Sunday, 12 February 2017 00:00

ብዙ መከራ አልፋ ስኬት የተቀዳጀች ስደተኛዋ ኢትዮጵያዊት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ወደዚህ ዓለም የመጣችው በኃይል ጥቃት ነው። እናቷን አንድ ሻምበል አስገድዶ ይደፍራታል። በዚያው ጥቃት ተፀነሰች፡፡ እንደማንኛውም ህፃን ከ9 ወር በኋላ በደብረማርቆስ ከተማ ተወለደች። እንደ ወጉ ቢሆን ህፃን ልጅን እናትና አባት ነበሩ የሚያሳድጉት፡፡ እሷ ግን ለዚህ ፀጋ አልታደለችም። አባቷን ስለማታውቅ እናቷ ብቻዋን አሳደገቻት - መንበረ አክሊሉን፡፡
አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ነዋሪ የሆነችውን ወ/ሮ መንበረን አግኝቼ ይህንን ቃለ ምልልስ ያደረግነው፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የሊንከን ኮሌጅ ለ6ኛ ዙር ኤምቢኤ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ያስተማራቸውን 45 ተማሪዎች በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ባስመረቀበት ወቅት የቢዝነስ ተሞክሮዋን፣ ያሳለፈችውን መጥፎ ህይወትና አሁን የደረሰችበትን ስኬት ለተማሪዎቹ እንድትናገር ዩኒቨርሲቲው ጋብዟት መጥታ ነው፡፡
እናቷ ብቸኛ በመሆንዋ የራሷንና የልጇን ህይወት ለመለወጥ ትፍጨረጨር ነበር፡፡ ኑሮዋን ለማሸነፍ ጠጅ ንግድ ጀመረች፡፡ የጠጅ ንግዱ ደራላት፡፡ “የማገኘው ገንዘብ ለልጄና ለራሴ ኑሮ ይበቃናል፡፡ ተመስገን! ይህንኑ ይባርክልኝ” ብላ አልተቀመጠችም፡፡ እንዲያውም ኮማሪትነትን አጧጧፈችው፡፡
ጥረቷ ሰመረላትና ጠጅ ቤቱን ወደ ሆቴልነት ለወጠችው፡፡ ሆቴሉን ከፍታ ያለ ዕረፍት ስትሰራ ገበያው ደራላት፡፡ ደንበኞቿን ለማስደሰት ሌት ተቀን ስትጥር አንድ ቀን ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ፡፡ በመጠጥ ቤቱ ሲጠጣ የቆየ አንድ ሻምበል ሰክሮ፤ “ሂሳብ አልከፍልም” በማለት አምባጓሮ ፈጠረ። በዚህ ጊዜ “የተጠቀምከውን ሂሳብማ ልትከፍለኝ ይገባል” በማለት ፖሊስ ስትጠራ፣ የታጠቀውን ሽጉጥ አውጥቶ ተኩሶ ገደላት፡፡
መንበረ በዚያን ወቅት የ10 ዓመት ልጅ ስትሆን፤ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ት/ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ እናቷ ስትገደል አይታለች፡፡ አሁን ወላጅ አልባ ሆነች፡፡ በዚህ ጊዜ አዲስ አበባ የነበሩት ታላቅ ወንድሟና ታላቅ እህቷ እናሳድጋታለን ብለው አመጧት፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ገብታ ትምህርቷን እስከ 12ኛ ክፍል ተማረች፡፡
