም 2001 እ.ኤ.አ ላይ በርካታ የአሜሪካ ንጽሓን ዜጎችን ሕይወት ቀጠፈ፡፡ በጥቃቱ የዓለማችን ግዙፍ የንግድ ማዕከል የሆኑት መንትያዎቹ የኒውዮርክ ዎርክ ማማዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀየሩ፡፡ ይህ መሬት አንቀጥቅጥ የሽብር ጥቃት በሶሻሊዝም ርዕዮት ዓለም እግር ተተክቶ፣ ምዕራባውያንን ቁምስቅል የሚያሳይ ተገዳዳሪ ልዩ ኃይል እውን እየሆነ እንደሆነ ምልክት መስጠቱ ነበር፡፡
ከሽብር ጥቃቱ ማግሥት የወቅቱ የአሜሪካ መሪ ትልቁ ቡሽ፤ ስለ ነፃነትና ዲሞክራሲ አስፈላጊነት ተደጋጋሚ ዲስኩር አሰሙ፡፡ “አሸባሪዎቹ አሜሪካንን ሳይሆን በሰው ልጅ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ላይ ነው ጦርነት ያወጁት” ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቱ፡፡
የመስከረሙ ወር የሽብር ጥቃት ከሁሉም በላይ ያስተላለፈው መልዕክት፣ ኃይማኖታዊ መልክን የተላበሰ አዲስ ርዕዮት ዓለም የወደፊቱ የምዕራባዊያን ተቀናቃኝ ኃይል ሆኖ እንደሚመጣ ነው፡፡ ባለንበት ዘመን በየትኛውም የዓለም ጥግ ያለ የሰው ዘር ከሚፈረጅበት የኢኮኖሚ መደብ ይልቅ ለሚጎዳኝበት ባህል ስስ መሆንን ይመርጣል። አልቃይዳ፣ አይሲስ፣ አልሻባብ፣ ቦኮሐራም እየተባሉ የሚጠሩት ጽንፈኛ ሃይማኖታዊ የሽብር ቡድኖች፣ ከምዕራባዊያን ሊብራል እሴት ጋር ፊት ለፊት የሚላተሙ ኃይሎች መሆናቸውን ዓለም ካወቀ ሰነበተ፡፡ እነዚህን ተጨባጭ ኹነቶች ታሳቢ በማድረግ፣ ርዕዮት ዓለም ቆዳ ቀይሮ በሌላ ገጽታ ብቅ አለ እንጂ ፈጽሞ አልሞተም ብለው የሚሟገቱ ልሂቃን አልጠፉም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሳሙኤል ሀንቲግተን ነው። ሳሙኤል ሀንቲግተን በ”ክላሽ ኦፍ ሲቪላዜሽን” መጽሐፉ፣ የፍኩያማን ችኩል ድምዳሜ የሚያመክን ግሩም የመልስ ምት ሰጥቷል፡፡
በሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ርዕዮት ዓለም ካምፕ ተከፋፍሎ፣ ማዶ ለማዶ መሻኮት የቀዝቃዛው ጦርነት መቋጫ ባገኘ  ማግሥት መልኩን ቀይሯል። በሶሻሊዝም እግር ተተክቶ የምዕራባዊያንን ርዕዮት ዓለም እየተገዳደረ ያለው ባህል እንደሆነ ሀንቲግተን በበርካታ ማሳያዎች ትንታኔውን ያቀርባል፡፡ ለዚህም እንደ ዋቢ የሚጠቀምበት ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖች፣ በሁሉም የዓለም ክንፍ በዘመነ ሉላዊነት/ግሎባላይዜሽን/ እምባጭ ሆነው መታየታቸው ነው።
የርዕዮት ዓለም ትንሳኤ
የልሂቃንን ውርጅብኝ በተለያየ ዘመን ያስተናገደውን የካርል ማርክስን ለሕጸጽ የተጋለጠ ትንተና በማከም፣ ጽንሰ ሐሳቡ በአዲስ መልክ እንዲወለድ እስትንፋስ የቀጠለለት ፈላስፋ ፈረንሳዊው ሊዊስ አልዙሰር ነው፡፡ ይህ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ተጽእኖ ፈጣሪ ልሂቅ፣ ርዕዮት ዓለምን ከሰዋዊ ባሕሪ ጋር ያስተሳስረዋል፡፡ ቀለም፣ ዘርና ሥልጣኔ ሳይለይ በሁሉም የሰው ልጅ ዘንድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚከወን ዘላለማዊ እውነታ ነው፡፡ ትናንትም፣ ዛሬም ወደፊትም ኅያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ርዕዮት ዓለም የማይረግጠው ሥፍራ የለም፡፡ ስለ ሕይወት ያለን አመለካከት፣ የምናራምደው እምነት፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችን በሙሉ በርዕዮት ዓለም ምርኮ ሥር ከመውደቅ አይድኑም ፡፡
Ideology for Althusser is a system (with its own logic) of representations (images,myths,ideas or concepts,depending on the case) endowed with a historical existence and role within a given society.
ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አርሲጣጢለስ፤ “የሰው ልጅ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ብሎ ያኖረው ዘመን ተሻጋሪን ምልከታ፣ አልዙሴር ባልታየ አቅጣጫ መልክ አበጅቶ ይተነትነዋል፡፡ የሰው ልጅን ያለ ፖለቲካ መኖር እንደማይችል ካመንን፣ የርዕዮት ዓለምን ሕያውነት በሌላ ግልባጭ መቀበል ውሃ የሚያነሳ አምክንዮ ነው። “human being is ideological” ብሎ ጨምሮ ያስረግጣል፡፡
ከአልዙሰር በተጨማሪ የርዕዮት ዓለምን ሕያውነት አጥብቀው የሚሞግቱት የድህረ ማርክሲዝም /Post-marxism/ አቋም የሚያራምዱ ልሂቃን ናቸው፡፡ በእዚህ ዘውግ የሚሰለፉ ፈላስፎች በቅድሚያ በዘመናችን የናኘውን ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ በፀጋ ይቀበላሉ፡፡ በመቀጠል ይህን ዝብርቅርቅ አጀንዳ በአንድነት አሰልፎ፣ ተገቢውን የተግባር መፍትሄ የሚሰጠው ርዕዮት ዓለም ብቻ እንደሆነ በጠንካራ ማስረጃ በተደገፈ ምልከታቸው ይታትራሉ፡፡
እኛ እና ርዕዮት ዓለም
የፖለቲካ ርዕዮት ዓለምን ከሀገራችን ተጨባጭ እውነታ አንጻር በቅጡ ለመፈተሽ በምንሞክርበት ጊዜ ብዙ ውጥንቅጥ ተሞክሮዎችን እናስተውላለን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአውፓዊያን የቅኝ ግዛት ዳፋ ብትተርፍም፣ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የርዕዮት ዓለም ቤተ-ሙክራ ከመሆን ግን አልዘለለችም፡፡
ቅኝታችንን ከወታደራዊ የደርግ አገዛዝ ስርዓት እንኳን ብንጀምር፣ ይህንን ገሃድ ሃቅ በደንብ ለመረዳት አንቸገርም፡፡ ደርግ በጥራዝ ነጠቅ ሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ሀገሪቱን በደምሳሳው እያንደረደረ፣ አሥራ ሰባት ዓመታትን እንደዋዛ አዘገመ፡፡ ሶሻሊስታዊ ርዕዮት ዓለም በአንድ ሀገር ላይ ለመተከል በቅድሚያ የካፒታሊዝም ስርዓት ሊጎመራ ይገባል፡፡ በእዚህ ኡደቱን ጠብቆ ከሚገባው ደረጃ ላይ በደረሰ የካፒታሊዝም ስርዓት ውስጥ ሁለት በተቃራኒ ጫፍና ጫፍ የተሰየሙ የከረረ ጠብ ያላቸው የኢኮኖሚ መደብ ክፍል ይፈጠራሉ። እነዚህም ላብአደሩና የከበርቴ መደብ ናቸው፡፡ ላብአደሩ በደሙና በወዙ፣ ነፃነቱን ሊጎናጸፍ መሬት አንቀጥቅጥ አብዮትን ያውጃል፡፡ ማሳረጊያውም ለሰፊው ላብአደር ደህንነትና ጥቅም የሚሠራ የፖለቲካ ሥርዓት እውን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ደርግ እንደግዲህ ይህንን ሁሉ ተጨባጭ እውነታን የሚረዳበት የዕውቀትም ሆነ የልምድ ተሞክሮ ስላልነበረው ከፊት ለፊቱ ያገኘውን ሶሻሊስታዊ ርዕዮት ዓለም፣ እንደ ዘመኑ ልኂቃን ጥቅስ በመደርደር፣ ደርሶ አብዮተኛ ለመሆን ተጣደፈ። ትርፍ ጭቃ ቤቶችን በአድኃሪያን ስም እየወረሰ፣ ለሰፊው ጭቁን ሕዝብ መቆሙን በይፋ አወጀ። ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማይገጥም የርዕዮት ዓለም ቤተ ሙከራ፣ በክሽፈት ተዳፋት ላይ እየተካለበ ማሳረጊያው ውድቀት ሆነ፡፡