ታላቅ ወንድሟ “ዩኒቨርሲቲ ገብተሽ ትምህርትሽን ቀጥይ” ብሏት ነበር፡፡ እሷ ግን “ተዋናይ መሆን ነው የምፈልገው” ብላ አሻፈረኝ አለች፡፡ እንደፈለገችው የትወና ትምህርቱን ተከታትላ ተዋናይ ሆነችና ብሔራዊ ቴአትርና ራስ ቴአትር ተቀጥራ ሰራች፡፡
በዚህ ወቅት አለቃዋና የልጇ አባት ከሆነው ሰው ጋር ተዋውቃና ተግባብተው ፍቅር ጀመሩ፡፡ ፍቅረኛዋ ስኮላርሺፕ አግኝቶ ጣሊያን ከሄደ በኋላ፣ “ታዋቂ ተዋናይ መሆን ትችያለሽና እዚህ ነይ” ብሎ የግብዣ ወረቀት ላከላት፡፡ እሺ! ብላው ጣሊያን ሄደች፡፡ ቤተሰቦቿ (እህትና ወንድሟ) ወደ ጣሊያ መሄዷን አልወደዱም ነበር፡፡ ምክንያቱም እዚህም እያሉ ፍቅረኛዋ ጥሩ ሰው እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ይጎዳትና ይደበድባት ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ አፍንጫዋን ሰብሯት ሆስፒታል ሁሉ ገብታ ነበር። በዚህ የተነሳ ተከትላው እንድትሄድ ስላልፈለጉ “ይቅርብሽ” ብለዋት ነበር፡፡
መንበረ ግን የወንድምና የእህቷን ምክር አልተቀበለችም፡፡ ወጣትነት፣ ፍቅርና ከሀገር የመውጣት ፍላጎቱ ተደማምረው ተከትላው ኢጣሊያ ሄደች፡፡ ሮም ከተማ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ የፍቅረኛዋ ባህርይ ግን አልተለወጠም፤ እንዲያውም ባሰበት፡፡ ሮም በደረሰች ሦስተኛ ወሯ ፀነሰች፡፡ ፍቅረኛዋ ይደበድባትና ይጎዳት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ፊቷንና ክንዷን በሲጋራ አቃጠላት፡፡ ዘጠኝ ወር ሲሞላትም ጉዳትና ድብደባው አልቀረላትም፡፡ እንዲያውም ሊገድላት ይፈልግ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ ግፉ ስለበዛባት ከቤት ወጥታ ጠፋች፡፡
ለመውለድ 6 ቀን ነበር የቀራት፡፡ ገንዘብ የላት፣ ቋንቋ አታውቅ፣ የምትጠጋው ዘመድ የላት፤ … ወጥታ ቤተ ክርስቲያን በረንዳ ላይ ተቀመጠች። ቀኑ እየመሸ ሲሄድ መጠጊያ ስለሌላት እዚያው በረንዳ ላይ ለማደር ወሰነች፡፡ በዚህ ጊዜ አማርኛ የሚናገሩ አንድ ኢጣሊያዊ ቄስ፤ አይተዋት ጠጋ ብለው ምን እንደሆነች ጠየቋት፡፡ እሷም ታሪኳን ዘርዝራ አጫወተቻቸው፡፡ ቄሱም፤ “ልትወልጂ ድርስ ስለሆንሽ መንገድ ላይ ማደር የለብሽም፤ እኔ ቦታ አገኝልሻለሁ” ብለው ወደ ማዘር ቴሬሳ የሴቶች መጠለያ ወሰዷት፡፡
መጠለያው ውስጥ በአልኮል፤ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በሴተኛ አዳሪነት፣ … ወንጀል የተከሰሱ ሴቶች ነበሩ፡፡ ራሷን ከእነሱ ጋር አመሳስላ ቆየች፡፡ እዚያ በገባች በ6ኛ ቀኗ ልጇን ወለደች፡፡ ከ3 ወር በኋላ የቤት ውስጥ ሰራተኛነት ስራ አግኝታ ወጣች፡፡ ሳህን እያጠበች፣ ቤት እያፀዳች፣ ምግብ እየሰራች፣ ልብስ አጥባ እየተኮሰች፣ … አጠቃላይ የቤት ውስጥ ስራ እየሰራች ልጇን አሳደገች፡፡ ስራውን ወድዳና አክብራ፣ ልጇ 11 ዓመት እስኪሞላው ድረስ እዚያው ቤት ሰራች፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ መጥፎ አጋጣሚ ተፈጠረ - አሰሪዋ ሞቱ፡፡
እሷም “እስከ መቼ ድረስ ነው በቤት ሰራተኝነት የምቀጥለው? ይኼ ስራማ የህይወቴ መጨረሻ መሆን የለበትም፤ ልጄ ነፍስ ካወቀልኝ ህይወቴን የመለወጥ ትልቅ ህልም አለኝ፡፡” በማለት አሰበች። ምን እንደምትሆን፣ ምን እንደሚያጋጥማት አታውቅም፡፡ ሆኖም “በምንም ዓይነት መንገድ እንደዚህ ሆኜ መቅረት የለብኝም፡፡ ጠንክሬ በሥነ - ሥርዓት ከሰራሁ፤ እለወጣለሁ” የሚል እምነትና ጥንካሬ በውስጧ ስለነበር፣ ሁለተኛ የስደት ህይወት ለመጀመር ልጇን ይዛ አሜሪካ ገባች፡፡
አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሪችሞንድ በተባለች ከተማ አረፈች፡፡ እዚያም ሳሉቴ ኢቪታ (በጣሊያኒኛ ጤና ማለት ነው) በተባለ ሬስቶራንት ውስጥ በሰዓት ሰባት ዶላር እየተከፈላት፣ እንግዳ ሲመጣ ተቀብሎ ማስቀመጥ ሥራ አገኘች። በዚያን ጊዜ ለእሷ 7 ዶላር ትልቅ ገንዘብ ነበር። ሥራዋ፤ በፈገግታ እንግዶችን ተቀብሎ ወንበር ሰጥቶ ማስቀመጥ ቢሆንም፣ ስራው እንዳያመልጣት በማለት የማትሰራው ነገር አልነበረም፡፡ ግድግዳ ታጥባለች፣ መስኮት ትወለውላለች፣ ወለል ታፀዳለች። የሥራ ባልደረቦቿ “ይኼ ያንቺ ስራ አይደለም፡፡ ያንቺ ስራ ጥሩ ለብሶ፣ በር ላይ ቆሞ በፈገግታ ሰዎችን መቀበልና ማስቀመጥ ብቻ ነው” በማለት ይመክሯት ነበር፡፡ እሷ ግን ምክራቸውን አልተቀበለችውም፡፡ ኢጣሊያ እያለች ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ያለ ዕረፍት ትሰራ ስለነበር፣ አልከበዳትም፤ እንዲያውም አጠነከራት እንጂ፡፡ ደሞዟም 8፣ 9፣ 10፣ … ዶላር እያለ አድጎ የማታ ማታ የሬስቶራንቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነች፡፡
በዚህ ዓይነት ለ6 ዓመት እንደሰራች ባለቤቱ ሳሉቴን መሸጥ ፈለገና ለሰራተኞቹ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ በውሃ ላይ የተሰራ፣ ሳንፍራንሲስኮን ዙሪያዋን ማሳየት የሚችል በከተማዋ (ሪች ሞንድ) ትልቅ ሬስቶራንት ነበር ሳሉቴ፡፡ በሬስቶራንቱ ውስጥ መንበረ ተወዳጅ፡፡ ተወዳጅነትን ያገኘችው የኢጣሊያ ቋንቋ አቀላጥፋ ስለምትናገር፣ ጠንካራ ሰራተኛ ስለሆነች፣ የተዋናይነት ስሜትና ተግባቢነት በውስጧ ስላለ ነው፡፡ የእሷን ጥንካሬና ቅልጥፍና ለማየት የሚመጡ ደንበኞች “መንቢን ልናጣ ነው፣ ምን ይሻላል?” ይሉ እንደነበር ተናግራለች፡፡
ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ፣ ያላሰበችውና ያልጠበቀችው ነገር ተፈጠረ፡፡ “ስራ ፈልጉ” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፣ አንድ በስራዋና በቅልጥፍናዋ እንዲሁም በቋንቋዋ ይማረክ የነበረ ኢጣሊያናዊ ደንበኛቸው፣ “መንቢ፣ ምንድነው እቅድሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡ እሷም፤ “ምንም! እቅድ የለኝም፡፡ ስራ እፈልጋለሁ፣ ወይም ሬስቶራንቱን የሚዙ ሰዎች ከቀጠሩኝ እዚሁ እሰራለሁ” አለች። ያ ኢጣሊያናዊ በማግሥቱ ከልጁና ከሚስቱ ጋር መጥቶ፣ “መንቢ፣ እኔም እንዳንቺ ከጣሊያ አገር በ13 ዓመቴ ወጥቼ ነው እዚህ ሀብታም የሆንኩት። ዓለም ለእኔ ጥሩ ስለሆነች ያገኘሁትን ሁሉ መልሼ ለሌሎች ሰዎች መስጠት አለብኝ” አላት፡፡ “እናስ?” በማለት ጠየቀችው፡፡ “እናማ፤ የትም አትሄጂም። ገንዘብ አበድርሻለሁ፡፡ ይህንን ሬስቶራንት ትገዣለሽ” አላት። መንበረም፣ “እኔ አልችልም። በምን እውቀቴ ነው የማስተዳድረው?” አለች፡፡ “ምንም እውቀት አያስፈልግሽም፡፡ ጠንካራ ሰራተኛ ነሽ፡፡ ለሬስቶራንቱ 24 ሰዓት ትሰሪ ነበር። ወደፊትም 24 ሰዓት መሥራት ነው፤ ለውጥ የለውም” በማለት ብትከስርም ምንም እንደማያገኝ እያወቀ     “በአምስት ዓመት ትከፍይኛለሽ፤ ካልቻልሽም ሌላ እጨምርልሻለሁ” በማለት አስፈርሞ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር አበደራት።
መንበረ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ጠንካራ ሰራተኛ ስለሆነች፣ ብዙ ችግር ያሳለፈች፣ መኖሪያ አጥታ መጠለያ ውስጥ የኖረች ስለነበር … እኒህ ሁሉ መከራዎች ድፍረትና ጥንካሬ ሰጧት፡፡ ሌት ተቀን ጠንክራ በመስራት የአምስት ዓመቱን ብድር በአንድ ዓመት ከፍላ ጨረሰች፡፡ ይህን ዕዳ ለመክፈል ያየችው ፍዳ አይጣል ነው፡፡ ሌሊት መነሳት፣ ከወዲያ ወዲህ ሲወዛወዙ መዋል እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ከመድከሟና ከመዛሏ የተነሳ መኪና መንዳት አቅቷት፣ ሦስትና አራት ቀን ሬስቶራንቱ ውስጥ ለማደር እንደተገደደች ትገልጻለች፡፡ “ዛሬ እኔም ሬስቶራንቱም ታዋቂ ሆነናል” ትላለች፤ መንበረ። በሳሉንቴ ሬስቶራንት 6 ዓመት በአስተናጋጅነት፣ 16 ዓመት በባለቤትነት በአጠቃላይ ለ22 ዓመታት መስራቷን፣ ሬስቶራንቱ 18 ሰራተኞች እንዳሉት ተናግራለች፡፡ መንበረ “እግዚአብሔር ለእኔ እንዲህ ደግ ከሆነ፣ እኔስ ምንድነው ማድረግ ያለብኝ” በማለት አሰበች፡፡ እዳዋን ከፍላ ከጨረሰች ከአንድ ዓመት በኋላ፤ “እኔም ከእነሱ አንዷ ነበርኩ” በማለት ጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰበች፡፡ በዓመት አንድ ቀን “የድሆች ቀን” በማለት፣ 1,500 ለሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች እራት ታበላለች፡፡ በሥነ ስርዓት ተቀብለው፣ ሁለትና ሶስት ሹካ አስቀምጠው፣ ክሪስታል ብርጭቆ አኑረው፣ እንደማንኛውም 100ና 200 ዶላር እንደሚከፍል እንግዳ ተስተናግደው ይሄዳሉ፡፡ ሐኪሞችን በማስተባበር ኢንፍሉዌንዛ እንዳይዛቸው ክትባት እንዲያገኙ፤ የደም ግፊት ካለባቸው እንዲለኩና ምክር እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ በራባቸው ጊዜ ደግሞ ወደ ሬስቶራንቱ መጥተው ምግብ እንዲወስዱ ነግረው ያሰናብቷቸዋል፡፡