የርዕዮት ዓለም ቤተ ሙከራው ከደርግ ውድቀት ማግሥትም መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ነው። ከተለያዩ ርዕዮት ዓለም ተዋጽኦ የተዋቀረው አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ለእዚሁ ማስረጃ ሆኖ መቅረብ ይችላል። አብዮታዊው ዲሞክራሲ ውሎ አድሮ ልማታዊ መንግሥትን ወለደ፡፡ የቤተ-ሙከራው ቀጣይ ክፍል መሆኑ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከደርግ በተለይ ለስነልቦናዊ ቅኝት ጉልህ ሥፍራን እንደሚሰጥ ምስክር የሚሆኑን ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእዚህ ውስጥ የብሔር ማንነት ጉዳይ ተጠቃሽ ነው፡፡ የኢህአዴግ የርዕዮት ዓለማዊ ቅኝት ማኅለቁን የጣለው ብሔር ብሔረሰብ በሚለው አደናጋሪ ጽንሰ ሐሳብ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እዚህ ጋ ርዕዮት ዓለምን በስነልቦናዊ መነጽር ግሩም አድርጎ የተነተነውን ስሎቬኔያዊውን ስላቮዥ ዢዤክ ዋቢ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡
According to zizek, all ideologies turn around certain ‘sublime objects’ of subjects’ belief. These are objects named by what zizek call the ‘master signifiers’ of a particular regime, master signifiers like ‘the American people’, ‘the Soviet Cause’, ‘freedom’, the Serbian /Croatian/Albanian nation’.  እንግዲህ በስላቮዥ ዢዤክ ትንተና መሠረት፤ ማንኛውም ርዕዮት ዓለም የሚደገፈው አንጓ አጀንዳ ወይም ‘sublime objects’አለ፡፡ “አሜሪካዊነት” የሚለው ማንነት በሪፐብሊካንም ሆነ በዲሞክራት የፖለቲካ ፓርቲ ዘንድ ከሁሉም ልቆ ከቁጥር የሚጣፍ አጀንዳ ነው፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኦባማ፣ ለምርጫ ቅስቀሳ የተጠቀሙበት መሪ መፈክር፡- “yes we can” እና የትራምፕ “Make America Great Again” አሜሪካዊ ብሔርተኝነትን ወይም ሀገራዊ ማንነትን የበለጠ ለማራገብ የተነደፉ ፖለቲካዊ ቀመሮች ናቸው፡፡ አሜሪካዊያን ከብሔር ማንነት ይልቅ ለሀገራዊ አርበኝነት የሚሰጡት ቦታ ትልቅ መሆኑን ፖለቲከኞቹ ጠንቅቀው ስለሚረዱ የርዕዮት ዓለማቸውን ቅኝት በእዚሁ ማዕቀፍ ዙሪያ ያሾሩታል።
በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን፣ “ከእኛ ኢትዮጵያን” ይልቅ “እኛ ብሔር ብሔረሰቦች” የሚለው ስነልቦናዊ ቅኝት፣ ርዕዮት አለሙን ቀስቶ ያቆመው ወጋግራ ነው፡፡ በዢዤክ የርዕዮት ዓለም ትንተና መሠረት፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲም ሆነ ልማታዊነት ከብሔር ማንነት ውጭ ምንም እንዳልሆኑ እንረዳለን፡፡

Read 2836 times