ይህ በየዓመቱ የሚደረግ ግብዣ መንበረን በአሜሪካ እንድትታወቅ አደረጋትና “ሆሊ ኔምስ” የተባለ ዩኒቨርሲቲ፣ “ስደተኛ ሆና ይህን የመሰለ የተቀደሰ ተግባር በመፈጸሟ ልትሸለም ይገባል” በማለት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደሰጣት ገልጻለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እሷን እያዩ ፈረንጆችም መተባበር ስለጀመሩ፣ በከተማዋ አስተዳደር የሚመራ ፋውንዴሽን ከፍታለች፡፡ ይህ ደግሞ ለሌላ ተግባር አነሳሳት፡፡
አሜሪካ ውስጥ “ማዘርስ ዴይ” ይከበራል። በዚህ ዕለት ባል ያላቸው ዕድለኛ እናቶች የሽቶ፣ የአበባ … ስጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡ ጥሩ እራትም ይጋበዛሉ። መንበረ፤ በእናቶች ዕለት “በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ድሃ እናቶችን እናስብ” በማለት በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩትን እናቶች በሙሉ አሰባስባ እራት ታበላለች። ድሃ እናቶች ወደ ግብዣው ስፍራ ከመምጣታቸው በፊት ልጆቻቸውን የሚጠብቅላቸው ሰው ይመደብላቸዋል፣ ፀጉራቸውን እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ የአዕምሮ ሐኪሞችን አስተባብራ እንዲመረምሯቸው፣ እንዲመክሯቸውና እንዲያበረታቷቸው ታደርጋለች፡፡
የልጃገረዶች ፕሮጀክትም አላት፡፡ ጥሩ ውጤት ኖሯቸው ትምህርት ቤት መሄድ ለማይችሉ 8 ልጃገረዶች በየወሩ እየከፈለች በግል ት/ቤት እያስተማረች ነው፡፡ ይህ የልጃገረዶች ፕሮጀክት ወደ ኢትዮጵያም ዘልቋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ የእናቷ ቤት በነበረበት ቦታ፣ ባለ 3 ፎቅ ህንፃ በ300 ሺህ ዶላር አሠርታ፣ 80 ልጃገረዶችን ለማስተማር ዝግጅት መጀመሯን ገልጻለች፤ ወ/ሮ መንበረ አክሊሉ፡፡
ያ በኢጣሊያ ማዘር ቴሬሳ መጠለያ ውስጥ የተወለደው የመንበረ ልጅ፤ በሚቀጥለው ዓመት ከኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ይመረቃል።     
ወ/ሮ መንበረ በዳንግላ ከተማ ጋሹና ሆቴል ውስጥ ሼፍ ሆና ስትሰራ፣ የቀድሞ ፍቅረኛዋ ፊቷ ላይ አሲድ ደፍቶባት ጉዳት ለደረሰባት መሰረት ንጉሤ 5 ሺህ ዶላር መላኳን፣ ሐኪሞች፣ የመሠረትን ጉዳት አይተው መታከምና መዳን እንደምትችል ስለገለጹላት አሜሪካ ወስዳ ለማሳከም ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ተናግራለች፡፡   

Read 3072 times